Get Mystery Box with random crypto!

_ዲድስቅልያ ክፍል ፪_ √_አንቀጽ ፬_√ ይህ አንቀጽ ስለ ኤጲስ ቆጶስ ይናገራ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_ዲድስቅልያ ክፍል ፪_
_አንቀጽ ፬_√
ይህ አንቀጽ ስለ ኤጲስ ቆጶስ ይናገራል።
፩-፬:- ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ የሚሾመው 50 ዓመት የሞላው፣ ነገር የማይሠራ ሊሆን ይገባል። ሀገሪቷ ትንሽ ብትሆንና 50 ዓመት የሞላው ባይገኝ አዋቂና ብልህ እድሜው ጥቂት የሆነ መሾም ይችላል።
፲-፲፩:- ኤጲስ ቆጶስ የሚሾም ሰው ቂም፣ ክፋትና ዐመፅ የሌለበት ልበ ንጹሕ ይሁን። የማይቆጣ፣ የማይሰክር፣ የማይበቀል፣ ጸብና ክርክር የሌለው፣ የማይሳደብ ይሁን።
፲፯:- የኤጲስ ቆጶስ ምግቡ የላመ የጣመ ይሁን። መጥኖ ይመገብ። ሕዝቡን መክሮ አስተምሮ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይቻለው ዘንድ። ከክፉም ሁሉ ይርቅ ዘንድ መጻሕፍትን ሁልጊዜ ይመልከት።
፳፪:- ኤጲስ ቆጶስ ማንንም ቸል አይበል። መኳንንቱን አይከተል። እግዚአብሔርን ይፍራ።
፳፭:- የሚያስተምረውን የሚሠራ ሰው በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይሆናል።
፳፮:- ኤጲስ ቆጶሳት ሕዝቡን አስተምራችሁ ከስሕተት ታድኗቸው ዘንድ ለእናንተ ይገባል።
፵፪:- ሰው ሐሰትን በላዩ የተናገረበት ቢኖርም ብፁዕ ነው።
፵፮:- ለኤጲስ ቆጶሱ እውነትን ይመረምር ዘንድ ይገባዋል። ከማንም መማለጃን አይቀበል።
፵፱:- ኤጲስ ቆጶስ ባያስተምርና ባይገሥፅ በቅንነት መንገድም ባይሄድ ውግዘት ያገኘዋል።
፶:- በደል ሳይኖርባቸው ንጹሓንም ሲሆኑ በኤጲስ ቆጶሱ ላይ በሹማምንቱም ላይ የሚበድል ቢኖር ወደ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሊገባ አይገባውም። ደፍሮ በራሱ ፈቃድ በስንፍና ኖሯልና።
፷፪:- ሰው ሆይ እወቅ አስተውልም። በዚህ ዓለም ብትበድል ኃጢአትንም ብትሠራ ንስሓም ባትገባ ድኅነት አይኖርህም።
፷፭:- ለኤጲስ ቆጶሱ በእውነት አስተውሎ ይፈርድ ዘንድ ይገባዋል። ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና።
፸፯:- ድል የነሣ ሰው የድል አድራጊነቱን አክሊል ይቀበላል። እግዚአብሔር ጻድቅን ከኃጥእ ጋር አይቀጣምና።
፸፱:- ኃጥአን በጻድቃን እንደማይቀጡ፣ ጻድቃንም በኃጥአን እንደማይቀጡ የታወቀ ነው።
_አንቀጽ ፭_√
፳፩:- ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም። አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም።
፴፩:- ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
_አንቀጽ ፮_√
፩:- እግዚአብሔር ያለምሕረት በማክበድና በልብ ተንኮል የሚፈርዱትን አይወድም።
፫:- አሁንም ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን በደስታና በፍቅር ንስሓቸውብ እንቀበል። የበደሉትንም ለንስሓ እንደሚገባ በፍቅርና በምሕረት እንፍረድላቸው።
፬:- ኀጢአትን የሚሠራ በስሕተትም የሚሰነካከል ሰው ብታይ ከወደቀበት አንሣው። ሥራውን ብታጣጥምለት ግን እነሆ ወንድምህን ገደልከው።
፱:- ለኃጢአተኛ ሰው ያዝንና ይተክዝ ራሱንም ይንቅ ዘንድ ይገባዋል
፲፫:- ያገኘውን ሁሉ የሚነክስ እብድ ውሻ ካልገደሉት የነከሳቸው ሁሉ በአንድነት ከእርሱ ጋር እንደሚያብዱ እንዲሁ የሚዘብት፣ የሚያስት፣ ክርክርንም የሚያመጣ፣ በሕግ ያለውንም ትእዛዝ የሚያፈርስ ሰው ቢኖር የእግዚአብሔርን ቤት እንዳያጠፋ ከቤተክርስቲያን ወደ ውጭ ያውጡት።
፲፬:- ስለ ኃጥአንና ስለ ዐመፀኞች ዝም እንል ዘንድ አይገባንም። ነገር ግን ክፉ ሥራቸውን ይተው ዘንድ እንምከራቸው። እግዚአብሔርንም መፍራትን ይማሩ ዘንድ እንዘዛቸው።
፲፭:- ኤጲስ ቆጶስ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ያዝን ዘንድ ይገባዋል።
፲፯:- ሕዝቡን በሰላም ይጠብቃቸው ዘንድ ለኤጲስ ቆጶሱ አግባብ ነው።
፳፰-፳፱:- ቸር እረኛን የማይከተል ይጠፋ ዘንድ ለጅብ እንደሚሆን እንደዚሁ ሰነፍና ክፉ እረኛን የሚከተል ለሞት ይሆናል። ራሱ እረኛው ይውጠዋልና። ስለዚህ ከማይራሩና መንጋቸውን ከማያድኑ ከክፉዎችና ከከዳተኞች እንርቅ ዘንድ አግባብ ነው። ነገር ግን የሚራሩና መንጋቸውን የሚያድኑ ቸሮች እረኞችን እንከተላቸው።
፴፩:- ኤጲስ ቆጶሱ ሕዝቡን እንደ ልጆቹ ሊወዳቸው ይገባል። እነርሱ ልጆቹ ናቸውና። የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራቸው። ሥርዓትን አያክብድባቸው።
፵:- ለኤጲስ ቆጶስ ኀጢአት በመሥራት የታመሙ ድውያንን ያድን ዘንድ፣ ይጎበኛቸውና ያጽናናቸው ዘንድ ቁስላቸውንም ያድናቸው ዘንድ ይገባዋል።
፵፩:- የክርስቶስን መንጋዎች ሳትቆጣ በሥልጣንህም ሹመት ሳትታበይ በትሕትናና በፍቅር ጠብቅ። የክርስቶስ መንጋዎች ጠባቂ አንተ ነህና።
++++
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፫ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው