Get Mystery Box with random crypto!

__ቀኖና ዘቀሌምንጦስ ክፍል ፩__ ቀኖና ፩:- ሊቀ ጳጳሳት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤና ያለ ጳጳስ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ቀኖና ዘቀሌምንጦስ ክፍል ፩__
ቀኖና ፩:- ሊቀ ጳጳሳት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤና ያለ ጳጳስ መኖር አይሾምም።

ቀኖና ፪:- ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ እንዲሾም ያመጡት (የመረጡት) ሰው ሹመቱ የሚሰጠው በአገሩ ሰዎች ስምምነት ይሁን። የሚሾመው ጳጳስ ወይም ሊቀ ጳጳስ ይሁን። በሹመቱ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት መኖር አለባቸው። ቄስና ዲያቆንን እንዲሁም ከዚያ በታች ያሉትን ኤጲስ ቆጶሱ ብቻውን ይሹማቸው።

ቀኖና ፫:- በቁርባን ጊዜ ሕግ ተላልፎ በመሥዋዕቱ ላይ ማር ወይም ወተት ወይም በወይን ፋንታ ስኳር ወይም ጠጅ ያቀረበ ኤጲስ ቆጶስም ቢሆን ቄስም ቢሆን ዲያቆንም ቢሆን ከክህነቱ ይሻር። ንጹሕ ከሆነ ስንዴ ኅብስትና ከጠራ የወይን ፍሬ በስተቀር ከአዕዋፍም ቢሆን ከእንስሳትም ቢሆን ይህን ያደረገ ከሹመቱ ይሻር። ስንዴው ያልከረመና የመጀመሪያ ፍሬ የሆነ ይሁን። የወይኑ ፍሬም ያልቆየ ፍሬውን ውኃ የሞላውና የሚጣፍጥ ይሁን።

ቀኖና ፮:- ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የተመደበ ከዓለም ሥራ ምንም አይሥራ። እንደዚህ ቢሠራ ይሻር።

ቀኖና ፯:- ፋሲካን ከአይሁድ ፋሲካ ቀጥሎ ባለው ከእሑድ በስተቀር በአንድ ቀን ከእነርሱ ጋር ያደረገ ከሹመቱ ይሻር።

ቀኖና ፱:- በቅዳሴ ጊዜ ከምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን የገባ ሰው ቢኖር ቅዱሳት መጻሕፍትንም ቢሰማ ቅዳሴ እስከሚጨርሱ ድረስ ባይታገሥ ቁርባንም ባይቀበል ከቤተክርስቲያን ይውጣ። በሰማያዊ ንጉሥ ፊት መቆምን አቃሏልና።

ቀኖና ፲:- በውግዘት ምክንያት እንዳይቆርብ ከተከለከለና ከተባረረ ሰው ጋር የተነጋገረ ወይም በጸሎት የተሳተፈ ወይም ለምሳ ወደ ቤቱ የጠራው ሰው ቢኖር ይባረር።

ቀኖና ፲፪:- ካህኑን የሾመው ኤጲስ ቆጶስ ሳይፈቅድለት አገሩን ትቶ ወደሌላ ሀገር የሄደ ካህን ቢኖር እንደካህን ቆጥረው አይቀበሉት። ቢቀበሉት ግን የተቀበለውም ይባረር። እርሱም ይባረር።

ቀኖና ፲፯:- ካህን ድንግል ያልሆነችውን ቢያገባ በማናቸውም የክህነት መዓርግ ላይ ሊሾም አይገባም።

ቀኖና ፲፰:- የእኅቱን ልጅ ወይም የወንድሙን ልጅ ያገባ ካህን ቢኖር ከክህነት መዓርግ በየትኛውም ላይ ሊሾም አይገባውም።

ቀኖና ፳፫:- ራሱን የሰለበ ምእመን ቢኖር ለሦስት ዓመታት ከቤተክርስቲያን ይታገድ። ካህን ቢሆን ከሹመቱ ይሻር።

ቀኖና ፳፬:- ካህን ቢሰርቅ፣ በዝሙት ቢገኝ፣ በሐሰት ሲምል ቢገኝ ከክህነቱ ይሻር።

ቀኖና ፳፮:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን አንድን አማኝ ቢማታ ከመዓርጉ ይሻር።

ቀኖና ፳፯:- ባደረሰው በደል ምክንያት ወይም በትክክል በሥልጣነ ክህነት ከእርሱ በሚበልጠው ሰው ሥልጣኑ በመያዙ ከቤተክርስቲያን የተባረረ ኤጲስ ቆጶስም ቢሆን ዲያቆንም ቢሆን ይህ የሥልጣን መያዝና ግዝት ሳያግደው ያለፍርሀትና ያለመገረም በግድ አገልግሎቱን ቢቀጥል ውግዘቱን አቃሎም ቢያገለግል እስከ መጨረሻው ከቤተክርስቲያን ይወገድ።

ቀኖና ፴፪:- አንድ ኤጲስ ቆጶስ ከሩቅ ሀገር የመጡ ሌላ ኤጲስ ቆጶስን ወይም ቀሳውስትን ወይም ዲያቆናትን አይቀበል። ማንነቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ያለው ካልሆነ በስተቀር እንደ ካህናት አያድርጉት። ደብዳቤ ካላቸው ምግባራቸውን ይጠይቁ።

ቀኖና ፴፬:- ጳጳስ ባልተሾመበት ሀገረ ስብከት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን መሾም አይገባውም። ሕግ ከተላለፈና ያለዚያ ሀገረስብከት ሰዎች ፈቃድ እንደዚህ ካደረገ ይሻር። የሾማቸውም ይሻሩ።

ቀኖና ፴፭:- ኤጲስ ቆጶስ ከግማሽ በላይ ያሉ ምእመናን ከመረጡት ይሾም። ከዚህ በኋላ የሚቃወሙ ካህናት አይኑሩ። ካሉ ግን አልተስማሙምና ይሻሩ።

ቀኖና ፵፪:- ኤጲስ ቆጶስም ቢሆን ቄስም ቢሆን ዲያቆንም ቢሆን ከአበደረው ገንዘብ ወለድ የሚፈልግ ከሆነ ይህን ሥራውን ካልተወና ካልተመለሰ በስተቀር ከመዓርጉ ይሻር።

ቀኖና ፵፭:- ያለምክንያት ሚስቱን ከቤቱ ያስወጣት ወይም ሌላዋን በዝሙት የተፈታችውን ሴት ያገባ ሕዝባዊ ሰው ቢኖር ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።

ቀኖና ፵፮:- እግዚአብሔር የፈጠረው ጥሩ እንዳልሆነ የሚሳደብና የሚክድ ከእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ይሻር።

ቀኖና ፶:- ኤጲስ ቆጶስን የሰደበ ወይም የረገመ እንደ ሰነፍም የቆጠረ ከመዓርጉ ይሻር። እንደዚሁም ኤጲስ ቆጶስ ካህንን ቢረግም ወይም ቢሳደብ እርሱም ይሻር።

ቀኖና ፶፩:- ከካህናት ወገን ወይም ከምእመናን ቄስን ወይም ዲያቆንን የሰደበ ወይም የረገመ ቢኖር አስቀድመን እንደተናገርነው ይለይ።

ቀኖና ፶፪:- ከካህናት ወገን ወይም ከሕዝባውያን መስማት በተሳነው ሰው ላይ ወይም በዕውር ወይም በአንካሳ ወይም ድውይ ወይም ሽባ ላይ የተሳለቀ ወይም የሳቀ ሰው ቢኖር ይሻር።

ቀኖና ፶፫:- ኤጲስ ቆጶስ ሕዝቡን ባያስተምራቸው ይሻር።

ቀኖና ፶፬:- በአንድ አገር ላይ የተሾመ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ቢኖርና ከካህናት የተቸገረ ሰው አይቶ የሚፈልገውን ባይሰጠው ችግሩንም ባያስወግድለት በአጋጠመው ችግርም ባይረዳው ይሻር።

ቀኖና ፶፯:- ከካህናት ወገን ወይም ከሕዝባውያን አይሁድን ወይም አረመኔን በመፍራት የእግዚአብሔርን ሕግ የካደ የሕጉን ሥራም ያልገለጸ የክርስቶስን ስም ለመካድና ለመበደልም መርሕ የሆነ ከመዓርጉ ይሻር። ንስሓ ከገባ ግን ከምእመናን ወገን አድርገው ይቀበሉት።


ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
መ/ር በትረማርያም አበባው