Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ ...            'ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መ | በማለዳ ንቁ !

የቀጠለ ...

           "ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል" (ዮሐ. 7፥38)

እንዴት? ሊጠጣ እንኳ የተጠማ አንድ ሰው፥ መልሶ ወንዝን ያህል ከሆዱ ያፈልቃል? ጉዳዩ ሚሥጢርነት ያለው ይመስላል፡፡

በመነሻችን፥ ለሁለት የከፈልነውን ጉባዔ ማስታወሱ እዚህ ይጠቅማል፡፡ ከፅንሰት - ሞት እና ከሞት - ዕርገት ብለን በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ጉዞ በኩል ያየነው መንገድ አለ፡፡ የመጀመሪያው ሂደት የማንኛውም በሥጋ ያለ ሰው ጉዞ ነው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮ በመፀነስ ተጀምሮ በመሞት ይገባደዳል፡፡

ስለዚህ አምላክ ሰውን ሲሆነው፥ የተገለጸውን የሰው ልጅ የኅልውና  ሂደት ሳያስቀር ይሄድበታል /በባሕርይ ተዋሐደ የሚሉት ይሄን ነው፤ ካልተዋሐደ ሰው እንደሆነው አይሆንም፤ አለመዋሐድ (ምንታዌ) ሂደቱን ያገድፋል፤/፡፡ በመሆኑ ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ቋንቋ ይማራል፣ ያድጋል፣ ..  ለሰውነት የባሕርይ ሕጎች ይታዘዛል፡፡ ይሄ መታዘዝ እስከ መስቀሉ ድረስም ይቀጥላል፤ ለመስቀል ሞት እንኳ ታዘዘ እንዳለ!

በእምነት ጉዞ ውስጥ ላለውም ምእመን ሂደቱ ከላይ የተገለጸው ነው፡፡ በ'እንደ ቃልህ ይሁንልኝ' አሜንታ፥ ወንጌልን እየሰማ በልቡ ያኖራል፡፡ ይወለድ ዘንድ ይፀንሰዋል፡፡ ወንጌል በጽሩይነት ከተቀበሉት ከሰው ልቦና የሚጸነሰው ሕይወትነት ስላለው ነው፡፡ ሕይወት ስላለው፥ መጸነስ፣ መወለድ፣ ውህደት ፈጥሮ በጊዜ ጊዜ ማደግ፣.. ይችላል፡፡

እንግዲህ "የተጠማ ይምጣና ይጠጣ" ይኸው ቀዳሚ ጉዞ ነው፡፡ ንጹሕ ቃሉ ውኃ ነው፤ ከውኃም የሕይወት ውኃ፡፡ ምእመን ይህን ውኃ ከጥልቁ /ወንጌል በተፈጥሮ፣ በፍጥረታት፣ በሰው ባሕርይ፣ በመጽሐፍ ተጽፋ ያለች መሆኗ ጥልቅ እውነት ያሰኛታል፤/ እየጨለፈ ይጎነጫል፡፡ ስብዕናውን የሚሠራውን፣ ከየትኛውም ባርነት የሚገላግለውን፣ አስቀድሞ ማንነቱን ተከትሎ ሁሉን የሚያሳየውን ቃል እየተዋሐደ ወደፊት ይቀጥላል፡፡ አካሄዱን ዘርዝረነዋል፤ አንደግመውም፡፡ .. ምእመን ይቀጥላል፡፡

ጥሩ ምሳሌ ለዚህ የሚሆኑልን የመጀመሪያዎቹ የሕይወት ውኃ ተጎንጪዎች ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ ኢየሱስ፥ ሕያው ቃልን በማውጣት ማውረድ አስደምጧቸዋል፡፡ በየዋህነት፣ በደስታ፣ በእምነት፣ በተስፋ፣ በግርታ ሰምተውታል፡፡ ኋላም፥ እርሱ የሚያዝበት ጊዜው ደረሰና ተይዞ ተወሰደ፡፡ ተገደለም፡፡

በዚሁ አንጻር፥ እየፈሰሰላቸው ይጠጡት የነበረው የሕይወት ውኃ፥ በሚታየው ደረቀባቸው፡፡ "ከእኔ ትለፍ" ሲል ያሳለፋትን መሪር ጽዋ ቀመሷት፡፡ ከገዳይ ጎዳና ጠፍተው፣ ሥጋ ደሙን ወስደው፣ የቀጠራቸውን ረስተው (የሰሙትን ያህል ሞተው) ተሸሸጉ፡፡ ግን የሞተባቸው ወዳጅ፥ ከሞትም በኋላ የእንገናኛለን ቀጠሮን ሰጥቷቸው ነበር፡፡

              "ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።" (ዮሐ.14፥19)

ወይም፥

            "እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።" (ም. 16፥22)

'ዓለም ሳያየኝ እናንተ ታዩኛላችሁ፥ እንደገና አያችኋለሁ' የሚላቸው ያልሞተው፣ ከፊታቸው በሥጋ ሕግ የሚያዩት ኢየሱስ እንደሆነ ያጤኗል፡፡ ስለዚህ እንዴት ከዓለሙ ተሰውሮ ለነርሱ እንደሚገለጥ እንግዳ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚያውም ላይ ማንኛውም በሥጋ ያለ ሰው ሃሳብ እስከ ሞት ድንበር ይረዝማል፤ እነርሱም ሲያስቡ እስከዚህ ጫፍ ድረስ ነው፡፡ ከመቃብር ባሻገር፥ አለቀ፣ ደቀቀ፣ ተጠናቀቀ የሚል የነበርነትን ታሪክ እንጂ፥ ሕይወትን አግኝቶ የሚቀጥል ኅልውና አያውቁም፡፡ በመሆኑ ከሞት ወዲያ ቀጠሮ ይሉት ጉዳይ አይገባቸውም፡፡ ከመካከላቸው አንዱ እንግዳውን ንግግር እንዲያስረዳቸው ጠየቀ፥

              "ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው?"

ተመለሰለት፤

             "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።" (ም. 14፥23)

ይሄ ቃል የሕይወት ውኃ ነው፡፡ አንዲት ሳምራዊት ሴት እንደሰማቺው፥ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ዳግመኛ አይጠማም፡፡ ምክንያት?

ሐዋሪያቱ ጉዟቸው በቀራኒዮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ውስጣቸውን ሲዋሐድ የኖረው ቃል፥ ከውጪ ሲያገኙት የቆዩት ነው፡፡ በትምህርት፣ በምሳሌ፣ በሥራ፣ .. ሲቀበሉት ሰንብተዋል፡፡ ውኃው ወደነርሱ በመግባት ይፈስ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ውኃው ውስጣቸውን አጥለቅልቆ ሲሞላ /ይሄ በወቅቱ ለነርሱ ባይገለጥላቸውም፤/፥ ከሚታየው ይመጣ የነበረው ተቋረጠ፡፡ በድምፁ፣ በድርጊቱ ይሰሙት የነበረ ቃል ዝም አለባቸው፤ እንደነርሱ ባለ ውስን ሥጋና ነፍስ ሆኖ ይናገራቸው የነበረ መምህር፥ በአደባባይ ተገድሏልና፡፡

ሆኖም፥ እንደቀጠራቸው፥ ከሞቱ እንደተነሣ ወደነርሱ ሄደ፡፡ ከዓለም በሞቱ ተሰውሮ ግን ለነርሱ በትንሣኤ ተገልጦ አገኛቸው፡፡ "እኔው ነኝ" እያለም የሞተውን ቀሰቀሰላቸው፡፡ አሁን ሐዋሪያት ጌታቸውን ባለመጥፋት ያውቁታል፡፡ ህያውነትን አስረግጠዋል፡፡ ስለዚህ ትምህርቱን፣ ያሳየቸውን ሁሉ ከእንግዲህ በነበር አያስቡትም፤ መቃብርን አልፎ አግኝቷቸዋልና፡፡

በዚህ ሥርዓተ ትንሣኤ ለ40 ቀናት ተመላልሶላቸው፥ ወደ አባቱ ሊሄድ ወደ ዕርገቱ ወጣ፡፡ ወደ አብ (ዋናው ልብ) ከፍ ከፍ አለ ስንል፥ ከእነርሱ የኖረ ቃልነቱ ወደ ውስጥ አስኳላቸው፣ ወደ ልባቸው ዘለቀን እናስተውላለን፡፡ ልብ፥ ባሕርያዊ ግብሩ መውለድ ነው ይላሉ ሊቃውንት፡፡ አንባቢ አንተስ ልብ ብለሃል?

ቃል ወደ ወለደው ከሄደ፥ ውኃውም ወደ ምንጩ ተመልሷል፡፡ እነሆ ከውጪ የሚመጣው ከውስጥ የሚፈልቅ ሆኗል፡፡ ያ ሊጠጣ የተጠማ ሰው፥ ሌሎችን የሚያጠጣ የሕይወት ውኃ ወንዝን እንዲህ ባለ የሕይወት ጉባዔ ከሆዱ ያፈልቃል፡፡

የአብን ወላዲነት በወልድ መንገድነት በኩል በእውነት ያገኘ፥ ሃብታት፣ ሚሥጢራትን ይወልዳል፤ አዲስ ሃሳብ ያስገኛል፤ ጥበብን፣ ዕውቀትን ከማይታየው እየገለጠ ያመጣል፡፡ ይኸውም መገለጥ ጠርዝ፣ ማብቂያ የለውም፤ በየዕለቱ ይነጋል፡፡ ማለዳ ማለዳ ወጋገኑ የሚጨምር ዕፁብ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ ወንዝ አለው፤ ቢፈስ ቢፈስ ገደብ የሌለው፣ ያለማቋረጥ የሚወርድ አንጸባራቂ ውኃ ስለሆነ፡፡ እናስ ማነው? ይህን ያፈልቅ ዘንድ ጠጥቶ ሳለ ዳግም የሚጠማው? ..

አሁን ጥቅል ውጊያው ግልጽ ሆኖ ይገባናል፤

                   "ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።" (2ኛ ቆሮ. 4፥4)

ምእመን ቀዳሚውን ጉዞ በአስተምህሮት፣ በአምልኮት፣ በሕግ ትእዛዛት (በጥቅሉ ቃሉን በመጠበቅ) ይሄድበታል፡፡ የሚሄደው ምእመን፥ ሦስቱን የሃይማኖት ዐላባውያን የሚቀበለው ከርሱ ውጪ እንደሆነ ግልጽ ነው /በርግጥ አምልኮት መተሳሰሪያ ስለሆነ ከርሱ ውስጥ የሆነንም ይጠይቃል፤/፡፡ እነሆ ውጊያ ቁጥር አንድ ከዚህ ይጀምራል፡፡