Get Mystery Box with random crypto!

_ኢየሱስ ማን ነው? ክፍል ፫_ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው። ራሱ መድኃኒት ነው። እንጂ ለማ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_ኢየሱስ ማን ነው? ክፍል ፫_
ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው። ራሱ መድኃኒት ነው። እንጂ ለማዳን አብን የሚለምን አይደለም። በሥልጣን አብና ወልድ አንድ ናቸውና። ዮሐ. ፲፣፴ "እኔ እና አብ አንድ ነን" ይላልና። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ መድኃኒት ነው እንጂ ለማዳን ከአብ የሚለምን በሥልጣን የአብ ተወራጅ የሆነ አይደለም። ታድያ እንዲያ ከሆነ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. ፲፬፣፳፰ "ከእኔ አብ ይበልጣል" ለምን አለ ከተባለ የሚራብ የሚጠማ ሥጋን በመዋሐዱ እንዲያ አለ። በዚህ ምክንያት ዕብ. ፪፣፯ "ከመላእክት ጥቂት አሳነስከውም" ተብሏል። መላእክት የሚራብ የሚጠማ ሥጋ የላቸውምና በዚህ ምክንያት። በክብር ከመላእክት እንደሚበልጥ ዕብ. ፩፣፬-፮ "ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል---የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ" ተብሏል።
+
+
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ አምላክ የሆነ ሰው ነው ብለናል። ስለዚህ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውነትንም የአምላክነትንም ሥራ ይሰራል። ቅድመ ዓለም ነበረ ዓለምን ፈጠረ የምንለውም በኋላ ከድንግል ማርያም ተወለደ የምንለውም ያው አንዱን ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንደሆነ እንደሚነግሩን ሁሉ አምላክ እንደሆነም ይነግሩናል። ሃይማኖተ አበው ዘሄሬኔዎስ ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፲፱ "በከመ ይነግራነ መጻሕፍት ቅዱሳት ከመ ክርስቶስ ሰብእ ከማሁ እሙንቱ ይነግራነ ከመ ውእቱ አምላክ" እንዲል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ተብሏል ማቴ. ፩፣፩። የዳዊት ጌታም ተብሏል። አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክነትንም የሰውነትንም ሥራ ይሰራል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ለእኛ አርዓያ ለመሆን የሰራው ሥራ አለ፣ አምላክነቱን ለማሳወቅ የሰራው ሥራ አለ፣ ሰውነቱን ለማስረዳት የሰራው ሥራ የተናገረው ነገር አለ፣ ለቤዛነት የሰራው ሥራ አለ።ለእኛ አርዓያነት የሰራቸው ሥራዎች መጾሙ፣ መጸለዩ፣ መጠመቁ እና የመሳሰሉ ሥራዎች ናቸው። ማቴ. ፲፩፣፳፱ "ከእኔም ተማሩ" ብሎናልና። እሱ በመጾሙ በመጸለዩ በመጠመቁ የተጨመረለት ክብር የለም እርሱ በባሕርይው ክቡር ነውና። የአምላክነት ሥራ ሲሰራ ያዩት አምላክ ብቻ ነው ሰውነት የለውም ሰው አይደለም የሚሉ ነበሩና ሰውነቱን ለማስረዳት ራሱን ሲጠራ ብዙ ጊዜ የሰው ልጅ እያለ ይጠራ ነበር። ማቴ. ፲፩፣፲፱ "የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ" ተብሏል። መራቡ፣ መጠማቱ፣ መድከሙ፣ መሰቀሉ ሁሉ ሰው ስለሆነ የሆነው ነው። ከኃጢአት በስተቀር የሰውን
ሥራ ሁሉ ሰርቷል። ይህን አይተው ሰው ብቻ (ዕሩቅ ብእሲ) ለመሰላቸው ደግሞ አብርሃም ከመወለዱ በፊት አለሁ ብሎ በመናገር የአምላክነትን ሥራ ማለትም በደረቅ ግንባር ዓይን መፍጠር እና የመሳሰሉ ሥራዎችን ሰርቷል። ማቴ. ፲፪፣፰ "የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና" ተብሏል። ሌላው ለቤዛነት (ለካሣ) ነው። የአዳምን በደል ይቅር ለማለት አዳም ሊያደርገው የሚገባውን ሁሉ አድርጓል። አምላክ ሆኖ ሳለ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ" ብሏል። ተሰቅሏል። ተቀብሯል። በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል። መሥዋእት ወልድ በመስቀል ተሰቅሎ ራሱ ሊቀ ካህናት መሥዋእት አቅራቢ ሆኖ አዳምን ከአብ፣ ከራሱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስታርቆታል (ታርቆታል)። አዳምም ድኅነትን ስላገኘ ወደ ገነት ገብቷል።
+
+
ሥጋ ደካማ ነው። በቦታ የተወሰነ ነው። በጊዜ ተዋሕዶ ቃልን በመዋሐዱ የቃልን ርስት ወረሰ ማለትም የቃልን ገንዘቦች ረቂቅነትን፣ በሁሉ ቦታ መኖርን ገንዘብ አደረገ በዚህም ምክንያት ስለ ሥጋ እንግድነት ዮሐ. ፭፣፳፯ "የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው" ተባለ። ማቴ. ፳፰፣፲፰ "ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ" ብሏል። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሥልጣን አንድ ናቸው። አንዱን ብቻ ቢጠራ አድሎ መናገሩ ነው። ለምሳሌ ትንሣኤውን በተመለከተ ራሱ ወልድ በራሴ ሥልጣን ተነሳሁ ይላል። በሌላ ቦታ አብ አስነሳው ይላል። ሁለቱም አንድ ነው። በአንዲት ግብረ ባሕርይ ሦስቱም ይጠሩባታልና ነው።
+
+
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንናገር ራሱ ስለራሱ የነገርንን እና እርሱ ያስተማራቸው ሐዋርያት ስለእርሱ የተናገሩትን መሰረት አድርገን ነው። ክርስቶስ ያልሆነውን ኩነት ነው ማለት እና የሌለውን ማንነት መስጠት ግን ሰይጣናዊ ሥራ ነው። ወተት ነጭ ሆኖ ሳለ የሌለውን ማንነት በልብ ወለድ ወይም በውሸት ጥቁር ነው ማለት የሰይጣን የግብር ልጆቹ ሥራ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍትን በመሰለኝ እየተረጎሙ ከተጻፉበት ዓውድ አያወጡ እየተረጎሙ ብዙውን ዓለም እያታለሉ ያሉ የሰይጣን የግብር ልጆች አሉ። የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ራሱ ቃሉን ባስተላለፈበት ዓውድ ይነገራል እንጂ ቃሉን እኛ በተረዳንበት ልክ ብቻ አይነገርም። የሰው ልጅ በእውቀት የተወሰነ ስለሆነ ማለት ነው። ፪ኛ ጴጥ. ፫፣፲፮ "ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ" እንደተባለው ራሳቸው ለፈጠሩት ግላዊ አመለካከት ብለው የመጻሕፍትን ቃል የሚያጣምሙ ሰዎች በዝተዋል። በዋናነት ግን የሚጎዱት ራሳቸውን ነው። ምክንያቱም ሕይወትም መድኃኒትም ከሆነው ኢየሱስ ራሳቸውን አግልለው ራሳቸው በሕሊናቸው ለፈጠሩትና ማንነት ለሰጡት ነገር ይገዛሉና።

ክፍል ፬ ይቀጥላል ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።