Get Mystery Box with random crypto!

ተግሣጽ & ስድብ በአንድ ወቅት በአንድ ቤት ብዙ ሰዎች ተኝተው ሳለ አንዱ ፈርቶ ሌሎች የተኙ ሰዎች | በትረማርያም አበባው

ተግሣጽ & ስድብ
ንድ ወቅት በአንድ ቤት ብዙ ሰዎች ተኝተው ሳለ አንዱ ፈርቶ ሌሎች የተኙ ሰዎች ሳይሰሙ ከዚያው ከቤት ይጸዳዳል። በኋላ ሲያስበው ሰው ሊስቅበት ነው። ከዚያ ሰገራውን በእጁ ይዞ የሁሉንም ልብስ እንደተኙ ይቀባዋል። እርሱም እጁን አባብሶ መልሶ ይተኛል። እነዚያ የተኙት ሰዎች በኋላ ነቅተው ወደ ውጭ ወጣ ብለው ሳሉ ልብሳቸውን ቢያዩት ሰገራ በሰገራ ሆኗል። ሰው እንዳይስቅብን ብለው እነርሱ እንዳላደረጉት እያወቁ ጠፍተው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ይባላል። ያ አራም ግን በሰላም ከቤት ተኝቶ አደረ ይባላል።

አሁን እየሆነ ያለው ነገር ይህን ይመስላል። አራሞች በሰላም እየኖሩ ንጹሓን የሚሸማቀቁበት ክፉ ዘመን ነው። ነውረኞች ተወደው በሰላም እየኖሩ ነውረኞች ነውራቸውን የቀቧቸው ንጹሓን ሰዎች እየተሰደቡ ይኖራሉ። ምሁራን ዝም ብለው ተሳዳቢዎች ተናጋሪ የሆኑበት ዘመን ነው። ስድብና ተግሣጽ ይለያያል። ገሠጸ ተቆጣ፣ መታ፣ ደበደበ፣ አስተማረ ከሚለው የግእዝ ቃል ተግሣጽ የሚል ባዕድ ዘር ይወጣል። ትርጉሙ ቁጣ፣ ትምህርት ማለት ነው። መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ በሚልበት ጊዜ መገሥጽ የሚያስተምር ተብሎ ይተረጎማል እንጂ የሚሳደብ ተብሎ አይተረጎምም። ስድብ ጸዐለ ሰደበ ከሚለው የግእዝ ቃል የሚወጣ ሲሆን "ጽዕለት" መስደብ፣ መሰደብ ስድብ ይላል። ለምሳሌ ሕፃናትን መገሠጽ ይገባል ሲባል ትምህርት ሲገድፉ እና አልማር ሲሉ መቆጣት ይገባል ማለት ነው። እየቀጡ እየመቱ ማረም ይገባል ማለት ነው። ስንማታ ግን ሕይወታቸው እንዳያልፍብን ባለፈው በፍትሐ ነገሥት እንደተማርነው የምንማታበትን ኃይል በራሳችን ጉልበት ፈትነን አማትበን ሊሆን ይገባል። የሞት ብዙ ምክንያት አለውና ተብሎ ተገልጿል።

የተግሣጽ ትርጓሜ ይህ ነው። ከዚያ ውጭ ጥርግርግ እያደረጉ እየተሳደቡ ያሉ ሰዎችን መምህር ወመገሥጽ ማለት ትልቅ ነውር ነው። ንስሓ እንዳይገቡም መሰናክል መሆን ነው። እየተሳደበ የሚያስተምር ሰው መምህር ወመገሥጽ ሳይሆን መምህር ወመጽዕል ነው የሚባለው። ለቤተክርስቲያን ትልቅ ሸክም እየሆኑ ያሉት እነዚህ ናቸው። እናርማለን ይላሉ። ነገር ግን እነርሱ ተሳስተው ስታርማቸው ተሳዳቢ መንጋቸውን ይለቁብሃል። ደግሞ መንጋን መፍራት ተገቢ አይደለም። ማንኛውም መምህር በቀዳሚነት ሊፈራው የሚገባው እግዚአብሔርን ነው። ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ዳኝነት በመላእክትና በሰው ሁሉ ፊት ይቀርባል። ይህንን ነው ማሰብ። በክፉዎች መሰደብ ለመምህራን ክብር ነው። ከታገሡት ሐዋርያዊ ክብርን ያሰጣቸዋልና።

ስለዚህ ተሳዳቢነትን እንተው። ተምረን እናስተምር። ሳይማሩ ማስተማር ጥፋት ይኖረዋልና። ከተሳሳትን ይቅርታ እንጠይቅ። ሰው አምላኪ አንሁን። የሰውን መልካምነቱን ብቻ እንውሰድ። ክፉ ነገሩን አብነት ማድረግ አይገባም።

በትረማርያም አበባው