Get Mystery Box with random crypto!

__ቀኖና ቀሌምንጦስ ክፍል ፪_ ቀኖና ፶፰:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ወይም ከካህናት | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ቀኖና ቀሌምንጦስ ክፍል ፪_
ቀኖና ፶፰:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ወይም ከካህናት ሌላው ያልታረደ ሥጋ የበላ፣ ወይም ተኩላ የነከሰው ወይም በክት ወይም ሌላ የሞተ ነገር የበላ ከሹመቱ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነም ይባረር።

ቀኖና ፶፱:- ከቀዳም ስዑር ውጭ ቅዳሜ እና እሑድ ሲጾም የተገኘ ካህን ከሹመቱ ይሻር። ሕዝባዊ ቢሆን ከቁርባን ይከልከል።

ቀኖና ፷፩:- ከሌላ ሰው ጋር የተጣላ ካህን ቢኖር ቢመታውና ቢሞትበት ከሹመቱ ይሻር። ሕዝባዊ ቢሆን ደግሞ ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።

ቀኖና ፷፫:- ዳግመኛ የተሾመ ካህን ካለ ከሹመቱ ይሻር። የሾመውም ይሻር። [ቀድሞ የተሾመው ከከኃድያን ከሆነ ግን ያ ስለማይቆጠር ሁለተኛ ነው አይባልም]።

ቀኖና ፷፬:- ከአይሁድ በበዓላቸው ቂጣና የመሳሰሉ ስጦታዎችን የሚቀበል ካህን ከሹመቱ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ከሕዝብ ይለይ።

ቀኖና ፷፮:- ከካህናት ወይም ከምእመናን ለአይሁድ ምኩራብ ወይም ለአማልክት መስገጃ ቦታ ወይም ለጠንቋዮች ወይም ለከኃድያን አብያተ ክርስቲያን የሚያበሩት ዘይት ወይም መብራት ቢልክ ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።

ቀኖና ፷፰:- ከተቀደሰ ልብስ ጀምሮ ሁሉም የቤተክርስቲያን ሀብት ወይም የብር ገንዘብ ሰው በቤቱ ሊሠራባቸው አይገባም።

ቀኖና ፸፩:- ኤጲስ ቆጶስ ክህነትን መውረስ ወይም ማውረስ አይገባውም።

ቀኖና ፸፰:- ወታደር ሆኖ የቤተክርስቲያን ሹም ለመሆን የሚፈልግ ካህን ካለ ይሻር።

ቀኖና ፸፱:- ከመሳፍንት አንዱ በፍርድ ሳይገፋው ያለ አግባብ ንጉሥን የሰደበ ወይም የረገመ ካህን ከሆነ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ይባረር።

ቀኖና ፹:- ለቀሌምንጦስ የነገርነው ፹፩ መጽሐፍ ነው። እነዚህም:-
፩) ኦሪት ዘፍጥረት
፪) ኦሪት ዘጸአት
፫) ኦሪት ዘሌዋውያን
፬) ኦሪት ዘኍልቍ
፭) ኦሪት ዘዳግም
፮) መጽሐፈ ኢያሱ
፯) መጽሐፈ መሳፍንት
፰) መጽሐፈ ሩት
፱) መጽሐፈ ዮዲት
፲) መጽሐፈ ጦቢት
፲፩) መጽሐፈ አስቴር
፲፪) መጽሐፈ መቃብያን (፫)
፲፫) መዝሙረ ዳዊት
፲፬) መጻሕፍተ ሰሎሞን (፭)
፲፭) መጻሕፍተ ነገሥት (፬)
፲፮) መጽሐፈ ሲራክ
፲፯) መጽሐፈ ኢዮብ
፲፰) መጽሐፈ ዕዝራ (፫)
፲፱) ትንቢተ ኢሳይያስ
፳) ትንቢተ ኤርምያስ
፳፩) ትንቢተ ሕዝቅኤል
፳፪) ትንቢተ ዳንኤል
፳፫) ትንቢተ አሞጽ
፳፬) ትንቢተ ዮናስ
፳፭) ትንቢተ ዕንባቆም
፳፮) ዖዝያ (ትንቢተ ሆሴዕ?)
፳፯) ትንቢተ ናሆም
፳፰) ትንቢተ ሶፎንያስ
፳፱) ትንቢተ ዘካርያስ
፴) ትንቢተ ሚኪያስ
፴፩) ትንቢተ ሚልክያስ
፴፪) ወንጌል (፬)
፴፫) መልእክታተ ሐዋርያት (፯)
፴፬) የጳውሎስ መልእክታት (፲፬)
፴፭) የሐዋርያር ሥራ
፴፮) ራእየ ዮሐንስ
፴፯) መጽሐፈ ቀሌምንጦስ
ቀኖና ፹፩:- እንድትቀበሏቸው በቀሌምንጦስ እጅ ያዘዝናችሁ መጻሕፍት 8 የቀኖና መጻሕፍት ናቸው።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
መ/ር በትረማርያም አበባው