Get Mystery Box with random crypto!

__ዲድስቅልያ ክፍል ፭__ √አንቀጽ ፳፭ ፲፯:- የሙታን ትንሣኤ በክርስቶ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ዲድስቅልያ ክፍል ፭__
√አንቀጽ ፳፭
፲፯:- የሙታን ትንሣኤ በክርስቶስ ዳግም መምጣት ነው።
፳፰-፴:- ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ወንጀለኞችን ስሙ ፊንክስ የሚባል ተፈጥሮው አንድ የሚሆን ወፍ ያስረዳቸዋል። ወደ አመድነት ከተለወጠ በኋላ በትል መልኩ እንደገና ታድሶ ይነሣል
፴፪:- ሰውን ካለመኖር የፈጠረ እግዚአብሔር በፍጹም ከሃሊነቱ ሙታንን ማስነሣት አይችልምን?? (ያስነሣል)።
√አንቀጽ ፳፮
፩:- እነሆ ሰማዕታትን ከፍ ከፍ አድርጓቸው ፈጽማችሁም አክብሯቸው።
√አንቀጽ ፳፯
፩:- የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ ዘፈንን ከማድመጥና ከጨዋታ ነገር፣ ከተድላ ደስታና ከመባልዕት ጣዕም፣ ረብህ ጥቅም ከሌለው ከብላሽ ሥራም ሁሉ ትርቁ ዘንድ በጎ ምክርን እንመክራችኋለን።
√አንቀጽ ፳፰
፳:- በራስህ አትማል። አላዋቆች አይሁድ በራሳቸው ይምላሉና።
፳፩:- የምእመናን ነገራቸው እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት ማለት ነው።
√አንቀጽ ፳፱
፩-፱:- የበዓላትን ቀን ጠብቁ። እነዚህም በዓለ ልደት ታኅሣሥ ፳፱፣ በዓለ ጥምቀት ጥር ፲፩
፲-፲፪:- በሆሣዕና ማግሥት ሰኞ ቀን ሕግንና ሃይማኖትን የካዱ ክፉዎች አይሁድ ተሰብስበው በጌታ ላይ ተማክረዋል። ማክሰኞ ቀን ምክርን ጨመሩ፣ በረቡዕ ቀን ምክርን ፈጸሙ።
፷፰:- የተለየች የፋሲካ ጾምን ስድስት ቀን እንጹም።
፷፱:- ዳግመኛም ዓርብ ረቡዕን እንጹም።
፸:- በቀዳሚት ሰንበት እንዳንጾም መሆን አገባብ ነው። መከራን ከተቀበለባት ከቀዳም ሥዑር በቀር።
√አንቀጽ ፴
፩:- የሕማማትን መታሰቢያ በዓመት አንድ ጊዜ ያድርጉ።
፰:- ትንሣኤ በተቀደሰች የክርስቲያን ሰንበት ይሁን።
፲-፲፪:- በሕማማት ሳምንትም በጨው ከተሠራ ቂጣና ከውሃ በቀር ምንም አትብሉ አትጠጡ። የቻለ በየሁለት ቀኑ ይጹም። ያልቻለ በቀን በቀን ይጹም።
፴፰:- ጌታ ካረገም በኋላ በአሥረኛው ቀን በዓለ ሃምሳ ሲፈጸም በዓልን አድርጉ።
√አንቀጽ ፴፩
፵፯:- የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ በማርያምና በዮሴፍ ሩካቤ በሥጋ ፈቃድ ተወለደ የሚሉ ከኃድያን ፍዮኒዮክን ይባላሉ።
√አንቀጽ ፴፫
፵፮-፵፯:- የእሪያዎች ሥጋ ንጹሕ ነው የሚሉ አሉ። ነገር ግን ርኩስ ነው እንጂ ንጹሕ አይደለም። በመጽሐፍ ንጹሕ የሆነውን ግን ከእርሱ ይብሉ። (ይህ ሥርዓት ልክ ኤጲስ ቆጶስ አንድ ያገባ ይሁን እንደሚለው በሐዋርያት ዘመን የነበረ በኋላ በሠለስቱ ምእት የተሻሻለ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት እርያ የሚበላ ርኩስ ነው አይባልም)።
√አንቀጽ ፴፫
፭:- (ስለ ሥላሴ) ሁለት አይደለም። በሦስትነቱም አራተኛ አይጨመርበትም። ብቻውን ለዘለዓለሙ የሚኖር አንድ ነው እንጂ።
፲፬:- እንግዲህ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ መልካም እንደሆነ እንናገራለን።
፺፯:- እናንተ ግን ልጆቻችሁን ሕፃናት ሳሉ አጥምቁ። መንፈሳዊ ምግብንም መግቧቸው። በምክርና በጥበብም አሳድጓቸው።
፻፴፬:- ሥርዓት ጽድቅ ነው።
፪፻፳፰:- ሴቶች ለባሎቻቸው በፍቅርና በፍርሀት ይታዘዙ። ክብርት ሣራ ለባሏ ለአብርሃም ትታዘዘው ጌታዬም ትለው እንደነበረ። ጌታዬ አለቃዬ ትለው ነበር እንጂ በስሙ አትጠራውም ነበርና።
፪፻፴:- የልጅነት ሚስትህን ውደድ። የአንተ ናትና። ሁልጊዜም ከአንተ ጋር ትኖራለችና። አካልህም ናትና።
√አንቀጽ ፴፬
፩-፪:- ስለሞቱ ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቡ። ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙንም በምስጋና በቤተክርስቲያን አሳርጉላቸው። በመቃብርም የዳዊትን መዝሙር በፊታቸው አንብቡ።
፱:- የሞቱትን ሰዎች በድን በዳሰሳችሁ ጊዜ አጽማቸውን መሸከም አትጸየፉ። ስለእነርሱ የምትረክሱ አይደላችሁምና።
√አንቀጽ ፴፭
፯-፰:- ማንንም እንዳትጠሉ ዕወቁ። ሰውን ሁሉ አትጥላ። ግብፃዊውንም ቢሆን ኤዶማዊውንም ቢሆን ሁሉም የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ናቸውና።
፱:- ነገር ግን ከክፉ ሰዎችና ከዚህ ዓለም ፈቃድ ራቅ።
፴፪:- ቁጡና ቀናተኛ አትሁን።
፴፰:- በአንተ ላይ የሚመጣውን መከራ ሁሉ ተቀበል። እንደ ኢዮብና እንደ አልዓዛር ከእግዚአብሔር ዋጋህን ትቀበል ዘንድ።
፵:- የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማረህን አክብር። በቀንና በሌሊትም አስበው።
፵፪:- ጠብ ያለባቸውን ሰዎች አስታርቃቸው በእውነትም ፍረድ። ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና።
፵፰:- ለንጉሥም ተገዛ ሹመቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ እወቅ። ገዢዎችን አክብር። እነርሱ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸውና።
፵፱:- ከክፉ ሥራህ ሳትመለስ ክፉ እየሠራህ መሥዋዕትን አታቅርብ።
√አንቀጽ ፴፮
፰:- አሥራትንም ሁሉ ለባልቴቶችና ለድሃ አደጎች፣ እናት አባት ለሞቱበት ለእንግዶች እና ለድሆች ስጡ።
√አንቀጽ ፴፯
፪:- የመላእክት የወገን ስማቸው መላእክት፣ መናብርት፣ ሥልጣናት፣ አጋዕዝት፣ ኃይላት፣ ሊቃናት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይባላሉ። ሌትና ቀንም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።
√አንቀጽ ፴፰
፲፪:- ጌታ በሰንበት እናርፍ ዘንድ አዘዘን። ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ቀን ናትና።
፲፭:- (የክርስቲያን ሰንበትንም እናክብር)
√አንቀጽ ፴፱
፩:- ለሚጠመቅ ሰው (ንዑሰ ክርስቲያን) የምክር ቃልን ያስተምሩት።
፲፪:- ሊጠመቅ የሚወድ ንዑሰ ክርስቲያን ሰይጣንን ያውግዝ። በክርስቶስ ስም ይመን። የቀደመ ልማዱንም ይተው።
√አንቀጽ ፵
በማይ ላይ ስለሚጸለይ ጸሎት ይናገራል።
√አንቀጽ ፵፩
በሜሮን ላይ ስለሚጸለይ ጸሎት ይናገራል።
√አንቀጽ ፵፪
ሐዲስ አማንያን ሲጠመቁ የሚጸለይ ጸሎትን ይናገራል።
√አንቀጽ ፵፫
በሐዋርያት ስለተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ስም ዝርዝር ይናገራል።
++++++
ተፈፀመ
አነሳስቶ ላስጀመረን
አስጀምሮም ላስፈጸመን
ልዑል እግዚአብሔር
ምስጋና ይገባል አሜን።
መ/ር በትረማርያም አበባው