Get Mystery Box with random crypto!

__የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፭__ #ትእዛዝ #ሲኖዶስ ትእዛዝ ፵፪:- ከ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፭__
#ትእዛዝ #ሲኖዶስ
ትእዛዝ ፵፪:- ከካህናት መካከል ከኃድያንን ከመፍራት የተነሣ ቢክድ የካደው የክርስቶስን ስም ከሆነ ይባረር። የካደው ክህነትን ከሆነ ይሻር። ንስሓ ከገባ ይቀበሉት እንደ ሕዝብ ሆኖም ይግባ።

ትእዛዝ ፵፫:- ከካህናት አንዱ ደም ያለው ወይም ያልታረደ ወይም አውሬ የነከሰው ወይም በክት ከበላ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነም ይለይ።

ትእዛዝ ፵፬:- ከቀዳም ስዑር በስተቀር በሰንበትና በዕለተ እሑድ ከካህናት መካከል አንዱ ሲጾም ቢገኝ ይሻር።

ትእዛዝ ፵፭:- ከካህናት መካከል በከኃድያን ቦታ ይጸልይ ዘንድ ቢገባ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነም ይባረር።

ትእዛዝ ፵፮:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ሁለት ጊዜ ተሹሞ ቢገኝ እርሱም የሾመውም ይሻር።

ትእዛዝ ፵፯:- ደዌ ሕመም ካልከለከለው በስተቀር ጾመ አርብዓን፣ ረቡዕና ዓርብን የማይጾም ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ወይም አናጉንስጢስ ወይም መዘምር ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ደግሞ ይባረር።

ትእዛዝ ፵፰:- ከካህናት አንዱ ከአይሁድ ጋር ቢጾም ወይም ፋሲካን ከእነርሱ ጋር ቢያደርግ ወይም ለበዓላቸው ስጦታ ቂጣ ቢቀበል ወይም ይህን የመሰለ ቢያደርግ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ይባረር። ሕዝባዊ ሆኖ ዘይትና መብራት ወደ አይሁድ ምኵራብና ወደ አሕዛብ ምኵራብ ቢወስድ ከምእመንነቱ ይሻር።

ትእዛዝ ፵፱:- የተሾመ ካህን ከቤተክርስቲያን ሠም ወይም ቅባት ቢሰርቅ ይባረር። የሰረቀውንም አምስት እጥፍ አድርጎ ይክፈል።

ትእዛዝ ፶፩:- በኤጲስ ቆጶስ ላይ የከኃድያንን ምስክርነትና የአንድን ኤጲስ ቆጶስ ምስክርነት አይስሙበት። ኤጲስ ቆጶስነትን ይዋረሱ ዘንድ ትክክል አይደለም። ኤጲስ ቆጶስ የቤተክርስቲያንን ሀብት ለፈለገው ሰው አይስጥ። አንድ ዓይኑ የታወረ ወይም አንድ እግሩ አንካሳ የሆነ ሰው ኤጲስ ቆጶስነት የሚገባው ቢሆን ይሾም። ነውረ ነፍስ እንጂ ነውረ ሥጋ አያረክስምና። መስማት የተሳነውና ዐይነ ስውር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አይሾም።

ትእዛዝ ፶፪:- ጋኔን ያደረበት ካህን ሆኖ አይሾም። ከምእመናን ጋርም አብሮ አይጸልይ።ጌቶቹ እንዳያዝኑ ነጻ ያልወጣ ሰው ካህን ሆኖ ይሾም ዘንድ አናዝም።

ትእዛዝ ፶፫:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ዓለማዊ ሹመትንና ክህነትን ሁለቱን ለመሥራት ወታደር ሆኖ ማገልገል ቢፈልግ ይሻር። [መንግሥትነት] ንጉሥን ወይም መኮንንን የሚያቃልል ይበቀሉት። ካህን ከሆነ ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ደግሞ ይባረር።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፮ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው