Get Mystery Box with random crypto!

__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳__ አንቀጽ ፳፰ ስለውሰት ይናገራል። ፩) ውሰት በታወቀ ዕለት በታወቀ ቦ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳__
አንቀጽ ፳፰ ስለውሰት ይናገራል።
፩) ውሰት በታወቀ ዕለት በታወቀ ቦታ ዋጋ ሳይሰጡ ወይም ሳይቀበሉ ጥቅም የሚገኝበትን ገንዘብ መዋስ ነው። አንድም ማዋስ ነው።
_
፪) እስከዚህ ቦታ ብሎ ከብት የተዋሰ ሰው ቢኖርና ከቦታው አልፎ ሄዶ ከብቱ ቢሞት መክፈል ይገባዋል። ቦታውን አልፎ ሳይሄድ ነገር ግን በራሱ ቸልተኝነት ከሞተበትም መክፈል ይገባዋል። ከገደል አፋፍ ሆና ስትበላ አይቶ ዝም ቢልና ብትሞትም ይከፍላል። ጌታው አብሮ ካለ ግን አይከፍልም።
_
፫) በዋጋ የተዋሰ ከብት ቢኖርና ቢጠፋ የተዋሰው ዋጋውን ይከፍላል። ከተወሰነው ቦታ አልፎ የሄደ ቢሆን ላዋሰው ሰው አልፎ የሄደበትን ጨምሮ ይስጥ።
_
፬) ያዋሰ ሰው በወደደው ጊዜ መልስልኝ ማለት ይገባዋል። የተዋሰ ሰውም እንዲሁ በወደደው ጊዜ መመለስ ይገባዋል።

አንቀጽ ፳፱
ይህ አንቀጽ ስለ አደራ ይናገራል።
፩) አደራ ጠባቂ ለአስጠባቂ የሚሰጣት ገንዘብ ናት። ይህችውም አስጠባቂ ከጠባቂ ዘንድ አምኖ የሚያኖራት ገንዘብ ናት። የተቀበላትም ሰው እንደገንዘቡ አድርጎ በፍጹም ትጋት መጠበቅ ይገባዋል። ተግቶ እየጠበቃት ብትጠፋ ዕዳ የለበትም።
_
፪) አደራ አስጠባቂው ብዙ ዘመን ኖሮ ቢጠፋ አደራ ጠባቂው ለአደራ አስጠባቂው ወራሾች አደራውን ይስጥ። ወራሾች ባይኖሩት ለመሥዋዕት ይሁን።
_
፫) የሰው አደራ የተቀበለ ሰው ለእገሌ ስጥልኝ ቢለው ስጥልኝ ላለው መስጠት ይገባዋል።
_
፬) አደራ ጠብቆ መመለስ ለለመደ ነው እንጂ ላልለመደ መስጠት አይገባም። አደራ ያኖሩበት ሰው ቢሞት አደራ ይቀራል።
_
፭) አደራ የተቀበለ ሰው ጠባቂ አስጠባቂ በኃይል ሰርቆ ቀምቶ እንዳመጣው እያወቀ አደራ ቢያኖር እጥፍ ሊያስከፍሉት ይገባል። የሌባ ዋሻ የቀማኛ ጋሻ ሆኗልና።

አንቀጽ ፴
ይህ አንቀጽ ስለሹመት ይናገራል።
፩) ግብሩን ጠባዩን ያሳመረ ሰው፣ የሹመትን ሥርዓቷን ያወቀ የጠነቀቀ መሾም ይገባዋል። ለጌታው ገንዘብ ከፍሎ ይሾማል።
_
፪) የጌታው ገንዘብ ያለተንኮል ያለስንፍና በሹሙ እጅ ቢጠፋ መክፈል አይገባውም።
_
፫) ሿሚና ተሿሚው ምስክር የሌለው ጠብ ቢጣሉ ሿሚው ምሎ በተናገረው ይሁን። በገንዘቡ አምኖ ሹሞታልና።
_
፬) ሹም በተሾመበት ገንዘብ እንደራሴ መሾም አይገባውም። ጌታው ሹም ብሎ ቢፈቅድለት ነው እንጂ።
_
አንቀጽ ፴፪
ይህም የሹመትን ነገር ይናገራል። ከአንቀጽ ፴ የሚለየው ይህ አንቀጽ ፴፪ የሐፃኒ የመጋቢ ነው። አንቀጽ ፴ የቤተ መንግሥት ነው።
፩) ለሽማግሌ፣ ለሕፃን፣ ለእብድ፣ ለታማሚ ጽኑ ሹም ሊሾሙላቸው ይገባል።
_
፪) አገልጋይ በጌታው ትእዛዝ ማዘዝ መሠልጠን ይገባዋል። ተሿሚዎች ገንዘብ ቢያጠፉ መክፈል ይገባቸዋል። [ሐተታ:- ጥንቱን መሾማቸው ሊጠብቁ ነውና]።
_
አንቀጽ ፴፩
ይህ አንቀጽ አገልጋይ ስለመግዛትና አገልጋይን ነጻ ስለማውጣት ይናገራል።
፩) ሰው ሁሉ ከአንድ ከአዳም በመገኘት ባለመገዛት አንድ ነው። ነገር ግን ጦርነትና ሌሎችም ምክንያቶች አንዱ ለአንዱ ይገዛ ዘንድ መገዛትን ታመጣባቸዋለች። ድል የተነሡት ድል ለነሡት እንዲገዙ ታደርጋለች
_
፪) አማኒ አገልጋይን ላላመነ ሰው መሸጥ አይገባም። የአገልጋይ ልጆች ለጌታቸው ይገዙ። አንድም ለአባታቸው ጌታ ይገዙ።
_
፫) አገልጋይን ነፃ ማውጣት ከትሩፋት ሥራ ወገን ናት። አገልጋይን ሁሉ ነጻ ማውጣት ይገባል።
_
፬) አገልጋይ በሚከተሉት ምክንያቶች ነጻ ሊወጣ ይችላል።
√ ከጌታው ዘመድ አንዱ ቀድሞ ገዝቶት ከነበረ፣
√ ጌታው ክርስትና ቢያነሣው፣
√ በጌታው ፈቃድ ክህነት ከተሾመ፣ ከመነኮሰ
√ ጌታው ፈቅዶ ባርያው ዘማች ከሆነ/ከዘመተ
√ ጌታውን ከሞት ቢያድነው (ተዋግቶ/መክሮ)
√ ጌታው ቢሞት
√ አገልጋዩ በጠላቱ እጅ ከተያዘ በኋላ ከድቶ ወደ ጌታው ቢመለስ ነጻ መውጣት ይገባዋል።
_
፭) ነጻ የወጣች አገልጋይ ነጻ ያልወጣውን አገልጋይ ማግባት አይገባትም።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፳፩ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው