Get Mystery Box with random crypto!

፬. ዮሴፍና ዮሃንስ ዮሴፍ ለማርያም በእጮኝነት ስም የተመደበ ባለአደራ ነው። ይህ ሰው በማያውቀው | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

፬. ዮሴፍና ዮሃንስ

ዮሴፍ ለማርያም በእጮኝነት ስም የተመደበ ባለአደራ ነው። ይህ ሰው በማያውቀው ሁኔታ የማርያምን መፀነስ ሲያውቅ ሊተዋት ሲፈልግ ‘እርሷን ለመውሰድ አትፍራ፣ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና ውሰዳት” ተብሎ ወስዷታል። ዮሓንስ በቀራንዮ “እነሆ እናትህ“ ተብሎ ወስዷታል። ሁለቱ ሰዎች ማርያምን ውሰዱ በመባል አንድ ናቸው፤ አንዱ በጽንስ ሌላው በመስቀል። ዮሴፍ ተወዳጁ በህጻንነቱ እንዳይገደል ከእናቱጋ ይዞት ሸሽቷል። ሄሮድስ አላገኘውም። በመከራው ብዙ ተፈትኗል። ቤተሰብ ይዞ መሰደድን የሚያውቅ ያውቀዋል። ፈተናው “ውሰድ” ከተባለ በኋለ የተከተለው ነው። ዮሓንስ ማርያምን ተወዳጁ በመከራ ሳለ ነው የወሰዳት። እነሆ እናትህ ተባለ። በማርያም እናትነት በኩል የጥምቀትን እናትነት ተመልክቶበታል። በጌታ ሞት እኛ ተወልደንበታል። ስለዚህ በማርያም ውስጥ የዮሓንስ ልጅነት ሲኖር በዮሓንስ ውስጥ የማርያም እናትነት ታውቋል። በዚህ ውስጥ የአብን ወላዲነት የወልድን ልጅነትንም አውቋል። “አባት ሆይ አንተ በእኔ እኔም ባንተ እንዳለሁ እነርሱም በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” ያለውን ቃል ያስቧል። ዳግም ከተወለድን በኋላ ሰውን በክርስቶስ እንጂ በሥጋው አናውቀውም። ለምሳሌም ማርያምን የምናውቃት ኢየሱስ በእርሷ በሰራው ታላቅ ስራና ጥበብ እንጂ በመልኳ ወይ በዜግነቷ አይደለም። የተነሳው ክርስቶስ በመልክ እንደማንረዳው ሁሉ በትንሳኤው ያሉትንም በመልክ አናውቃቸውም። በቃል፣ በድምጽ ይታወቃሉ። ቃሉም መንፈስና ህይወት ስለሆነ ስንሰማና ስንኖራቸው እናውቃቸዋለን። ዮኃንስ ይህን የመንፈስ ቅዱስ ስርዓት አግኝቶታል። ቃሉን ሰምቶ የሚያደርገው ለጌታ እናቱም ወንድሙም ዘመዱም ነው። ተወዳጇ እመቤትም “እንደቃልህ ይደረግልኝ” በማለቷ ቃል በእርሷ ሥጋ ሆኗል። እናቱ ሆናለች። በዚህ በኩር ናት።

በዮሴፍ ጊዜ ተወዳጁ አልተገደለም። በዮሓንስ ጊዜ ግን ተወዳጁ በፈቃዱ ሞቷል። ዮሴፍ የግርዘቱን ደም ሲያይ ዮኃንስ የመከራውን ደም ተመልክቷል። ማርያም ሁለቱንም ጊዜ ተመልክታለች። ዮሓንስ በራእዩ ሴቲቱ 1260 ቀን እንደተስደደች ጽፏል። ይህ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ በዮሴፍ ጊዜ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ዮሴፍ ህፃኑና እናቱን ይዞ ከሄሮድስ ተሸሽጎባታል። ግብጽና ኢትዮጵያ መሸሸጊያ ናቸው(መንበረ ማርቆስ)። ይህን ያወቅነው በዮሃንስ የመቅደስ መለኪያነት ነው።መለኪያው ያለው ዮሓንስን ሆኗል (ማርያምን “ፀጋን የሞላብሽ” የሚያስብለን መንፈስ ለእኛም የተሰጠ እንደሆነ ያመለከተን ዮሓንስ ነው።”ቃል ስጋ ሆነ።ጸጋና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ” በማለት...በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ክፍፍል መነሻዎች ይህ የቃል ሥጋ ሆነ ነገር ነው)።

1260 ቀን በሰሜኑ በር 1985 ዓመታት ናቸው። ዓለምም እውነቱን ሲያሳድድና ሲገል እስከዛሬ አለ። ለዚህን ያህል ዘመን ይህ የወንጌል እውነት ተሸሽጎ ነበር። አሁን ከስደት ተመልሷል። እንደ ዮሴፍ በዚህ ተሸሽጓል። እንደዮኃንስ ከዚህ ይነገራል። 1985 ዓመታቱ ተጠናቀዋል። ዮሴፍ ስራውን ፈጽሟል። ዮሓንስ ይቀጥላል። በትንሣኤው “ና ተከተለኝ” ተብሎ በድጋሚ የተጠራ እሱ ነው።ወደ አብ የሚያርገው ተወዳጅ ስለጠራው ሙሉውን መለኪያ አግኝቷል። ‘በመጀመሪያ ቃል ነበር’ ብሎ ከአብ መወለዱን መስክሯል። የማርያምን የአብ ምሳሌነት አውቋል። አግኝቶታልም። ኖሮታልም።

ቅዳሴያችን በቤተልሄም ጀምሮ በቀራንዮ ያልቃል። እንደ ማርያም ስናየው በዮሴፍ ጀምረን በዮሃንስ እንፈጽማለን። ይህ እውነት በህይወታችን ከተፈጸመልን በእውነት ፍልሰታው ለእኛም ሰርቷል። በእምነቱ በዮሴፍነት ላይ ያለም በበአለ ሃምሳ ያለም ይጸልይ። ፍጻሜው ጌታ ነው፤ ይገለጻል። አበው ዮሴፍና ዮሃንስ አብረው ሲቀድሱ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል ይላሉ። ሁለቱን በአንድ ሰብእናና ዘመን አግኝተን እየኖርነው አይደል? ኢትዮጵያ የዮኃንስ ራእይ ማእከል ናት። በመቅደሱ ፍጻሜ በቅድስተ ቅዱሳን ነን። በሃያው ክንድ ወይም በአስሯ ቀን ነን። እርሷም መቶሃያው ቤተሰብ የተጉባትና በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁባት ናት። አህዛብን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛው ወንዱ ልጅ በዚያ ይኖራል። ለሁሉም እንደየቋንቋው ሊሰማው የሚችል ከነገድ ከቋንቋ የሚዋጅ የፅዮን ድምጽ ይነገርባታል።

፻፳ን በ፲ ስናበዛው ፲፪፻(1200) ቀናትን ይሆናል። ከዋናው የበዓለ ሀምሳ ፶ ቀናት'ጋ ሲደመር ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ይሆናል (እራሳቸው መቶሃያው ቤተሰብ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ ተሰደዋል። አሁን ይህ እየሆነ ነው። በምስራቁ በር መንፈስ ቅዱስ የወረደው በማርቆስ እናት ቤት ነው። በሰሜኑም እንደዚያው ይሆናል (ኢትዮጵያ በማርቆስ መንበር ናት፤ እዚያ ነን)፡፡ ዛሬ በዓለምና በተለይ በሃገራችን ዘንዶው እያሳደደ ያለው ይህን እውነት ነው። ምእመኗን ካላጠፋሁ ብሎ የከበበው ለዚህ ነው። ለ1260ቀን ውሸቱን እየለቀቀ ያሳድዳል። "ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት" ይላል ዮኃንስ። ዘንዶው የተፋውን ውኃ ውጣዋለች። እኛ ከተማይቱን ገልጾልን አይተናታል። ከሃያው ክንድ ኅይል ይወጣል። እንደሄደብን ይመጣል። ደግሞም መጥተናል። እስቲ እንደሀዋርያት እንዲገለጽልን የምንፈልገውን ነገር እንንገረው። ፍጻሜው ላይ ነን፤ ሚካኤል ስራ ላይ ነው (ለዛሬ በጸሎት ያላችሁ የዮኀንስ ወንጌልን እያነበብችሁ አስቡን)።

ተጻፈ: በደመወዝ ጎሽሜ (ጋሼ)
ማስታወሻ :- ፲፮ የሚለውን መጽሐፉን ካላነበባችሁ የቁጥር ስሌቱን ጨምሮ ሙሉ መረዳት አይኖራችሁም:: ለአሁን፣ የሆነ ነገር ካገኛችሁበት በቂ ነው:: ዞሮ ዞሮ፣ እስቲ መልካም ቆዩ!

@bemaledanek