Get Mystery Box with random crypto!

_የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፪_ #ግጽው ትእዛዝ ፲፫ ሕግና ሥርዓትን የማያው | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፪_
#ግጽው
ትእዛዝ ፲፫ ሕግና ሥርዓትን የማያውቅ ሰው በምእመናን ላይ አይሾም። በምእመናን ላይ ሊሾም የሚገባው በጠባዩ ቸር፣ ታጋሽ፣ በጉዞው ሁሉ ጥሩና ትሑት ይሁን። ይህን ካላደረገ ይሻር። ቃሉንና ትእዛዙንም አይቀበሉት። በአሠራሩ ታማኝ አይደለምና።

ትእዛዝ ፲፬:- ሐሰተኛን እና ሐሜተኛን ሰው ከሹመት ይከልክሉት።

ትእዛዝ ፲፭:- በኮከብ ቆጠራ የሚታመንና በጥንቆላ የሚያምን ሁሉ ከሹመት ይወገድ። ክርስቲያኖችን እግዚአብሔርን ከማያውቁት ጋር የሚያስተካክል ከክህነት ሥልጣን ይሻር።

ትእዛዝ ፲፯:- በዝሙትና በስስት የሚታወቅ እንዲሁም የዚህን ዓለም ጥቅም የሚፈልግ ቄስም ሆነ ዲያቆን ከሹመቱ ይሻር።

ትእዛዝ ፳:- የዚህን ዓለም ሥራ የሚሠራን ሰው በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ላይ እንዲያዝዝ ሹም አያድርጉት። ጸሎት የያዘ ቄስም ሆነ ዲያቆን ጸሎቱን አቋርጦ ወደሌላ ነገር አይሂድ። እንደዚህ የሚያደርግ ከሆነ ወደቀድሞ ቦታው መመለስ አይሆንለትም (አይገባውም)።

ትእዛዝ ፳፩:- ለቅዱሳን ሰማዕታት በሞቱበት ቀን መታሰቢያ ያድርጉላቸው።

ትእዛዝ ፳፩:- መዝሙረ ዳዊትን ቀንም ሌሊትም ይጸልዩት። መዝሙረ ዳዊት ተአምኖ ኃጣውእ፣ ጸሎት፣ ምስጋና አለበትና። ችግር፣ ሐዘንና፣ መከራ በአጋጠማቸው ጊዜ ከጥፋት ያመልጡ ዘንድ ይጸልዩ።

ትእዛዝ ፳፫:- በቤተመቅደስ ለማገልገል ከሕዝብ የተመረጡ ካህናት ሰባት ይሁኑ።

ትእዛዝ ፳፬:- ዐመፀኛውን ጻድቅ የሚያደርግ፣ ንጹሑን የሚያበሳጭ የተወገዘና ርጉም ይሁን። እንደዚህ የሚያደርገውን ከሹመቱ ይከልክሉት። ስለዐመፀኛነቱም ይመስክሩበት። ዐመፀኛ ከሆነ ጵጵስናው አያስፈራህ። (በእንተ ዐመፃሁ ወኢያፍርህከ ጵጵስናሁ)።

ትእዛዝ ፳፭:- በሰዎች ላይ የሚኩራራና በራሱ የሚታበይ ወደ ሹመት አይቅረብ። ከሌሎች ሰዎች እንደሚበልጥ እንደሚከብርና እንደሚሻል ራሱን የሚያይ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በንቀት ዓይን የሚመለከት በሹመት ላይ አይቀመጥ።

ትእዛዝ ፳፮:- በየአውራጃው ባሉ ቀሳውስት ላይ በመካከላቸው ሆኖ የሚያዛቸውና የሚገሥጻቸው ሊቀ ካህናት ይሹሙ።

ትእዛዝ ፳፯:- በጸሎት ጊዜ ንጉሥ በሰው ሁሉ ፊት ከምእመናን ጋር ይሁን። ለቁርባን ወደ መሠውያው ቦታ ይግባ። መቆሚያውም ከሊቃውንትና ከተሾሙ ካህናት ጋር በዚያ ይሁን።

ትእዛዝ ፴:- ቁርባንን በዕለቱ ያቀብሉት እንጂ ለነገ አያሳድሩ።

ሊቃነ ካህናቱ ኒቆዲሞስና ገማልኤል፣ ሐና፣ ቀያፋ፣ ሊቃነ ካህናት ሌሊት ወደክርስቶስ ይመጡ ነበር። በክርስቶስም ያምኑ ነበር። ነገር ግን አይሁድን ፈርተው ይህንን አልገለጹም። ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ሁላቸውም አምነዋል።

የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት እርስ በእርሳቸው ይተባበራሉ።

ሐዋርያት ከጠንቋዮች ጋር ይጋደሉ ነበር። ስለ ሃይማኖታቸው ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ እኛም የፈጠረንን አስቆጥተነዋልና ይህች የደረሰችብን ችግር ታስታርቀናለች ይሉ ነበር። ከእነርሱ መካከል ብዙ ጊዜ ንብረቱ የተዘረፈበት አለ፣ ከገንዘቡ ከልጆቹና ከቤቱ የራቀም አለ፣ የሰቀሉትም አለ። እስኪሞቱ ድረስ በፈቃዳቸው ይታገሡ ነበር።

ምእመናን ለአማልክት የተሠዋንና በክት የሆነውን ከመብላት፣ ደምን ከመጠጣት፣ ለባዕድ አምላክም ከመሳል እንዲታቀቡ ያዝዟቸው ነበር።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፫
መ/ር በትረማርያም አበባው