Get Mystery Box with random crypto!

_የመበለት ዱላ_ መበለት ማለት አሮጊት ሴት ማለት ነው። የኔታ ቡሩክ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የነበሩ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_የመበለት ዱላ_
መበለት ማለት አሮጊት ሴት ማለት ነው። የኔታ ቡሩክ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የነበሩ የመጽሐፍና የቅኔ መምህር ነበሩ። እና አንድ ቀን "ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለ" ብለው ይናገራሉ። ይህን የሰሙ መበለቶች ዱላቸውን ይዘው የኔታን ሊደባደቡ ግርርርርር ይላሉ። ይህንን የተመለከቱ አንድ ሸምገል ያሉ ሰውየ "ቆይ እስኪ ከዱላው በፊት እንጠይቀው" ይሉና። ሄደው አንተን ብሎ መምህር ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለ ብለሃል አሉ እውነት ነው ይሏቸዋል። የኔታም "አዎ እውነት ነው ለእግዚአብሔርኮ የሚሳነው ነገር አለ" ብለው ይደግሙታል። የሰው ብስጭት ጨመረና "ምንድን ነው እግዚአብሔርን የሚሳነው?" ይሏቸዋል። የኔታም ሲመልሱ "ውሸት ነዋ" ብለው መለሱ። እግዚአብሔር ጻድቅነት የባሕርይው ነው ካልን ውሸት ይሳነዋል ማለት ነው ብለው ሲናገሩ ዱላ ይዞ የመጣው መበለት ሁሉ አፍሮ ወደየቤቱ ሄደ ብሎ አንድ የኔታን በቅርበት የሚያውቃቸው ሰው ነግሮኛል።

እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ ያለ ምሉዕ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ኃያል ነው ወዘተ ካልን ይህ የባሕርይው ስለሆነ አይለወጥም ማለት ነው። ምክንያቱም የባሕርይ ማለት የማይለወጥ የራስ የሆነ ነገር ማለት ነው። እግዚአብሔር አይለወጥም። እንደማይለወጥም በትን. ሚል. ፫፣፮ እንዲሁም መዝ. ፩፻፩፣፳፯ ተገልጿል። እግዚአብሔር ምሉዕነት የባሕርይው ከሆነ ምሉዕነቱን መተው አይችልም ማለት ነው። እግዚአብሔር ኃያልነት የባሕርይው ነው ካልን ኃያልነቱን አይተውም ማለት ነው። ነገረ ሥጋዌን ስንናገር እንኳ ቃል ቃልነቱን ሳይለቅ ሥጋን ሆነ ሥጋም ሥጋነቱን ሳይለቅ ቃልን ሆነ ነው የምንለው። ኃያሉ ኃያልነቱን ሳይለቅ ድኩም ሥጋን ተዋሐደ። የማይሞተው የማይሞትነትን ሳይለቅ የሚሞት ሥጋን ገንዘቡ አደረገ። ይህንም ተዐቅቦ በተዋሕዶ እንለዋለን። የአንድን ሰው ሐሳብ ምክንያቱን እና የሐሳቡን መነሻ ሳይረዱ በግምት መናገር አይገባም። ዱላን ከማንሳት መጠየቅ ይቀድማል። በተለይ ሴት ልጅ ጭምት ዝም ያለች በትሕትና የምትኖር መሆን አለባት። ፈጠን ፈጠን የምትል ቀባጣሪ መሆን የለባትም።