Get Mystery Box with random crypto!

_ ፷፩) ጥምቀት የተነሣ ልጅ ያላቸው አባትና እናት በፊት ሁለት ቀን በኋላ ሁለት ቀን ከመገናኘት | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_
፷፩) ጥምቀት የተነሣ ልጅ ያላቸው አባትና እናት በፊት ሁለት ቀን በኋላ ሁለት ቀን ከመገናኘት (ሩካቤ) መከልከል ይገባቸዋል።
_
፷፪) ሩካቤ የሚከለከልባቸው ጊዜያት
√ ሴት በወር አበባዋና በአራስነቷ ጊዜ
√ በጾም ወቅት፣ በሰሙነ ሕማማት
፷፫) በጾም ሩካቤ መከልከሉ ስለጾም የሚሆን ፈቃደ ነፍስ ይፈጸም ዘንድ ነው። ከሰሙነ ሕማማት ውጭ ባሉ አጽዋማት በፍትወት ጾር ድል የተነሣ ሰው ቢኖር የፈቲውን ጾር ማራቅ ይገባዋል። [ሩካቤ ይፈቀዳል። ይህ ግን ላልተቻለው ነው እንጂ ለተቻለውስ ሁሉንም አጽዋማት መታቀብ መልካም ነው]።
_
፷፬) ከሴት ማኅፀን አውጥቶ ከውጭ ዘርዕን መዝራት አይገባም።
_
፷፭) ላለመፀነስ ወይንም የተፀነሰውን ለማስወረድ መድኃኒት መጠቀም አይገባም።
_
፷፮) ሚስቱ እንደሰሰነች የነገሩት ሰው ቢኖርና ድርስ ነገሩን ባያውቅ፣ ድርስ ነገሩን ሊያውቅ ቢወድ ወደ ቤተክርስቲያን ዳኛ ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ይውሰዳት። ከታቦቱ ፊት ያቁማት። ካህኑ መንቀል አንስቶ ይያዝ። ከርቤ ይጨምርበት። ከሐመደ ምሥዋዑ ከውሃው ይጨምሩበት። ከዚያ ይህንን በእጁ ይዞ። ክንብንብሽን አውርጂ ይበላት። በእግዚአብሔር ያምላት። ሌላ ሰው አልደረሰብኝም ብትል ባልሽ ከጠረጠረው ነገር የነጻሽ ከሆነ ይህን ውሃ ጠጪ ይበላት። በሐሰት ብትምዪ ግን ይህ የምትጠጪው ውሃ ሥጋሽን ያሳብጠው ይበላት። ሴትዮዋም አሜን አሜን ወአሜን ትበል። በታቦቱ ፊት ሆና ውሃውን ትጠጣ። ንጹሕ ከሆነች ደስ የምትሰኝበትን ልጅ ትወልዳለች።
_
፷፯) ማግባት ርኵስ ነው ብሎ ከጋብቻ የተከለከለ ሰው ኃጥዕ ነውና ከቤተክርስቲያን ይለይ።
_
፷፰) ሴት ልጅ በወር አበባዋ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን አትግባ። የደሟ ወራት እስኪፈጸም ድረስም አትቁረብ።
_
፷፱) ወንድ የወለደች ሴትም ከወለደች ጀምሮ 40 ቀን ከቤተክርስቲያን ውጭ ትቆይ። ሴት ከወለደች 80 ቀን ትቆይ።
_
፸) [ቁጥር ፱፻፴፮] አዋላጆች ወንድ ካዋለዱ 20 ቀን፣ ሴት ካዋለዱ 40 ቀን እስኪሆናቸው ድረስ ሥጋውን ደሙን አይቀበሉ።
_
፸፩) ባል ያላት ሴት ብትሰስንና ባሏ ባያውቅ ለብቻዋ ንስሓ መቀበል ይገባታል። ባሏ እያወቀ ሊፈታት ባይወድ ግን ሁለቱም ከምእመናን ይለዩ።
_
፸፪) የቄስ ሚስት ባሏ ከሞተ በኋላ ሌላ ብታገባ ንስሓ ይገባታል። በታች መቆም በኋላ መቀበል ይገባታል።
_
፸፫) ጋብቻ በሚከተሉት ነገሮች ይፈርሳል።
√ ባልና ሚስት ተመካክረው ከመነኮሱ
√ አንዱ የአንዱን ፈቃድ አልፈጽምም ቢል
√ አንዱ የአንዱን ሰውነት ሊያጠፋ ቢወድ
√ ባል ከሚስቱ ጋር መገናኘት (ሩካቤ) ካልቻለ
√ ሚስት ከባል ጋር መገናኘት ካልቻለች
(አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ሆኖ ለሩካቤ ቢከለክል)
፸፭) ባል ሚስቱን ጋኔን ሲጥላት ቢያገኛት፣ ይህ ሁኔታ ካገባት በኋላ ያገኛት ከሆነ እርሱ መርዳት መታገሥ ይገባዋል። እርሱንም እንዲህ ያለ ነገር ቢያገኘው እርሷ መርዳት መታገሥ ይገባታል። ከማግባቷ በፊትም እያመማት ሳለ ደብቀው ቢያጋቡትና ቆይቶ ቢያውቅ መፍታት ይችላል።
_
፸፮) ከተጋቡ በኋላ ከሁለቱ አንዱን ደዌ ሥጋ ቢይዘው አንዱ ከአንዱ ሊለይ ቢወድ መለያየት አይገባውም። ሊፈታት ቢወድ ግን ትልወቷን ማጫዋን ሁሉ መስጠት ይገባዋል።
_
፸፯) ሰው በእሥራት ሳለ ወይም ባልታወቀ ምክንያት ቢጠፋ ግቢው ይፍረስ አንልም። መፈታትና አለመፈታቱ እስኪታወቅ ድረስ ባልና ሚስት ሆነው ይኑሩ እንጂ።ከአምስት ዓመት በኋላ ግን እንደ ፈቃዳቸው ይሆናል።
_
፸፰) ባል ዘማች ቢሆን እስከ ሁለት ዓመት ሚስቱ ትጠብቀው። ሚስት ስለ ባሏ ህልውና ምንም ዓይነት ዜና ካልሰማች፣ መሞቱንም ከመኳንንት ካልሰማች አታግባ። ሌሎች ሰዎች ሞቷል ብለው ቢናገሩ ለምስክርነት በመካከላቸው ወንጌል ያኑሩና ያምሏቸው። ድርስ ነገሩ ከታወቀ ከዚህ በኋላ ዳዊት እያስደገመች ቁርባን እያስቆረበች አንድ ዓመት ትጠብቅ። ከዚያ በኋላ ማግባት ትችላለች። ምስክሮች በሐሰት ሞቷል ብለው ቢመሰክሩ አሥር ወቄት ወርቅ ይክፈሉ። ሞተ ብለው ያወሩበት ወታደርም ከወደደ ሚስቱን መልሶ ወደ ቤቱ ያግባት።
_
፸፱) ባሏ ሳይፈቅድላት ከሌላ ወንድ ጋር ብትጠጣ፣ ወደ መሸታ ቤት ገብታ ብትስቅ ብትጫወት፣ ከቤቷ ወጥታ ከውጭ ከባዕድ ቤት ብታድር ይፍታት።
_
፹) ሚስት ባሏን ለመግደል ብትሞክር ወይም ሌለች ሊገድሉት እንደሆነ እያወቀች ዝም ካለችው ጋብቻቸው ይፈርሳል።
_
፹፩) ሚስት ያገባ ሰው በእርሱና በሚስቱ መካከል ክፉ ነገር ቢገኝ፣ ከምክንያት ወገን ማናቸውም ምክንያት ቢኖርበት ይታገሣት። ከክፋት ወደ በጎነት እስክትመለስ ድረስ ይምከራት ያስመክራት። መክሯት አስማክሯት ባትመለስ ወደ ደግ ቄስ ይውሰዳት። ቄሱም በመካከላቸው ሆኖ ያስታርቃቸው። ቄሱን አይሆንም ብትለው ኤጲስ ቆጶሱ አብረሽ ኑሪ ብሎ ይፍረድባት። ለኤጲስ ቆጶሱም ባትታዘዝ ባሏን ጥላ ብትሄድ ሁለተኛ አባብሎ ይመልሳት። በእምቢተኝነቷ ከጸናች ባሏ የወደደውን ማድረግ ይገባዋል። ሌላ ሊያገባ ቢወድ ያግባ። በንጽሕና መኖር ከፈለገ ይመንኩስ። እርሱ ገፊዋ ጠላቷ እንደሆነ ከታወቀና የቤት ቀጋ የሜዳ አልጋ ቢሆንባት ቃሉን አይቀበሉት። ግድ አብረህ ኑር ብለው ይፍረዱበት።
_
፹፪) ባል ከሚስቱ ሌላ ሴት ጋር ሲዘሙት ቢገኝ (ሴትም ከባሏ ሌላ ወንድ ጋር ስትዘሙት ብትገኝ) ዝሙቱን ባይተው ጋብቻው ይፈርሳል። ባልና ሚስት የሆኑ ዘማውያንን አያፋቷቸው። ካህናት ቀኖና ሰጥተው ያስታርቋቸው እንጂ።

አንቀጽ ፳፭
ይህ አንቀጽ እቁባት ማኖር እንደማይገባ ይናገራል።
፩) በኦሪት ነበር እንጂ በወንጌልስ እቁባት ማኖር አይገባም [የተከለከለ ነው]። ዕቁባት ማኖር ዝሙት ነው።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲፱ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው