Get Mystery Box with random crypto!

በቀድሞ ዘመን የላይ ቤትና የታች ቤት መተርጉማን በምሳሌ ምክንያት አይግባቡም ነበር ይባላል። ወንጌ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

በቀድሞ ዘመን የላይ ቤትና የታች ቤት መተርጉማን በምሳሌ ምክንያት አይግባቡም ነበር ይባላል። ወንጌላውያን ለምን አራት ሆኑ ለሚለው ሐተታ ሲሰጡ አራት ወቅት፣ አራት ኪሩቤል፣ አራት ባሕርያት____ እያሉ ከሰጡ በኋላ አራትነት ያለውን ነገር ሁሉ ካልመሰልን ይላሉ። ይህን የተመለከተ አንድ ሊቅ ወደ ቤቱ ሲገባ ከግርግሙ ላይ አራት አሞሌ ጨው ተሰቅሎ ያያል። እና ሚስቱን ጠርቶ "እኒያ ሰዎች የአራቱ ወንጌላውያን ምሳሌ እንዳያደርጉት ደብቂው" አሉ ይባላል። ምሳሌ ሲሰጥ መጽሐፍን ሳይለቁ ነው። እንጂ ጥቂት መመሳሰል ያለውን ነገር ሁሉ ምሳሌ ካላደረግነው አይባልም።

ሊቃውንት አባቶቻችን ምሥጢረ ሥላሴን በፀሐይ ሲመስሉ በውስተ ፀሐይ ሤመ ጽላሎቶ የሚለውን የመዝሙረ ዳዊት ክፍል አብነት አድርገው ነው። ጽላሎት የአካል ምሳሌ ነውና። ሰውን የምሥጢረ ሥጋዌ ምሳሌ ያደረጉት ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ የሚለውን የኦሪት ዘልደት ቃል መሠረት አድርገው ነው። አርአያ በቁሙ ምሳሌ ነውና። ምሥጢረ ሥላሴን በእሳት ሲመስሉት በቀሌምንጦስ አቡየ እሳት ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስቅዱስ ዋዕዩ የሚለውን ኃይለ ቃል መሠረት አድርገው ነው። ምሳሌያትን ሁሉ ብንመለከት መጽሐፋዊ መሠረት ያላቸው ናቸው። ስለዚህ ከአበው ትምህርት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት ባንወጣ መልካም ነው።

አንዱ ምሳሌ ለሁለት ተቃራኒ ነገሮች የሚመሰልበት ወቅትም አለ። ምሳሌ ኮከብ የቅዱሳን ምሳሌም ይሆናል። ለአብርሃም አበዝኆ ለዘርዕከ ከመ ኮከበ ሰማይ ወከመ ኆፃ ዘድንጋገ ባሕር ሲል ኮከብ የቅዱሳን ኆፃ የኀጥአን ምሳሌ ሆኗል። ሲታተትም ኮከብ ብሩህ እንዲሆነ ጻድቃንም ብሩሃነ አእምሮ ናቸውና ይላል። የሰይጣን ምሳሌም ሆኗል። እፎ ወድቀ ኮከበ ጽባሕ ሲል ኮከበ ጽባሕ ያለው ሰይጣንን ነው። ለሁሉም ግን መጽሐፋዊ መሠረት አለው። መቼም ሁሉም ምሳሌ ዘየኀፅፅ ነው በማለት ሁሉን ለሁሉ ምሳሌ ላድርግህ ማለት አይገባም። ሕፀፁ እንዳይጎላብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

መ/ር በትረማርያም አበባው