Get Mystery Box with random crypto!

ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

የሰርጥ አድራሻ: @beteafework
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 29.70K
የሰርጥ መግለጫ

በዚህ ቻናል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች እና የአበው ቀደምት የተናገሯቸው መንፈሳዊ ንግግሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶችና መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡

Ratings & Reviews

2.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

1

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 64

2022-08-21 20:38:23 #ነሐሴ_16

#ዕርገተ_ማርያም

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ ።

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።

ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።

በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
7.4K views17:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 06:24:57 "መንፈሳዊ ጥበብን የምትወድ ነፍስ ዘወትር እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ሰው ሆይ! ሰዎች ክፉ ነገር ሲያደርሱብህ እግዚአብሔርን አመስግን፤ ያን ጊዜም ክፉው መልካም ይኾንልሃል፡፡

"እንዴት?" ብለህ የጠየቅኸኝ እንደኾነም፦ "በደል የሚፈፅመው ክፉ ነገር የሚቀበለው ሳይኾን ክፉ ነገር የሚያደርሰው ሰው ነውና" ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እመልስልሃለሁ፡፡

ስለዚህ ዘወትር እግዚአብሔርን አመስግን፡፡ ብትታመምም እግዚአብሔርን አመስግን፤ ሀብት ንብረት ብታጣም አመስግን፤ በሐሰት ቢከሱህም አመስግን፡፡ እንደ ነገርኩህ ተጎጂዎቹ ክፉ ተቀባዮች ሳይኾኑ ክፉ አድራሾች ናቸውና፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
5.6K views03:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-20 08:38:57 #የቅዳሜ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡ 
አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ

https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_16.html?m=1
6.0K views05:38
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-20 00:34:29 "በፈተና ጊዜ፥ ደካማው ሰው "እንደዚህ የደረሰብኝ'ኮ" እያለ የሚያመካኝበት ሌላ ሰውን ይፈልጋል፤ ብርቱው ሰው ግን በፈተናው ይጸና ዘንድ እግዚአብሔርን ይፈልጋል፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
5.0K views21:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-19 15:55:39

4.7K views12:55
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-19 06:46:39 የዓርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

አምላክን የወልድሽ እመቤታችን ሆይ! ፀሐይ ዘኢየዐርብ (የማይጠልቅ ፀሐይ) የተባለው የብርሃን ክርስቶስ እናቱ ነሽና በአፍኣ በውሰጥ በሥጋ በነፍስ አንቺን ብቻሽን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ልዑላን ከሚባሉ መላእክት አንቺ ትበልጫለሽ፤ ትሑታን ከሚባሉ ከደቂቀ አዳምም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከኀሊናት ኹሉ በላይ ነሽ (ኅሊና የአንቺን ክብር ተናግሮ መጨረስ አይቻለውም)፡፡ ክብርሽን ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው? አንቺንስ የሚመስል ማነው? ሊቁ አባ ሕርያቆስም፡- “ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩ ጥልቅነት ይዋኝ ዘንድ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል” ይላል /ቅዳ.ማር.ቁ.፹፬/፡፡ መላእክት ያከብሩሻል፤ ያገኑሻልም፡፡ ሱራፌልም ያመሰግኑሻል፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ አድሯልና፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ፤ ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለኛ ሰጥቶ ካባቱ ጋራ አስታረቀን፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በ “በእንተ ልደት” ድርሳኑ ላይ፡- “ስለዚህ ሥጋዬን ተዋሐደ! ወንጌልን ሲያስተምር እሰማው ዘንድ ሥጋዬን በተዋሕዶ ገንዘቡ አደረገው! ሥጋዬን ወስዶም መንፈሱን ሰጠኝ፡፡ ሰጠሁ፤ ተቀበልኩም፡፡ የእኔን ወስዶ የራሱን ስለ ሰጠኝም ሕይወትን ገንዘብ አደረግሁ፡፡ እኔን ለመቀደስ ሥጋዬን ተዋሐደ፤ የሚያድነኝ መንፈስ ቅዱስንም ሰጠኝ” ብሏል፡፡ ክብር የክብር ክብር ካለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

(ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ)
https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_1585.html?spref=fb&m=1
5.0K views03:46
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-18 20:27:32
5.2K views17:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-18 20:27:09 #ደብረ_ታቦር (ነሐሴ 13)

ነሐሴ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅና ክቡር በዓል ነው።

በዚች ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ስለ እነርሱም ጌታችን የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ አለ።

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደርሱ መጡ።
ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

ሰለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችንን ጌትነቱን የሚገልጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት።

ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ ስለ ርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጦአልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው ኤልያስንም ያሳረገው አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊአስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታቸንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው እንዴት አላት። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት። ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት። አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ።

ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሣው ቻለ። ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለ መለወጥ ያለ መለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁል ጊዜ አንድ ህላዌ ነው ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
6.1K views17:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-18 11:42:11 #የሐሙስ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡

  ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡

ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ

https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_14.html?m=1
4.6K views08:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-17 16:13:53 https://yt6.pics.ee/4e3rtw
5.6K views13:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ