Get Mystery Box with random crypto!

#የፍቅር #ትርጓሜ ፍቅር የአንዱን ድካም አንዱ ሲሸከም ነው። ሰማዕትነት የሌለበት ፍቅር ፍቅር አይ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

#የፍቅር #ትርጓሜ
ፍቅር የአንዱን ድካም አንዱ ሲሸከም ነው። ሰማዕትነት የሌለበት ፍቅር ፍቅር አይባልም። በአፍ ብቻ እወድሃለሁ እወድሻለሁ ማለት ውሸት ነው። ይህንንስ ባላገሩ "የአፍ ዘመድ ከገበያም አይገድ" ብሎ ተርቶበታል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. ፲፭፣፲፫ "ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም" ብሎ የፍቅርን ትርጓሜ አስተማረን። ፍቅር በአፍ የሚናገሩት ብቻ አይደለም በሕይወት የሚኖሩትም ነው እንጂ። ለዚያም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በቃል ከተናገረ በኋላ በተግባር ደግሞ አዳምን ለማዳን በመስቀል የተሰቀለ። መስቀል ፍቅር በተግባር የተገለጠበት አደባባይ ነው። ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት ብሎ ሊቁ የገለጠው ይህንን ነው። ፍቅር ራሱ እግዚአብሔር ነው። ፩ኛ ዮሐ.፬፣፰-፳ "ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም እግዚአብሔር ፍቅር ነውና----ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው" ይላል። ይህ የሚነግረን በፍቅር ጥላቻ እንደሌለ ነው። ፍቅር ሌላውን እንደ ራስ መውደድ ነው። ማቴ. ፯፣፲፪ "ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው" ተብሎ እንደተጻፈ ሰውን መውደድ በእኛ ሊደረግብን የማንፈልገውን በሌላውም እንዲደረግ አለመፈለግ ሲሆን እግዚአብሔርን መውደድ ደግሞ ትእዛዙን በመፈጸም ይገለጣል።ዮሐ. ፲፬፣፳፩ "ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው" እንዲል።
√√√
√√√
ማቴ. ፯፣፳፩-፳፫ "በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን ይሉኛል። የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ አመፀኞች ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ" እንዲል የጌታን ስም ብዙ ጊዜ ብትጠራ፣ በስሙ ተአምራትን ብታደርግ፣ በስሙ ትንቢትን ብትናገር፣ በስሙ አጋንንትን ብታወጣ ይህ የፍቅር ምልክት ተደርጎ አይያዝም። እግዚአብሔርን የመውደድ ዋናው ምልክቱ ፈቃዱን መፈጸም ነው። ፈቃዱ ምንድን ነው ከተባለ ዘጸ. ፳፣፩ ጀምሮ ያሉ አስሩን ሕግጋት መፈጸም ነው። ማቴ. ፲፱፣፲፯ "ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ" እንዳለ። ዮሐ. ፲፪፣፶ "ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ"እንዲል።
√√√
√√√
ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን ጠቅለል አድርጎ ሲያቀርበው እንዲህ ብሎታል። ፩ኛ ቆሮ. ፲፫፣፪-፰ " ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድኾችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፃ ደስ አይለውም። ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም" ብሎ ገልጾታል።