Get Mystery Box with random crypto!

__ቀኖና ዘስምዖን ቀነናዊ__ ቁጥር ፫:- ኤጲስ ቆጶስ ይባርክ እንጂ አይባረክ። በሰዎች ራስ ላይ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ቀኖና ዘስምዖን ቀነናዊ__
ቁጥር ፫:- ኤጲስ ቆጶስ ይባርክ እንጂ አይባረክ። በሰዎች ራስ ላይ እጁን ይጫን። በእርሱ ላይ ግን ከሊቀ ጳጳሳት በስተቀር ማንም እጁን የሚጭን የለም።

ቁጥር ፬:- ቄስ ካህናትን አይሹም። ግን ቀሳውስትና መነኮሳት የገዳማት አስተዳዳሪዎች ከሆኑ ወደእነርሱ ለምንኩስና የመጣውን በገዳማቸው የፈለጉትን በአንድነት ያመንኩሱ።

ቁጥር ፭:- ሊቀ ጳጳሳት መሻር የሚገባቸውን ሁሉ ይሽራል። ሊቀ ጳጳሳትን ግን መሻር የሚቻለው እንደእርሱ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳትና የኤጲስ ቆጶሳት አንድነት ባሉበት ነው።

ቁጥር ፮:- ቄስ በዲያቆናትና ከእነርሱ በታች በሆኑ ሕዝባውያን ራስ ላይ እጁን ይጫን ይባርክም።

ቁጥር ፯:- ዲያቆን አይባርክም። በመዓርግ ከእርሱ በላይ ለሆኑት ደሙን ሊያቀብል አይችልም። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ዲያቆን ከእርሱ የሚያንሰውን ማዘዝ ይችላል። በመዓርግ ከእርሱ የሚበልጠውን ግን ማዘዝ አይችልም። ዲያቆን ቀድሞ ጸሎት ማስጀመር አይገባውም።

ቁጥር ፱:- በቤተክርስቲያን ካለው ሁሉ አራት እጁ ለኤጲስ ቆጶስ ነው። ሦስት እጁ ለቄስ፣ ሁለት እጁም ለዲያቆን ነው። ለሌሎች ሰዎች አንድ አንድ እጅ ነው።የእንስሳት በኩር ለካህናት ብቻ ይገባል

ቁጥር ፲:- በነጋ ጊዜ ምእመናንና ምእመናት ሳይታጠቡ ምንም ሥራ አይሥሩ። ከዚያም ራስን በማስገዛት ወደ ፈጣሪያቸው ይጸልዩ።

ቁጥር ፲፪-፲፬:- ሠራተኞች በየሳምንቱ ሁለት ቀን እንዲያርፉ አዘዝን። እነርሱም ቅዳሜና እሑድ ናቸው። ቤተክርስቲያንን ለማገልገልና እግዚአብሔርን ለመፍራት ለመዘከር ይገናኙባቸው። ቅዳሜ የምታርፉት እግዚአብሔር ያረፈባት ቀን ስለሆነች ነው። እሑድ የምታርፉት የዕለታት መጀመሪያ ስለሆነች ነው። በተጨማሪም የትንሣኤው ዕለት ስለሆነች ነው። በመጨረሻው ሰዓት ፍርድና ኩነኔ የሚሰጥባትም ዕለት ናት።

ቁጥር ፲፭:- ምእመናን በሰሙነ ሕማማትና በሰሙነ ትንሣኤ እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ ዕረፍት ያድርጉ። ሰሙነ ሕማማት ጌታ በሰውነቱ መከራ የተቀበለባትና የኀዘን ሳምንት ናትና። ሰሙነ ትንሣኤም የደስታ ሳምንት ነውና።

ቁጥር ፲፮-፳፫:- ምእመናን በዕርገት በዓል ይረፉ። በጰራቅሊጦስም ይረፉ። በዕለተ ብሥራትም (መጋቢት ፳፱) ይረፉ። በዕለተ ልደትም (ታኅሣሥ ፳፱) ይረፉ። በጥምቀት ዕለትም (ጥር ፲፩) ይረፉ። በዕለተ ስምዖንም (ግዝረተ ኢየሱስ) (የካቲት ፰) ይረፉ። በዕለተ ደብረ ታቦርም (ነሐሴ ፲፫) ይረፉ። በሐዋርያት የመታሰቢያ ቀንም ይረፉ። በእስጢፋኖስ በዓልም ይረፉ። በሌሎች ሰማዕታትና ቅዱሳን በዓልም ይረፉ።

ቁጥር ፳፭-፴፩:- የጸሎት ጊዜያት (ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት፣ ጸሎተ ሠለስቱ ሰዓት፣ ጸሎተ ነግህ፣ ጸሎተ ስድስቱ ሰዓት፣ ጸሎተ ተስዓቱ ሰዓት፣ ጸሎተ ሠርክ፣ ጸሎተ ምሴት፣ ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት)። ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት የምንጸልየው ጌታ ለመፍረድ ይመጣል ብለን ተስፋ ስለምናደርግ ነው። ጠዋት የምንጸልየው ጨለማውን አስወግዶ ብርሃኑን ስላመጣልን ነው። ሦስት ሰዓት የምንጸልየው በክርስቶስ ላይ ሞት ስለፈረዱበት ነው። ስድስት ሰዓት የምንጸልየው ጌታ ስለተሰቀለባት ነው። ዘጠኝ ሰዓት የምንጸልየው የጌታ ነፍስ ከሥጋው ስለተለየባት ነው። በሠርክ የምንጸልየው ዕረፍትን ስላመጣልን ነው። በመኝታ ሰዓት የምንጸልየው ከጨለማ ፍጥረታት እንዲጠብቀን ነው።

ቁጥር ፴፫:- ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ባይቻላቸው በኤጲስ ቆጶሱ ቤት ይሰብሰቡ። በኤጲስ ቆጶሱ ቤት መሰብሰብ ባይችሉ እያንዳንዱ በያለበት ይጸልይ። ወይም ሁለትም ሦስትም ሆነው ይጸልዩ። አማኝ ከማያምኑ ሰዎች ጋር በአንድ ቤት ይጸልይ ዘንድ አይገባውም።

ቁጥር ፴፭-፴፮:- ለሞቱ ሰዎች በሦስተኛው ቀን፣ በሰባተኛው ቀን፣ በሠላሳኛው ቀን፣ በዓመቱ መታሰቢያ ያድርጉላቸው። ለሙት ዓመቱ ዕጣን ያሳርጉለት፣ ከገንዘቡም ለድሆችና ለምስኪኖች ይመጽውቱለት። ለዓላውያን ለከኃድያን ግን ይህን ሊያደርጉላቸው አይገባም።

ቁጥር ፴፱:- ለቀደሙት አባቶቻችን መጽሐፍ ወይን እንዳይጠጡ አላዘዛቸውም። ነገር ግን ለመስከር ወይን አትጠጡ ይላል።

ቁጥር ፵፪:- በሃይማኖት ምክንያት ካሳደዷችሁ ወደሌላኛዋ ሀገር ሽሹ።

ቁጥር ፶፬:- ዲያቆን በእጁ ያቆርብና ያጠምቅ ዘንድ ሕዝብንም ይባርክ ዘንድ አይገባውም።

ቁጥር ፶፮:- ከእኛ ከሐዋርያት ሊቃነ ካህናት ሦስት ወገን ነን፣ ቀሳውስትም በልዩ ሦስት ወገን ናቸው፣ ዲያቆናትም ሦስት ወገን ናቸው እነዚህም ዲያቆናት ንፍቅ ዲያቆናትና አናጉንስጢስ ናቸው።

ቁጥር ፶፱-፷:- ቅዱስ እስጢፋኖስ እስከ ዕለተ ሞቱ በዲቁናው ጸንቷል። ፈጽሞ ቁርባን አላቆረበም። በማንም ላይ እጁን አልጫነም።

ቁጥር ፷፪:- ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን ያጠመቀው ፊልጶስና ጳውሎስን ያጠመቀው ሐናንያ ክህነትን ከሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለው አጠመቁ።

ቁጥር ፷፮:- ጋኔን ላደረበት ሰው ጋኔኑ እስኪተወው ድረስ ቁርባን አያቁርቡት። ለሞት የሚደርስ ከሆነ ግን ይቀበሉት። ቁርባንም ያቁርቡት።

ቁጥር ፷፰:- ሴት ዘማዊት ብትሆን የዝሙት ሥራን ትተው። እምቢ ካለች ከእኛ ትባረር።

ቁጥር ፷፱-፸:- ወንድ ወይም ሴት ወደ ሕጋችን መግባት ቢፈልጉ ሰካራም ወይም ጣዖት አምላኪ፣ ተዋናይ ወይም ዘፋኝ፣ ወይም ዘፈን የሚያስተምር፣ ወይም ወደዝሙት የሚገፋፋ ቢሆን ሥራውን ይተው። እምቢ ካሉ ግን ከማኅበራችን ወጥተው ይባረሩ።

ቁጥር ፸፩:- ወታደር ከዝርፊያ፣ ከቅሚያና ከበደል ይራቅ። በሚሰጡት ደመዎዝ ይኑር። ከዝርፊያ ከቅሚያ ከበደል ካልራቀ ግን ይባረር።

ቁጥር ፸፯:- ወደ ዘፈንና ወደ ዳንኪራ በጭፈራ ቤትም ወደሚደረገው ፉከራ ወይም ወደሚገዳደሉበት የሚሄድ ካለ ይመለስ። ሥራውንም ይተው የአረመኔ ሥራ ነውና። እምቢ ካለ ይለይ።

ቁጥር ፸፰:- ለሰው መልካም ነገርን የሚያስተምር ሕዝባዊ ቢኖር በቃሉ ጭምት ይሁን። በሥጋው ደግ ይሁን። አይኩራራ። አንደበተ ርቱዕ ይሁን። ከዚያ በኋላ ሰውን ያስተምር።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
መ/ር በትረማርያም አበባው