Get Mystery Box with random crypto!

ጽንስ እንዲቋጠር፥ የወንድ ዘርና የሴት ደም ግዴታ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ጤናማ ካልሆኑ ጽንሱም አይ | በማለዳ ንቁ !

ጽንስ እንዲቋጠር፥ የወንድ ዘርና የሴት ደም ግዴታ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ጤናማ ካልሆኑ ጽንሱም አይሆንም፡፡ ዘር ከውጪ መጥቶ ደምን ይዋሐደዋል፡፡ በቅደም ተከተል ብናየው፥ ቀዳሚው የዘር ጤናማት ነው፡፡ ወይ ዘር የመዋሐድ አቅም ከሌለው፥ ደግሞ ቢኖረው ወደመዋሐድ አድራሻ መድረስ ካቃተው፥ ጽንስ አይፈጠርም፡፡ /አንባቢ የመጀመሪያው ሂደት፣ የእምነት ጉዞ፣ ከሥጋ ወደ ነፍስ ወደ መንፈስ የሚሄደው መንገድ፥ ከፅንሰት እንደሚነሣ በተደጋጋሚ የተነገረው እንዳይረሳ፤/

ለምእመናን በዘርነት የሚሰጠው ከወንጌል የሆነው አስተምህሮት ነው፡፡ ሕግና ትእዛዛት አስተምህሮቱን ይጠብቁታል፤ አምልኮት ወዲህ በምእመኑ ሕይወት ያዋሕደዋል፤ ከማይታየው ትስስር ያገናኘዋል፡፡ አስተምህሮት፥ በዕውቀትነት ሕግና ትእዛዛቱን ጨምሮ አምልኮቱንም ያስተምራል፡፡ ሚናው ወሳኝ ነው፡፡ ታዲያ አስተምህሮት ከተባለሸስ? ከወንጌል (ከእውነት) ማዕከል ፈር ከለቀቀስ? ዘር አቀባዩ ጤናማ ካልሆነስ? .. /አናብራራም፤ ኑሮአችን ስለሆነ እያንዳንዳችን ስለ እዚህ የምናውቀው፣ የምንለው ብዙ አለን፡፡/

የጥንቶቹ፥ ትምህርት ከሦስት ወገን ነው ይላሉ፡፡ ከመጽሐፍት፣ ከመምህራንና ከልቦና ነው ይላሉ፡፡ በተዋሕዶ ጉባዔ፥ ምእመናን ከመምህራን ወደ መጽሐፍት፣ ከመጽሐፍት ወደ ልቦና እንዲዘልቁ ታላቅ መስመር ተዘርግቶ ነበር፡፡ ሁለቱ፥ መምህራንና መጽሐፍት፥ ምእመናንን የሕይወት ውኃ እያጠጡ፥ ከልቦናው ሆድ ወንዝ እንዲያፈልቅ ተሰይመው ነበር፤ .. ነበር፡፡ ያው እንደምናየው ነው፡፡ /በመሠረቱ የመምህራን የአስተምህሮት ድርሻ፥ የምእመንን አስተሳሰብ ካነቁ በኋላ በወንጌል ወሳጅነት ራሱ ወደ ልቡ እንዲገባ ማገዝ ነበር፤ ግን ጌታ እንዳለው ነው፤ "እናንተ የዕውቀትን መክፈቻ ተቀበላችሁ ወይ አትገቡ ወይ አታስገቡ" እንዳለው፤/

ዘር በጤና ቢያልፍ፥ ሁለተኛው ደም በበኩሉ ጤናማ መሆን አለበት፡፡ ዘርን መቀበል፥ ተቀብሎም መዋሐድ ለጽንስ መኖር ግዴታ ነው፡፡ ጽንስ የሚቋጠረው በሴቷ ነው፡፡ ጽንሱን የመጠበቅ፣ የመሸከም፣ የማሳደግ ተፈጥሯዊው ባሕርይ እርሷ ጋር ነው፡፡ ካልቻለችስ? ብእሲት ምእመን ቃልን መዋሐድ እምቢ ካላትስ? ቃልን እንደሰማቺው መኖር ከሸሸችስ? .. /የዚህ ጥያቄ መልስ ከሁላችን ነው፡፡ እንደየራሳችን እንመልሰው እንጂ ስለ ልባችን ነገር ምን ተብሎ ምኑን ትቶ ይወራል?/

ሌሎቹ ከነዚህ ሥር የሚዘረዘሩትን የውጊያ ክፍሎች፥ ሁለቱን፥ መሠረታዊያኑን ስናልፋቸው እናወሳቸው ይሆናል፡፡ ጽንስ ሳይቋጠር ስለ አስተዳደጉ አንጨነቅምና፡፡

ለማንኛውም፥ ስናረዝመው የጀመርነው ይጠፋል፡፡ ስለዚህ በተወዳጅ ሰው፥ በጳውሎስ ሃሳብ እንጨርስ? /ታዲያ እስከ አሁን ባየነው ጉባዔ መሠረትነት የሃሳቡን አተረጓጎም እንዳናርቀው፤ ሰማይ በነፍስነት እኛ ውስጥ ነው፤ ምድርም በሥጋነት የኛው አካል፤/

            "በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።" (2ኛ ቆሮ. 5)


ተፈጸመ!

ማስታወሻ ፦ ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተያያዘ ወደታች ቢነበብ በጎ ነበር፡፡

@bemaleda_neku