Get Mystery Box with random crypto!

_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፱_ አንቀጽ ፳፮ ስለ ስጦታ ይናገራል። ፩) ገንዘብ ላለው፣ ለባለጸጋ የሚሰ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፱_
አንቀጽ ፳፮ ስለ ስጦታ ይናገራል።
፩) ገንዘብ ላለው፣ ለባለጸጋ የሚሰጡት ስጦታ ሀብት ይባላል። ገንዘብ ለሌለው ለድሃ የሚሰጡት ስጦታ ምጽዋት ይባላል።
_
፪) ሀብት የትሩፋት ሥራ ናት። ስጦታ ነውር ቢገኝበት ይመለሳል። ምጽዋት ግን አይመለስም።
_
፫) ስጦታ የተቀበለ ሰው ስጦታውን ከተቀበለ በኋላ በስጦታው ማዘዝ መሰልጠን ይገባዋል።
_
፬) ስጦታ የሚሰጥ ሰው አካለ መጠን ያደረሰ፣ አዋቂ፣ ራሱን የቻለ ደልዳላ ካልሆነ ስጦታው አይጸናም።
_
፭) ስጦታን ሰጪው መልሱልኝ ካለ ሊመለስ ይችላል።
_
፮) ስጦታ ለባዕድ ከሆነ በደብዳቤ፣ ለዘመድ ከሆነ በቃል ያለ ደብዳቤ ትጸናለች።
_
፯) ገንዘብ ላለው ነው እንጂ ገንዘብ ለሌለው ሰው የሰጡት ስጦታ አይጸናም።
_
፰) አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ስጦታ ቢሰጥና በኋላ ቢወልድ እንደገና ያንን ስጦታ ለልጁ መስጠት ቢፈልግ ቀድሞ ከሰጠው ተቀብሎ ለልጁ ይስጠው።
_
፱) ሰጭ ልቡናው ድል የሚነሳበትን ገንዘብ መስጠት አይገባውም። በስጦታው እንዳይጸጸት።
_
አንቀጽ ፳፯
ይህ አንቀጽ ስለ ብድር ይናገራል።
፩) ብድር ከምጽዋት ወገን ናት። [በረኃብ ዘመን በዓይነታው ማበደር ከምጽዋት ቁጥር ነውና]
_
፪) ከአንተ ሊበደር የወደደውን አትከልክለው። ተበዳሪም ብድሩን ለመክፈል ማሰብ መትጋት ይገባዋል።
_
፫) የሚከፍለውን እስኪያገኝ ድረስ አበዳሪ ተበዳሪን መታገሥ ይገባል።
_
፬) በመያዣ፣ በገንዘብ ዋስ፣ በእጅ ዋስ፣ በደብዳቤ ማበደርና መበደር ይገባል። ደብዳቤው ሲጻፍ ምስክሮች ሊኖሩ ይገባል።
_
፭) ብድርን በቀነ ቀጠሮው መመለስ ይገባል። ተበዳሪ ባላገኝ መያዣውን አስቀር ያለ ቢሆን አበዳሪ መያዣውን መውሰድ ይገባዋል።
_
፮) ተበዳሪ የምከፍለውን ገንዘብ አጣሁ ቢል አበዳሪ ከተበዳሪ ገንዘብ በዳኛ ትእዛዝ ያገኘውን መውሰድ ይገባል።
_
፯) ተበዳሪ በእርሱ ላይ ያለውን ዕዳ ቢክድ፣ ከካደ በኋላ አበዳሪ የያዘው ደብዳቤ ቢመሰክርበት ሙሉውን ይክፈል። ተበዳሪው ክዶ ቢምል፣ ከማለ በኋላ ምስክሮች ቢመሰክሩበት በሐሰት ስለማለ እጥፍ ይክፈል። ከካደ በኋላ ማል ሲሉት ፈርቶ ቢያምን እጥፍ ከመክፈል ይድናል።
_
፰) በመያዣ የሄደ ገንዘብ ቢኖርና ገንዘቡ ቢጠፋ መያዣው ትርፍ ካለው ትርፉን መልሰው ዓይነታውን (ተገምቶ) ይውሰዱ። ብድሩን ከባለዕዳው የተቀበለ አበዳሪ መያዣውን ለባለቤቱ መመለስ ይገባዋል።
_
፱) አበዳሪ ከተበዳሪ የተቀበለውን መያዣውን እንደገንዘቡ አድርጎ ሳይጠብቀው ቀርቶ ቢጠፋና ባይገኝ መሰሉን መክፈል ይገባዋል። በተወሰነ ሥርዓት እስከዚህ ቀን ድረስ ባገኝ ብድርህን እሰጥሀለሁ ባላገኝ መያዣውን ታስቀራለህ ተባብለው ቢሆን ዳኛ ይፍረድ። መያዣው ከብድሩ ጋር እኩል ከሆነ ሁለቱም ነጻ ናቸው። መያዣው ቢበዛ ብድሩ ቢያንስ አበዳሪ በብድር ልክ አስቀርቶ የመያዣውን ትርፍ መመለስ ይገባዋል። ብድሩ ቢበዛ መያዣው ቢያንስ ተበዳሪ ቀኑ ሲደርስ የብድሩን ትርፍ መመለስ ይገባዋል።
_
፲) ሊሸጡት የማይገባውን መያዣ አድርጎ መቀበል አይገባም። ብድሩ ከሚከፈልበት ቀን አስቀድሞ ፈጥኖ ብል የሚበላውን ልብስ ነቀዝ የሚበላውን እህል መያዣ አድርጎ መቀበል አይገባም።
_
፲፩) ከሰው ዘንድ ገንዘብ ያለው ሰው እስከ ሠላሳ ዘመን ስጠኝ ባይለው ከዚያ በኋላ ተመልሶ ስጠኝ ማለት አይገባውም። ማንኛውም ሕጋዊ ጉዳይ ከሠላሳ ዓመት በላይ ከሆነ አይጠየቅም።
_
፲፪) አባት እርሱ አዞት የተበደረ ካልሆነ በልጁ ብድር መያዝ አይገባውም። ልጅም በእናቱ በአባቱ ብድር መያዝ አይገባውም። [ሐተታ:-አባት እርሱ አዞት የገደለ ካልሆነ በልጁ ደም መያዝ አይገባውም።ወንድምም በወንድሙ ደም መያዝ አይገባውም። አብሮ የመከረ የገደለ ቢሆን ነው እንጂ]።
_
፲፫) የእጅ ዋስ (የሰው ዋስ) አድኅኖ ይባላል። የእጅ ዋስ የሆነ ሰው እጁን ማቅረብ ይገባዋል። የእጅ ዋስ ሲዋስ እገሌን ላቀርብ ተውሻለሁ ይበል። ቀን ወስኖ ቢዋስ የተዋሰውን ሰው አቅርብልን ሲሉት ማቅረብ ይገባዋል። ሰውየውን ካቀረበ በኋላ የእጅ ዋስ አይጠየቅም። ሰውየውን ማቅረብ ካልቻለ ግን ይጠየቃል። እርሱ ይከፍላል። የገንዘብ ዋስ ተሐብዮ ይባላል። ገንዘቡ ለታወቀ ይከፍላል ለሚሉት ሰው መዋስ ይገባል። አበዳሪ አስቀድሞ ተበዳሪን ይጠይቀው። ባይከፍለው ሄዶ ዋሱን ይያዝ። ተበዳሪ ሩቅ ሀገር ቢሄድ ለዋሱ ዳኛ ቀን ይስጠው። ዳኛ በሰጠው ቀን ባያገኘው ዋሱ ይክፈል።
_
፲፬) ለዋስ ዋስ የሚሆን ሰው የጠለፋ ዋስ ይባላል። ዋስ ባይገኝ የጠለፋ ዋስ ይያዛል። ካህን አንዱንድንኳ በጭዋ ዳኛ ቁሞ መዋስ ማዋስ፣ መያዣ መያዝ ማስያዝ አይገባውም።
_
፲፭) ሴት የእጅ ዋስ የገንዘብ ዋስ መሆን አይገባትም።
_
፲፮) መያዣ ልብስን መያዝ አይገባም። ተበዳሪው እንዲራቆት መፍረድ አይገባምና።
_
አንቀጽ ፴፰
ይህም አንቀጽ ስለብድር ይናገራል። አንቀጽ ፳፯ የእጅ ብድርን ይናገራል። ይህኛው አንቀጽ ደግሞ ትርፍ የጋራ ስለሆነ ብድር ይናገራል። ባለሀብቱ ገንዘብ ችሎ ንግዱን ሥራውን ደግሞ ተቀጣሪው ይሠራና ትርፉን መካፈል ነው።
፩) ከትርፉ በስፍር በቁጥር በታወቀ ገንዘብ ነው እንጂ ባልታወቀ ገንዘብ መዋዋል አይገባም።
_
፪) በእኩሌታው በተገኘው ትርፍ አንዱ ለራሱ ሥራ ሊሠራበት አይገባም። ባለቤት በወደደው ጊዜ ውሉን ማፍረስ ይገባዋል። ነጋዴም በወደደው ጊዜ ውሉን ማፍረስ ይገባዋል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፳ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው