Get Mystery Box with random crypto!

_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳፩__ አንቀጽ ፴፫ ስለመሸጥና ስለመግዛት ይናገራል። | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳፩__
አንቀጽ ፴፫ ስለመሸጥና ስለመግዛት ይናገራል።

እሑድ፣ በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላት መሸጥ መግዛት አይገባም። [አክብሩ ያለውን ሥርዓር ማፍረስ ነውና። ቁጥር ፲፻፩፻፬]

፩) ሻጭና ገዥ በገንዘባቸው ቢያዙ ቢሰለጥኑ ነው እንጂ ካላዘዙ ካልሰለጠኑ መሸጥ መግዛት አይጸናም አይፈጸምም። አውቀው ወደው መዋዋል ይገባቸዋል።
+
፪) ሻጭና ገዢ በዋጋ ሳይስማሙ ቢለያዩ መሸጥ መግዛት ትቀራለች። መሸጥ መግዛት በሁለቱ ፈቃድ ነውና።
+
፫) በደብዳቤም ያለ ደብዳቤም የሚሆን መሸጥና መግዛት አለ። ደብዳቤ የሚናገረው በዋጋ መስማማታቸውን፣ ውሉን፣ የሚሸጡትን የከብቱን አኳኋን፣ የዋጋውን ቁጥር፣ የቀኑን ልክ፣ ዓመተ ምሕረቱን ነው። ያለ ደብዳቤ የሚሆን ዋጋ ዐረቦኑን (ቀብዱን) በመቀበል ይሆናል። ያለ ዐረቦንም ይሆናል።
+
፬) ሻጭ ቦታ የሚሸጥ ከሆነ ለይቶ ይሽጥ። ተክሉንም ይጨምራል ወይስ ቦታውን ብቻ የሚለውን ለይቶ መንገር አለበት።
+
፭) ሻጭ ለገዢ የሸጠለት ንብረት ቢጠፋ ከሻጩ እንዳለ ከጠፋ ገዢው አይጠየቅም። ገዢው ከተረከበ በኋላ ቢጠፋበትም ሻጭ አይጠየቅም።
+
፮) የተሸጠው ነገር ከተሸጠ በኋላ እጅ እግሩ ቢሰበር ዓይኑ ቢጠፋ፣ ቤት ቢሆን ቢቃጠል፣ ሀገር ቢሆን በመላው ውሃ ቢተኛበት፣ ወይም የተወሰነው ቢጎደጉድ፣ ናዳ ቢወስዳት፣ ቤቶቿ ቢፈርሱ፣ ዛፎቿ እየተነቀሉ ቢወድቁ አንድም ቢደርቁ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን በሻጭ ምንም ተንኮል ሳይኖርበት የተደረገው ሁሉ ለገዥ ሀብቱ ነው። ሻጭ ከዕዳ ይድናል።
+
፯) ከብት የሸጠ ሰው ቢኖር ገዡ እስኪፈትነው ሦስት ቀን ወይም አራት አምስት ቀን ይስጠው። ፈተናውን ባይወጣ ገዢ ለሻጩ መመለስ ይገባዋል። ገዢ ከወደደውና በኋላ ግን የራሱ ይሆናል።
+
፰) ሰው ሁሉ ንግድ አወቅሁ ብሎ ከሚገባው ዋጋ አዋርዶ መግዛት ነውር ነው። [ቁጥር ፲፻፺፫]። ሻጭ ለገዢ የሸጠለት ተዋጊ በርጋጊ አበያ በሬ መሆኑን ሳይነግረው ከሆነ፣ ሌላም ነገር ቢሆን ነውሩን ሳይነግረው ከሸጠለትና ገዢው በኋላ ቢያውቅ ሻጭ ለገዢው መክፈል ይገባዋል።
+
፱) [ቁጥር ፲፻፺፯] ያመኑትን አገልጋዮች ላላመኑ ሰዎች መሸጥ አይገባም። ለቤተክርስቲያን የጎለቱትን ጉልት መሸጥ አይገባም። ጠብቅልን ብለው በአደራነት የሰጡትን በገንዘብ መሸጥ አይገባም።
+
፲) ይዞ መስጠት የማይቻለውን መሸጥ አይገባም። ይኽውም ምሳሌ በወንዝ ያለውን ዓሣ ሽጨልሀለሁ ወንዙ የእኔ ነው ዓሣውን ሽጨልሀለሁ አይበል። በክንፍ የሚበረውን ቆቁን ጅግራውን ሽጨልሃለሁ አይበለው። አዳኝ በዱር ያለውን ፌቆውን ዋልያውን ድኩላውን ሳይያዝ መግዛት አይገባውም።
+
፲፩) ለጣዖት የተሠዋውን፣ ሙቶ ያደረውን፣ የአውሬውን ትራፊ፣ በመርዛቸው የሚገድሉ እንስሳትን ሥጋ፣ የሚገድሉ መርዛም እፀዋትን፣ አራዊትን መግዛት አይገባም።
+
፲፪) ፈጽመው የማይረቡትን የማይጠቅሙትን መሸጥ መግዛት አይገባም። ፅንሱን ከእናቱ ለይቶ መሸጥ አይገባም። ፍሬው ሳያፈራ ቡቃያውን፣ ሳይታለብ ወተቱን፣ በማድጋ ውስጥ ያለውን ማር ሳያሳዩ መሸጥ ሳያዩ መግዛት አይገባም።
[ሐተታ እስከ ሥዑል ሚካኤል ድረስ ይሸጥ ነበር። በሥዑል ሚካኤል ጊዜ አንድ ሰው የቅሉን የዱባውን አንጀት ጨምሮ ላዩን ማር ቀብቶ ሽጧል። ከዚያ ወዲህ ሻጭም አሳይቶ ገዢም አይቶ ይግዛ ተብሎ አዋጅ ተነግሯል]
+
፲፫) የአንድነት ቦታዎችን መሸጥ አይገባም። ይኽውም አውራ ጎዳናን፣ የሁሉ መውጫ መጋጫ ሜዳን፣ ወንዝን መሸጥ አይገባም። ጡት ሳይተው ጥጃን ወይም ሌላን እናቱን ከልጇ ለይተው መሸጥ አይገባም።
+
፲፬) ከሌባ መግዛት አይገባም። ጥፋትን ለሚያመጡ ሰዎች መሣርያ መስጠት አይገባም። ጽፈው ያዘዙለት ሐፃኒ ከሕፃናቱ ገንዘብ ማናቸውንም መግዛት አይገባውም።
+
፲፭) እሑድ፣ በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላት መሸጥ መግዛት አይገባም። [አክብሩ ያለውን ሥርዓር ማፍረስ ነውና]
+
አንቀጽ ፴፬
ይህ አንቀጽ ስለተሳትፎ ይናገራል። ተሳትፎ የሚለው አንዱ በከብት አንዱ በጉልበት ሆነው የሚነግዱት ንግድ ነው።
+
፩) ተሳትፎ በገንዘብ በማይተካከሉ ሰዎች መካከል ትጸናለች። ገንዘብ የሌለው ድኃ በትርፉ አንድም በጉልበቱ ፈቃዱን ይፈጽማልና። [ድኃ በጉልበቱ ባለጸጋ በከብቱ እንዲሉ]
+
፪) በተሳትፎ የገንዘቡ ልማትም ጥፋትም ለሁለቱም ሊሆን ይገባል። በአንድነቱ ገንዘብ ለባልንጀራው ቀርቶበት አንዱ ብቻ ሊያዝበት አይገባውም።
+
፫) አንድነት ከገቡ ሰዎች ሁሉ እያንዳንዱ በቃን በቃን ቢሉ፣ አንዱ አንዱን ሽማግሌ ልኮ ገንዘቤን ስጠኝ ቢለው፣ በዳኛ ቢይዘው አንድነት ትቀራለች። ትቅር።
+
አንቀጽ ፴፭
ይህ አንቀጽ ስለ አገብሮና ስለ ተኃይሎ ይናገራል። አገብሮ የሚለው የግድም የውድም የሆነን ነገር ነው። ተኃይሎ ግን የግድ የሆነ ነገር ነው።
፩:- አገብሮ ሃይማኖትህን ካድ ብሎ ቢያገብረው በፍጹም ልቡናው ቢያምን መከራውን እንጂ አገብሮውን መቀበል ፈጽሞ አይገባም።
+
፪:- ሃይማኖቴን አልክድም ብሎ መከራ የሚቀበል ሰው በሰማዕትነት ቢሞት ሰማዕት ዘበደም ይባላል። ለሃይማኖቱ የታመነ ምስክር ሆኖ ከመከራ ቢድን ሰማዕት ዘእንበለ ደም ይባላል።
+
፫:- አንዱ አንዱን ሕግ አፍርስ፣ ነፍስ ግደል፣ ሰስን ብሎ ቢያገብረው አገብሮውን መቀበል አይገባም። ያገኘውን መከራ ታግሦ መቀበል እንጂ።
+
፬:- (ተኃይሎ) ቀማኛ ባዕለጸጋ ቢሆን) በአንድ አራት በአንድ አምስት ይክፈል። ይህን ካልተቻለው እትፍ ይክፈል። ይህንም ካልቻለ ዓይነታውን ይመልስ። (ሐተታ) ምእመናንን ከሰደበ ኤጲስ ቆጶሱን የሰደበ ሰው ቅጣት ይጸናል።
+
፭:- የሰው ልብስ የቀደደ ሰው ጉዳያውን (የተቀደደውን የሚተካ) ይክፈል።
+
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፳፪ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው