Get Mystery Box with random crypto!

_ዲድስቅልያ ክፍል ፩_ ስምንቱ የሕግና የሥርዓት መጻሕፍት የሚባሉት:- ፩) ሥርዓተ ጽዮን | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_ዲድስቅልያ ክፍል ፩_
ስምንቱ የሕግና የሥርዓት መጻሕፍት የሚባሉት:-
፩) ሥርዓተ ጽዮን
፪) ትእዛዝ
፫) ግጽው
፬) አብጥሊስ
፭) ፩ኛ መጽሐፈ ኪዳን
፮) ፪ኛ መጽሐፈ ኪዳን
፯) ቀሌምንጦስ
፰) ዲድስቅልያ
ናቸው። አራቱን ከዚህ ቀደም ተማምረናቸዋል። ዲድስቅልያ ማለት ትምህርት ማለት ነው። የጽርእ ቃል ነው። ዮሐንስ ቅዱስ ጴጥሮስን አበ ዓለም ይለው ነበር። ይህንን ዲድስቅልያ የተባለ መጽሐፍ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ከተማ ተሰብስበው ሠርተውታል።
_አንቀጽ ፩_√
፪:- በቤተክርስቲያን ያሉ የሹመት መዓርጋት በሰማያት ባለው አምሳል እንዲሆን አዘዝን።
፬:- ኤጲስ ቆጶሱ እንደ ጠባቂ ነው። ቀሳውስትም መምህራን ናቸው። ዲያቆናትም አገልጋዮች ናቸው። ንፍቀ ዲያቆናትም ረዳቶች ናቸው። አናጉንስጢሳውያንም በማስተዋል የሚያነቡ ናቸው። አብስሊድሳውያን መዘምራን ናቸው።
፭:- (ምእመናን) የትምህርቱን ቃል ያስተውሉ።
፱:- ለእግዚአብሔር ደስ የማያሰኘውን ሥራ አትሥራ።
፲:- ለራሳችሁ የሚበልጠውን ክፍል መውሰድን፣ ለወንድሞቻችሁ ግን ጥቂት መስጠትን አትውደዱ።
፲፰:- የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ብሩህ ሕጉን የሚጠብቁ ሰዎች ይቅርታንና ምሕረትን ያገኛሉ። ለራስህ የምትጠላውን በባልንጀራህ ላይ አታድርግ። አንተ ሌላው ሰው ሚስትህን ያይ ዘንድ ማንም በተንኮል ያስታት ዘንድ እንደማትወድ እንደዚሁ አንተም የሌለውን ሚስት በክፉ ሕሊና አታስብ። ለራስህም መርገምን ስድብንና መመታትን እንደማትወድ እንደዚሁ አንተም በሌላው አታድርግ።
፲፱:- የረገመህም ቢኖር አንተ ግን መርቀው።
፳፪:- ወዳጆቻችን ሆይ የብርሃን ልጆች እንሆን ዘንድ ትእዛዛትን እናስተውል። እርስበእርሳችን ትዕግሥትን እንያዝ።
፳፫:- ወንድ ሚስቱን ይታገሣት። ትዕቢተኛና ግብዝም አይሁን። ነገር ግን የሚራራና ቅን ይሁን። ለብቻዋም በፍቅርና በትሕትና ደስ ያሰኛት።
፳፮:- የራስህን ጠጉር አታሳድግ፣ ጠጉርህን ቁረጥ።
፳፱:- ጽሕማችንን እንላጭ ዘንድ ለእኛ አይገባም።
፴:- እግዚአብሔርን ደስ ታሰኘው ዘንድ ከወደድህስ ክፉ ሥራን አትሥራ። ፈጣሪህም የሚጠላውን ሁሉ ከአንተ አርቅ። ሰካራም አትሁን። በእጆችህ ሥራ ትረህ ግረህ ተመገብ።
_አንቀጽ ፪_√
፩:- ሥራ ፈት ሆነህ አትኑር። በነገሥትና በነቢያት መጽሐፍ ውስጥ ያለውንም ተመልከት። የምስጋና መዝሙርን ዘምር። የሕግ ሁሉ ፍጻሜ የሚሆን የወንጌልንም ቃል ስማ።
፪:- ለማይረባ ለማይጠቅም ለከንቱ ነገር ሁሉ አትጨነቅ። ከወንጌል ልዩ የሚሆን ሕግንና ሃይማኖትን ለውጠው የሚያጠፉ ሐሰተኞች መምህራንን አትሻ።
፴፰:- በሃይማኖትና በጎ በመሥራትም እንጽና። ከክፉ ሥራም ሁሉ እንራቅ።
_አንቀጽ ፫_√
፩:- ሴት ለባሏ በትሕትና ትታዘዝ።
፳፰:- ክፉ ሴት ለራሷ ውርደትን ታመጣለች።
፴፪:- ያመኑ ሴቶች ራሳቸውን በንጽሕና ሊከናነቡ ይገባል። የፊታቸውን ውበት በማሳመርና ቀለም በመቀባት አይደለም። እግዚአብሔር በፈጠረው መልክ ውስጥ ጥቅም በሌለው ኩል መኳልና ማጌጥም አይደለም። እንዲህ ያለውን ሁሉ አይሥሩ። ነገር ግን እነርሱ ተከናንበው በጎዳና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይሂዱ።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፪ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው