Get Mystery Box with random crypto!

ሰሙነ ፲፮ ማርያምና ኢትዮጵያ ሰሞኑ ለተዋሕዶ ክርስትና አማኞች የፆም ወቅት ነው። | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

ሰሙነ ፲፮
ማርያምና ኢትዮጵያ

ሰሞኑ ለተዋሕዶ ክርስትና አማኞች የፆም ወቅት ነው። የፍልሰታ ፆም! እስቲ አንዳንድ እውነታዎችን እንጨዋወትበት።

፩. የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም!

ከቶማስ ውጭ ያሉት ሌሎች ሐዋርያት የማርያምን ትንሣኤ ከእርሱ ሰምተው መንፈሳዊ ቅናት ይይዛቸውና ሱባኤ ይገባሉ። ተገለጸችላቸውም። ጾሙ የዚህ መታሰቢያ ነው። እኛ ጾሙን ለሕይወታችን እንጠቀምበታለን። ታሪኩ እንዳለ ሆኖ 'ለሐዋርያት ምስጢር ይከፈልባቸዋል ወይ? ለአንዱ ተገልጾ ለሌላው ሳይነገር የሚቀር ነገር አለ?' ብለን እንጠይቅ። እርገት በመጽሀፍ ቅዱስ ሲመሰጠር የወንድ ስርዓት ነው። የሴት አይደለም። ዝርዝሩ ይቆየን። ሐዋርያትን ሊያስደንቃቸው የሚችለውም ይሄ ነው። በተለምዶ ይሁን ለቃል ካለመጠንቀቅ ባላውቅም የድንግል ማርያም እርገት ከተወዳጁ እርገት'ጋ ተመሳስሎ ይነገራል። የማርያም እርገት ከጌታ እርገት ይለያል። የጌታ ወደአብ፣ ወደክብሩ፣ ወደ አባቱ የገባበት ነው። በሊቀ ካህንነቱ እስካሁን ነፍሳችን ትገለገላለች። ወደ አብ በመግባቱ በምልአት እንደ አባቱ ሆነ። በሰው በኩል ሲታይ “ሰው አምላክ ሆነ “። የእግዚአብሔር ሀሳብ በእኛ ለመታሰብ ቻለ። ይህ የሆነልን በተወዳጁ እርገት ምክንያት ነው። ጳውሎስም ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የሚለው ለዚህ ነው። የማርያምና የሀዋርያት ግን በትንሳኤው ቢመስሉትም በእርገት ወደ አብ አልሄዱም። በነፍስ ስርዓት ይኖራሉ። ጌታ ተነስቶ ለአርባ ቀናት በኖረው ስርዓት ይቆያሉ። እነሱ የሞትና የሕይወት ቁልፍ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ የሰጣቸው ልጅነት አለቻቸው። ስለዚህ ሲሞቱም ፈልገውት እንጂ ሞት ገዝቷቸው አይደለም። ጳውሎስ “ቢሆንልኝ የሞቱን ጥምቀት እጠመቃለሁ” የሚለው በሞት መንገድነት የሚገኝ ታላቅ ምስጢር ስላለ ነው። ልጅነት ካለችህና ሙት ካስነሳህ አንተም ትነሳለህ ማለት ነው (ጠንቋይ ነው ለራሱ የማይሆነው)። ጌታ የኅያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እነማርያም ሕያዋን ናቸው። ጌታ እንዳለው ”አምላክ ሙሴን ሲያናግረው የአብርሃም፣ የይስሃቅ፣ የያእቆብ አምላክ ነኝ” ማለቱን በመጥቀስ የህያዋን አምላክነቱን ተናግሯል። በሞቱ እንደመሰሉት በትንሳኤውም ይመስሉታል። ሞቶ መነሳት ዋንኛ መገለጫው በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ መገኘትን ነው። አንዱ ስንዴ ሞቶ ሲነሳ ብዙ ሆኖ መውጣቱን ይመለከቷል። ጳውሎስ ስለ ትንሳኤ ሙታን ሲናገር “እኛ ህያዋን ሆነን የምንቀረው ያንቀላፉትን አንቀድምም” በማለት ነው። ታሪክ ጳውሎስ እንደሞተ ይናገራል። እርሱ ግን እስከ ምጽአት ህያው እንደሆነ ይናገራል። ጳውሎስ ትክክል ነው። እነርሱ በዙሪያችን አሉ። እንደ ደመና ከበውናል። የትንሳኤን ትምህርት ምስጢር የሚያሰኘውም እንደዚህ አይነት በመኖር ብቻ የሚታወቁ ነገሮች ስላሉት ነው። በዚህ የተነሳ ማርያምም ተነስታለች። ሁሉም ግን በራሱ ተራ ነው።

፪. ቶማስ

ሀዋርያት በቶማስ ያዩት ግን ያላወቁት አንድ ጉባኤ አለ። ይህም ከእርሱ በስተቀር ትንሣኤውን ያመኑት በቃልና በመገለጽ ነው። እንደ ቶማስ በመንካት አላመኑም። የተወዳጁን ጎን በመንካት የሚያነጋግረው ኢየሱስ እንደሆነ አውቆ አመነ። ያ ጎን በቀራንዮ ደምና ውኃ የፈሰሰበትና አባት በልጁ አምጦ እኛን የወለደበት ነው። ማየ ገቦ እንዲል መጽሀፍ። ከተወለድንበት ማህጸን ነው ማለት ነው። እናት!

የተነሳው ተወዳጅ ስጋና አጥንት ከመስቀል በፊት ከነበረው ስጋው የሚለይበት አንድ ነገር አለ። የተነሳው የሞት አገልግሎት አይከናወንበትም። ቀን በጨመረ ቁጥር ለሞት አይቀርብም እንደማለት ነው(በትንሳኤ የማያስፈልጉ የሰውነት ክፍሎችና ስርዓቶች አሉ። የሆድ እቃ ላያስፈልግ ይችላል እንደማለት ነው) እኛ ወደእርጅና እንገሰግሳለን። ጌታ ከተነሳ በኋላ ይህን አስቀርቶታል። ከክብር ወደ ክብር እየሄደ በመጨረሻም እየረቀቀ ሄዶ ወደ አባት ገብቷል። መርቀቅን ነው ማረግ የምንለው። ቶማስ ይህን አካል ነክቶት አምኗል። ይህ የነካው ስጋ ከማርያም የነሳው ስጋ ነው። ይህ ስጋ በነፍስ ስርዓት ውስጥ ያለ ነው።

፫. መቶ ሃያው ቤተሰብ

ጌታ ካረገ በኋላ ያሉት አስሩ ቀናት በሰሜኑ የመቅደሱ በር ሲለኩ 16.4 ዓመታት እንደሆኑ ከዚህ በፊት አውስተናል። ይህ የቅድስት ቅዱሳን ቁጥር አብን ይወክላል። ከአስሩ ቀን መንፈሱን ልኮ ወልዶናል። ማርያም የአብ ምሳሌ የተባለችውም በዚህ ወላጀነቷ ነው። በ16.4 ዓመቷ ወልዳዋለች። ይህ በስጋ ነው። በእነዚያ አስር ቀኖች ውስጥ 120ው ቤተሰብ እየጸለዩ ነበር። ማርያም እዚህም አለች። በስጋዋ የሆነውን ነገር የተረዳችውና ያወቀችው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነበር። የዚህ እውነት ምሳሌነቷን በሥሉስ ቅዱስ ተረጋገጠላት። ይህ የፅዮን እናትነት ነው፤ ሁሉም የሚወለድበት። 16.4 ለእርሷ ብቻ ታውቆ አልቀረም። ሁሉም ይህን እናትነት አገኙት። ተገለጸላቸው።

አጠቃላይ መቅደሱ በዘመን ሲለካ 1968 ዓመታትን ይሆናል (ፖለቲካችን ከመቅደስ የወጣበት ዘመን ነው)።መቶ ሀያው ቤተሰብ የኖራት ፲ ቀን ወይም 16.4 ዓመታት ቅድስተ ቅዱሳን ናቸው። ሁሉም ይህንን የወላጅነት ስርዓት አግኘተውታል። ተገልጾላቸዋል። በሌላ አባባል እያንዳንዳቸው 16.4 በመሆን ዓለምን ለውጠዋል። ስሌቱ ፦
1968 ÷ 120 = 16.4

በበዓለ ሀምሳ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ድምጹ ተነግሯል። ይህ ሁነት በሰሜኑ በር ለ1968 ዓመታት ክርስትና ለዓለም ሁሉ ተሰብኳል። በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመስክሯል። እኛም ይህ እንዲገለጽልንና እንድንኖረው ያስፈልጋል። ስሌቱም የሚናገረው ይህንን ነው (በነገሬ ላይ አንድ ሰው ለመብቃት 16 ዓመት ይፈጅበታል ማለት አይደለም። ይህ በጉ በሄደበት ሁሉ ለሚሄዱት የተሰጠ ነው። ከእነሱ የተነሳ ይህን በማመን የምናገኘውን ጸጋ ሰው ሆኖ በተገለጸበት ምልዓት መጠን ለመግለጽና ምን ያህል አምላክ እየሰራ እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳን ነው። ሁሉ በእርሱ ሆኗል። ያለ እርሱ የሚሆን እንደሌለም እንድናይበት ነው።)