__የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፬__ #ትእዛዝ #ሲኖዶስ ትእዛዝ ፳:- ኤጲስ ቆጶ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw
__የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፬__
#ትእዛዝ #ሲኖዶስ
ትእዛዝ ፳:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን መማለጃ በመስጠት የሹመት መዓርግ ቢይዝ ይሻር። የሾመውም ይሻር። ከክህነት ሥርዓትም እስከ መጨረሻው ይባረር።
•
ትእዛዝ ፳፩:- ኤጲስ ቆጶስ ቤተክርስቲያንን በዚህ ዓለም የአገዛዝ ሥርዓት ለመግዛት የሚፈልግን ሰው ከረዳ ይሻር።
•
ትእዛዝ ፳፪:- ቄስ ኤጲስ ቆጶስን ቢንቅ ይለይ።
•
ትእዛዝ ፳፫:- ኤጲስ ቆጶስ ያባረረውን ቄስ ወይም ዲያቆን ራሱ ካልፈቀደ በስተቀር ሌላ ኤጲስ ቆጶስ እንዲመለስ አያድርገው።
•
ትእዛዝ ፳፬:- ሊቀ ጳጳሳት የሁሉንም ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶሳት ያውቅ ዘንድ ይገባል።
•
ትእዛዝ ፳፭:- ኤጲስ ቆጶስ የሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶስ ካልፈቀደለት የእርሱ ባልሆነ ሀገረ ስብከት ላይ ለመሾም አይደፋፈር። ተደፋፍሮ የተገኘ ካለ እርሱም የሾማቸውም ይሻሩ።
•
ትእዛዝ ፳፯:- የኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይደረግ። በቤተክርስቲያን ላይ ስለአለ ስሕተትና እንቅፋት ስለሚሆኑ ነገሮችም ይተርጕሙ። የመጀመሪያው ጉባኤ በበዓለ ኃምሳ መካከል ይሁን። ሁለተኛው ጉባኤ ጥቅምት 12 ይሁን።
•
ትእዛዝ ፳፰:- ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔርን ገንዘብ ለዘመዱ ልጆች መስጠት የለበትም።
•
ትእዛዝ ፳፱:- ከቀሳውስት ወይም ከዲያቆናት ማንም ኤጲስ ቆጶሱን ሳያማክር ምንም አያድርግ።
•
ትእዛዝ ፴፩ [የጦር ሠራዊት]:- የንጉሥ ሠራዊትም ከጠላት ጋር ጦርነት የሚያደርጉት በራሳቸው ምግብ አይደለም።
•
ትእዛዝ ፴፪:- ወደ ጭፈራ ቤት የሚሔድና የሚዞር ስካርም የሚያበዛ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ይተው። አልተውም ካለ ግን ይባረር። ሕዝባውያንም ቢሆኑ እንደዚሁ ይሁኑ።
•
ትእዛዝ ፴፫:- ወደ ከኃድያን ጥምቀት ወይም ወደ ቁርባናቸው የሚሔድ ካህን ይሻር።
•
ትእዛዝ ፴፬:- ሥጋ መብላት፣ ጋብቻ፣ ወይን መጠጣት እንደ ርኩስ የሚቆጥር ቢኖር ይህን ሐሳቡን ይተው ዘንድ ይንገሩት። ካልተወ ግን ይሻር። ሕዝባዊ ቢሆንም እንዲሁ ይደረግ።
•
ትእዛዝ ፴፭:- ከኃጢአት ንስሓ የሚገቡትን አልቀበልም የሚል ካህን ቢኖር ይሻር።
•
ትእዛዝ ፴፯:- ከካህናት መካከል በገበያ የሚበላ ወይም የሚጠጣ ቢገኝ ከካህናት አንድነት ይለይ። ከካህናት መካከል አንዱ ኤጲስ ቆጶስን ቢሳደብ ይሻር። በሕዝብ ላይ በተሾመ ሰው ላይ መጥፎ ቃል አትናገር ይላልና። ቄስን ዲያቆንን የሚሳደብም ይባረር።
•
ትእዛዝ ፴፰:- ካህናትን ወይም ሕዝብን የሚንቅና የእግዚአብሔርን መልእክት የማያስተምር ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ይባረር። በንቀቱ ቢቀጥልበት ይሻር።
•
ትእዛዝ ፴፱:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ከካህናት የተቸገረን አይቶ ቸል ቸል ካለ የሚፈልገውን ነገርም ባይሰጠው ይለይ። በዚሁ በቸልታው ከቀጠለም ወንድሙን እንደገደለ ይቆጠራልና ይሻር።
•
ትእዛዝ ፵:- ከኃድያን በውሸት የጻፉትን መጽሐፍ ያሳየ ሕዝብንና ካህናትንም ለማጥመድ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቆጥሮ ወደ ቤተክርስቲያን ያስገባ ሰው ቢኖር ይሻር።
•
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፭ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው