Get Mystery Box with random crypto!

ትምህርቱን ሼር በማድረግ ያዳርሱ። ------የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ልዩነት----- _ኢየሱስ ማን | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

ትምህርቱን ሼር በማድረግ ያዳርሱ።
------የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ልዩነት-----
_ኢየሱስ ማን ነው? ክፍል ፪_
ከካቶሊክ ጋር ያለን ልዩነት በዋናነት በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።ካቶሊኮቹ ክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ነው ይላሉ። እኛ ኦርቶዶክሳውያን ደግሞ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንላለን። መጀመሪያ ኦርቶዶክስ የሚለው ስያሜ የተሰጠን በ325 ዓ. ም በኒቅያ ነው። ቀጥ ያለ ትክክለኛ እምነት ማለት ነው። በሐዋርያት ዘመን ደቀመዛሙርት እንባል ነበር። የሐዋ. 11፣26 "ደቀመዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ" ይላል። ክርስቲያን የተባሉት ቀድመው ደቀመዛሙርት ይባሉ የነበሩት ናቸው። በኋላም ኦርቶዶክስ የተባሉት ቀድሞ ክርስቲያን የተባሉት ናቸው። በ431 ዓ. ም ደግሞ ተዋሕዶ ተብለናል።
+
+
በአካል አንድ በባሕርይ አንድ ከማለታችን በፊት አካል ምንድን ነው? ባሕርይስ ምንድን ነው? የሚለውን መተርጎም ያስፈልጋል። አካል ባሕርይ ያልሆነ ነገር ግን የባሕርይ መገለጫ የሆነ ነው። በግሡ ከሄድን አከለ-በቃ ካለው የሚወጣ ዘመድ ዘር ነው። መብቃትን ያመለክታል። መብቃት ደግሞ በሁለት ይተረጎማል ወሰን ያለው መብቃት እና ወሰን የሌለው መብቃት ነው። ለምሳሌ በእንስራ ውሃ እያደረግን ሲሞላ በቃ እንላለን ወሰን እንዳለበት ለማመልከት ነው። አካል ስንል በሌላ መንገድ መብቃትን ማለትም ምንም እንከን የለሽ መሆንን ያመለክታል። አካል ለእግዚአብሔር ሲነገር ወሰን የለሽ ፍጹም መሆንን ያመለክታል። ስለዚህ አካለ ሥላሴ ሦስት ነው። አብ የራሱ የሆነ በዓለም የመላ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ አለው። የወልድም የመንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ነው። በአካል ሲኖሩም አንዱ ካለበት ቦታ ሁሉ በህልውና ሌላኛው አለ። ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. 14፣10 "እኔ በአብ አለሁ አብም በእኔ አለ" ያለው ይህንን ነው። ባሕርይ ማለት ደግሞ መሠረት ተብሎ ይተረጎማል። አካል ያልሆነ ነገር ግን በአካል ያለ አካል የገለጠው ባለቤት ነው። ሌላው ባሕርይ የሚባለው ሦስቱ አካላት አብ ወልድ መንፈስቅዱስ በከዊን (በመሆን) ቃል ልብ እስትንፋስ ናቸው። የኩነታት በሕልውና መገናዘብ ባሕርይ ይባላል። አንዲት ባሕርየ ሥላሴ ሦስት ኩነታት አላት መባሏም በዚህ መሰረት ነው። ወልድ ቃል ነው። ዮሐ. 1፣1 "በመጀመሪያ ቃል ነበር" እንዲል። አብ ልብ ነው መንፈስቅዱስ እስትንፋስ ነው። አንዲት ባሕርየ ሥላሴ በኩነት ትለያለች።
+
+
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነ ነው ስንል ሁለት አካል የተባሉ አካለ ሥጋና አካለ ወልድ ናቸው። አካለ ቃል በዓለም የመላ ረቂቅ ነው። አካለ ሥጋ በሦስት ክንድ ከስንዝር የተወሰነ ግዙፍ ነው። ሁለቱ በተዋሕዶ አንድ ሆኑ ማለት ነው። አንድ ሲሆኑ ግን ከተዋሕዶ በፊት ያላቸውን ማንነት ለውጠው ወይም አጥፍተው አይደለም። መምህረ ዓለም ቅዱስ ቄርሎስ "እንተኣሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲኣሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል" ቅድመ ተዋሕዶ የቃል ገንዘብ የሆኑት ሁሉ ማለትም ረቂቅነት በሁሉ ቦታ መኖር ለሥጋ ገንዘቡ ሆኑ። ይህም ሲሆን በተዓቅቦ ነው። ተዐቅቦ ማለትም ሥጋ ረቂቅ የሆነው ግዙፍነቱን ሳይለቅ ነው። ቃልም የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ ማለትም ረቂቅነቱን በሁሉ ቦታ መኖርን እንደያዘ ግዙፍነትንና በድንግል ማኅጸን መወሰንን ገንዘብ አደረገ። ክርስቶስ በአካል አንድ ነው ማለት ይህ ነው። በባሕርይ አንድ የምንለው ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ ማለታችን ነው። ሁለት ባሕርይ የተባሉት አሐቲ ባሕርየ ሥላሴ እና ባሕርየ ትስብእት ናቸው። ባሕርየ ሥላሴ በግብረ ባሕርይ ትገለጣለች። ይኽውም ሁሉን ቻይነት፣ ፈጣሪነት፣ ቀዳማዊነት፣ አለመራብ፣ አለመጠማት የመሳሰሉት ናቸው። ባሕርየ ሰብእ የሚባለውም በመገለጫ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚታመም፣ እና የመሳሰለው ነው። ሃይማኖተ አበው ዘሱኑትዩ "ኢይትረከብ ህላዌ ዘእንበለ አካል ወኢአካል ዘእንበለ ህላዌ" አካል ያለ ባሕርይ ባሕርይ ያለ አካል አይገኝም ብሏል። የባሕርይ ምንታዌ ስለሌለ የማይሞተው ሞተ ተባለ። ይህም የሆነው መዋቲን በመዋሐዱ ነው። መዋቲው ሕያው ተባለ ይህም የማይሞተውን በመዋሐዱ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ አምላክ የሆነ ሰው ሰው የሆነ አምላክ ነው። ሰው እንደመሆኑ በምራቁ ጭቃን ለወሰ ለመለኮት ምራቅ የለውምና። አምላክ እንደመሆኑ በምራቁ አፈርን ለውሶ ዓይንን አበራ።
+
+
ካቶሊኮቹ የሚያነሱት ሐሳብ ባሕርየ ሥላሴ አንዲት ከሆነች እርሷ የሰውን ባሕርይ ከተዋሐደች አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ ያሰኛል የሚል ነው። ነገር ግን ባሕርየ ሥላሴ ባሕርየ ሰብእን በቃልነቷ ከዊን ተዋሐደች የሚል መልስ ነው ያለን። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው ዮሐ. ፩፣፲፬ "ቃል ሥጋ ኮነ" በማለቱ ነው። አካል ብቻ ቢዋሐድ ኖሮስ በአካል ስሙ ወልድ ሥጋ ኮነ ባለ ነበር። ቃል ሥጋ ኮነ በማለቱ ግን የካቶሊካውያንን ነገር አፈረሰው። ሮሜ ፭፣፲ "ጠላቶቹ ስንሆን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን" እንዲል የአብ ልጅ የማርያም ልጅ ነው። ወልደ አብ ወልደ ማርያም አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በአካል አንድ ነዉ በባሕርይም አንድ ነው። አንድ ስለሆነም ዮሐ. ፫፣፲፮ "አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና" ተብሏል። ቅዱሳት መጻሕፍትም ክርስቶስን ሁለት ያሉበት ቦታ የለም። እኛና ካቶሊኮች "በመንፈስ ቅዱስ መሥረጽ ጉዳይ" ያለንን ልዩነት በቀጣይ ክፍል አቀርባለሁ።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
(ሃይማኖት በአደባባይ የሚነገር ስለሆነ ጥያቄ ያለው ካለ ይምጣ በአደባባይ እንጠያየቅ)