Get Mystery Box with random crypto!

__ዲድስቅልያ ክፍል ፫__ √_አንቀጽ ፯_√ ፩:- ያልበደለውን የሚያሳድድ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ዲድስቅልያ ክፍል ፫__
_አንቀጽ ፯_√
፩:- ያልበደለውን የሚያሳድድ ሰው ከነፍሰ ገዳይ ይከፋል።
፶:- ኤጲስ ቆጶስ ለቤተክርስቲያን ከሚገባው አሥራትና ከእህሉ ቀዳምያት ይመገብ።
፶፩:- ኤጲስ ቆጶሱም ለድኃዎች፣ የዕለት ራት ለሌላቸው ጦም አዳሪዎች፣ ለባልቴቶች፣ እናትና አባት ለሞቱባቸው ልጆች፣ ለስደተኞች፣ ምንም ለሌላቸው መፍቅዳቸው ይሰጥ ዘንድ ይገባዋል። ኤጲስ ቆጶሱ ግዳጃቸውን ባይሰጣቸው ግን ስለእነርሱ እግዚአብሔር ይመራመረዋል።
፷፰:- ያልነጹትን እንስሳት በኩራትና የሰውን በኩራት መቤዠት ነው።
_አንቀጽ ፰_√
፱:- ዲያቆናዊት ሴት ያለዲያቆኑ ፈቃድ ምንም ምን አትሥራ። ማንኛዋም ሴት ከዲያቆናዊት ጋር ካልሆነች በቀር ወደ ዲያቆኑ አትሂድ። እንደዚሁም ሴት ከዲያቆኑ ጋር ካልሆነች በቀር ወደኤጲስ ቆጶሱ አትግባ።
፲:- እንግዲህ ካህናትን አክብሯቸው ይመክሯችኋልና። የእግዚአብሔርንም መንገድ ያስተምሯችኋልና።
፲፩:- ኤጲስ ቆጶሱ ለተቸገሩት ሁሉ ያዝን ዘንድ ሕይወታቸውንም ይመረምር ዘንድ ኑሯቸውንም ይረዳ ዘንድ ይገባዋል።
፲፱:- ዲያቆናት የሕዝቡን ችግር ሁሉ ለኤጲስ ቆጶሳት ይነግሯቸው ዘንድ ይገባል።
፳፪:- ኤጲስ ቆጶሳት የእግዚአብሔር አፍ እንደሆኑ እናስብ።
_አንቀጽ ፱_√
፩:- ዲያቆን ለኤጲስ ቆጳሱ መልእክተኛ ነው።
፯:- ከእግዚአብሔር በታች አባት ለሆነህ ለኤጲስ ቆጶሱ እጅ ንሣ።
፲፪:- ክህነት ከመንግሥት ትበልጣለች።
_አንቀጽ ፲_√
፲፰:- ኤጲስ ቆጶስ ሆይ ኃጥአንን እርዳቸው በእግዚአብሔር ቃልም አጽናቸው። አትናቃቸው ከእነርሱም ጋር መብላትን እንቢ አትበል። ጌታችን ከኀጢአተኞችና ከቀራጮች ጋር መብላትን እንቢ አላለምና።
፵፪:- ኤጲስ ቆጶስ ሆይ ንኡሰ ክርስቲያንን በምታጠምቅበት ጊዜ እንዲህ አድርግ። ተቀብለህ በላያቸው ላይ እጅህን ጫንባቸው። በንስሓ ነጽተዋልና።
፶:- ኤጲስ ቆጶስ ሆይ አንተም እንደ ብልህ ባለመድኃኒት ኃጥአንን አድናቸው። ከኃጢአት ቁስልም ፈጽመህ አድናቸው።
፸፩:- ከቤተክርስቲያን ሹሞች በቀር ሕዝባዊ አይፍረድ። ሽማግሌዎችም አይፍረዱ።
፸፪:- ምሥጢራችሁን ያውቁ ዘንድ ለአሕዛብ አትፍቀዱላቸው።
፹፭:- ሐሰትን ከመናገር ተጠበቁ። ሐሰትን የሚናገር ሰው በብዙ ይፈረድበታልና።
፹፯:- የዋሆች፣ የማይቆጡ፣ ንጹሓን፣ ቸሮች፣ ትሕትናን የሚወዱ፣ የታመኑ፣ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ምስክር ይሆኑ ዘንድ አግባብ ነው። የንጹሓን ሰዎች ምስክርነት ይገባልና።
፹፱:- ለፍርድ ወደ እናንተ የመጣ ሰው ቢኖር ግብሩና ልማዱ እንዴት እንደሆነ ሕይወቱን መርምሩ።
፺፪:- የከሰሰ ሰው ቢኖር ሁለቱም በአንድነት በአደባባይ ሳይኖሩ ለአንዱ አትፍረዱ። (ከሳሹም ተከሳሹም መኖር አለባቸው)
_አንቀጽ ፲፩_√
፫:- የወንድምህን በደል አራት መቶ ዘጠና ጊዜ ይቅር ብትል ግን ራስህን ታድን ዘንድ ቸርነትህ የበዛ ቁጣህም ያነሰ ሆንክ። እንዲህም ብታደርግ የሰማያዊ አባትህ ልጅ ትሆናለህ።
፬:- ኤጲስ ቆጶሳት ሆይ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቡ።
፰:- ኤጲስ ቆጶሳት ሰላምን የሚያደርጉ፣ እነርሱንም የበደሏቸውን ይቅር የሚሉ፣ ርኅሩኃን ወይ እግዚአብሔር የሚመለሱትንም ንስሓቸውን የሚቀበሉ ይሆኑ ዘንድ አግባብ ነው።
፳፪:- በንስሓ ፈጽማ የዳነችውን ነፍስ በቁጣና በብስጭት አትግደሉ።
፴:- እንግዲህ ቤተክርስቲያን እንዲህ ትሁን። ርዝመቷ በምሥራቅ በኩል ይሁን። በጎንና በጎንም በመርከብ አምሳል ሁለት ክፍሎች ይኑሩ። የኤጲስ ቆጶሱ መንበርም በመካከል የተዘጋጀ ይሁን።
፴፯:- ወንጌልም በሚነበብበት ጊዜ ቀሳውስት ዲያቆናት ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ፍርሀት ይቁሙ።
፵፩-፵፪:- የሚበቃቸው ቦታ ባይኖር ወንዶች ልጆች በአባቶቻቸው ፊት ይቀመጡ። ሴቶች ልጆችም ብቻቸውን ይቀመጡ። ቦታ ባይኖር ግን ባገቡት ሴቶች ኋላ ይቁሙ። ደናግልና መበለቶች ባልቴቶችም በሴቶች ፊት ይቁሙ። ባልና ልጅ ያላቸው ሴቶች ግን ብቻቸውን ይቀመጡ።
፵፬:- (በቤተክርስቲያን ውስጥ) በሳቅና በዋዛ የሚገኙ ሰዎች ቢኖሩ ዲያቆኑ ይምከራቸው። ዝም እንዲሉም ያድርጋቸው።
፵፮:- ንዑሰ ክርስቲያን ይውጡ ብሎ ዲያቆኑ አሰምቶ በሚናገርበት ጊዜ መምህራንና በንስሐ ያሉ ሰዎች ሕዝቡም ሁሉ ቆመው ወደ ምሥራቅ ይመልከቱ።
፶፮:- ሴቶች ራሳቸውን ተሸፍነው ይቁሙ። ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙንም ይቀበሉ።
፷፰:- በነግህና በሠርክ በቤተክርስቲያን ተሰብስባችሁ መዝ. 62ን እና መዝ. 140ን ዘምሩ
፸:- በክርስቲያን ሰንበት ዕለት የክርስቶስን የትንሣኤውን ስብከት እንሰማ ዘንድ፣ መከራዎቹንም እናስብ ዘንድ፣ መታሰቢያውንም እናደርግ ዘንድ፣ የነቢያትን መጻሕፍትና ቅዱስ ወንጌልንም እናነብ ዘንድ፣ መንፈሳዊ ምግብ የሚሆን መሥዋዕትንና ቁርባንን እናቀርብ ዘንድ ይገባናል።
++++
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፬ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው