Get Mystery Box with random crypto!

በሥጋ ወራት በተወሰነ ቦታና ጊዜ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው አንድ ኢየሱስ፥ በትንሣኤው ምክንያትነት | በማለዳ ንቁ !

በሥጋ ወራት በተወሰነ ቦታና ጊዜ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው አንድ ኢየሱስ፥ በትንሣኤው ምክንያትነት ከመወሰን ማዕቀፍ የወጣ ኅልውና ሆኗል፡፡ አንዲቱ የዘር ቅንጣት፥ አፈር ገብታ ስትበቅል አንድ ሆና አትወጣም፡፡ ትበዛለች፡፡ የተነሣውም ክርስቶስ ጊዜና ቦታ (የሥጋ ሕግ) ስለማይገዛው፥ ውስንነት የማይዘው ሁለንተናዊ ሆኖ በዝቷል፡፡ እንደማንኛውም ሰው በአንድ ሃገር፣ በአንድ ስፍራ፣ ከአንድ ሥጋና ነፍስ የተወለደው እርሱ፥ እስከአሁን ስንነጋገርበት በመጣንበት መልኩ በትንሣኤው ኃይል በሚቀበሉት ሁሉ ውስጥ የሚወለድ ረቂቅ ሆኗል፡፡ /ቃል ሥጋ ሆነ - ቀዳሚው ልደት፤ ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ - ደኃራዊው ልደት፤ አንባቢ ወንጌላዊ "እኛ" ብሎ አንዱን ኢየሱስ በክርስቶስነት ሲያበዛው አስተዋልክ?/

ስለዚህ ከትንሣኤው በኋላ፥ ክርስቶስን በሥጋ እንደሆነ አናውቀውም (እንደ መግደላዊት)፡፡ ይልቅ በእኛ ይኖር ዘንድ ባስቀመጠው፥ "አባ (ዳግም ከመንፈስ የተወለዱት)፣ አባት (ከሥጋ ተወልደው በመንፈስ ሊወለዱ የሚተጉት)" ስንል አብን በምንጠራበት የልጅነት መንፈስ እናውቀዋለን፡፡ ወይም በዚህ መንፈስ ባሕርያችንን በሚጎበኝበት ልዩ ቃሉ!

ቃል ካለ ሃሳብ አለ፡፡ ሃሳብም አስተሳሰብን ይሆናል፡፡ እንኪያስ ከላይ የጠቀስነው ብርቱ አሳዳጅ ይህን አስተሳሰብ መግደል ላይ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ሰው እንደየአስተሳሰቡ ክበብ ይኖራልና፤ አስተሳሰቡን እንደሠራው ቃል ያስባል /የሰውን ሕይወት ለመምራት አስተሳሰቡን መምራት ነው፤/፡፡ በመሆኑ ባለ ራሶቹ ዘንዶውና አውሬ፣ ነቢያቸውም የምድሩ አውሬ፥ ዘመቻቸውን በዚህ ክርስቶስ ኢየሱስ ሠርቶ፣ ለክቶ ባለሰበን መንፈስ ላይ ካደረጉ ዓመታት ከርመዋል፡፡ ይሄ ማስረጃን የማይጠይቅ የአኗኗራችን መረጃ ነው፡፡ አንባቢ፥ ለመሆኑ አሁን በዚህ ሰዓት፣ በዚህ ደቂቃ ምን እያሰብክ ነው?

በጀመርንበት እንጨርስ ዘንድ፥ ወዲህ ከመጽሐፍት፣ ከሰው ልብና አእምሮ፣ ከታሪክ፣.. አጠቃላይ ከዓለም ይሰደዳል ስላልነው አስተሳሰብ ግልጽ መረዳት ይኖረን ዘንድ፥ ተከታዩን የጌታ ሃሳብ ለመጠቅለያነት እናነሣው፥

              "ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል" (ዮሐ. 7፥38)

እንዴት? ሊጠጣ እንኳ የተጠማ አንድ ሰው፥ መልሶ ወንዝን ያህል እንዴት ከሆዱ ያፈልቃል? ጉዳዩ ሚሥጢርነት ያለው ይመስላል፡፡

*14 - ዓለሙ፥ ክርስትናን የተገነጠለ ሃይማኖታዊ መልክ ሰጥቶ በተቋምነት ብቻ ያውቀዋል፤ ሆኖም እርግጡን አደንድነን ከተነጋገርን ክርስቲያን መባል የሰው ልጅነት በከፍተኛ ክብርና ልዕልና ሲገለጥ የሚያገኘው የብቃት ስም ነበር፤ ክርስትና ክርስቶስን በመምሰል አያበቃም፤ በመሆን ይፈጸማል እንጂ /"መምሰል ላይ የሚያቆመው ዓለም አቀፎቹ የክርስትና ርእዮቶች ናቸው፤ ዓለሙ የሚያውቃቸው ዝነኛ ሃይማኖቶች የልዕልናይቱን ጽዋ ወደ ውስጥ እንድንጎነጭ አያሰናብቱንም፤ እያየናት ከደጅ ቆመን እንድናደንቃት እንጂ፤/፡፡ ኢየሱስ ተከታዮችን ሊያፈራ ለዓለም አልታየም፤ በእርሱ የተገለጠው ሁለንተናዊነት ማንነት በሁሉ እንደሁሉ እንዲሆን እንጂ፡፡ .. ህዝብ የሚከተላቸው የአደባባይ ሃይማኖቶች (main stream religions) በማወቅም ሆነ ሆን ብለው የሚያሳድዱት፥ ይህን የሰው ልጆቾ ሁሉ እውነትና መዳረሻ ነው፡፡


ይቀጥላል ...

@bemaleda_neku