Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ ... አዲስ ፍጥረት የመሆን ጸጋ የተሰጠው በክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ አዲስ ፍጥረት ያሰኘ | በማለዳ ንቁ !

የቀጠለ ...

አዲስ ፍጥረት የመሆን ጸጋ የተሰጠው በክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ አዲስ ፍጥረት ያሰኘውም፥ የሚታየውን ዓለም የተሻገረ ልዩ ኅልውና በመሆኑ ነው፡፡ የመጀመሪያው የፍጥረታት መገኛ የዘፍጥረቱ እሁድ፥ የክርስቶስ የትንሣኤው ዕለትም መሆኑ ይህን እውነት ያጸናዋል፡፡ ሁለተኛው እሁድ የአዲሱ ፍጥረት መገኛ ሁለተኛው ልደት ነው፤ ወይም የሁለተኛው መንገድ መነሻ ነው፤ ከሞት - ዕርገት ያልነው መንገድ፡፡ የማርቆስ ወንጌል 13፥31፤

              "ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።"

አስቀድመን እንዳልነው፥ ልደት ካለ የሚዘለቅበት ዓለም አለ፡፡ ልደት ማለፊያ በር ነው፡፡ እና፥ ከሥጋ የተወለደ ሁሉ ወደሥጋው ዓለም ይገባል፤ ከመንፈስ የተወለደ ደ'ሞ ወደረቂቁ ዓለም ይሻገራል፡፡፡ የሥጋ ልደት - የዚህ ዓለም ሂደት - በዘፍጥረቱ እሁድ - በመጀመሪያዎቹ ሰማይና ምድር ተይዞ እስከ እልፈቱ ይቀጥላል፡፡ ዳግም ልደት - የማይታየው ዓለም - በትንሣኤው እሁድ - በአዲሱ ሰማይና ምድር ይጀምራል፡፡ (ራእ. 21፥1) ይሄ ትንሣኤና ልደት አንድ መሆናቸውን ይነግረናል፡፡

እነሆ ኢየሱስ በሥጋ ልደቱ፥ ከታተመች ማኅፀን ወጥቶ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በትንሣኤ፥ ከታተመች መቃብር ወጥቶ ወደዚያኛው ሄደ፡፡ የሄደበት ዓለም፥ በጊዜ ልኬቱና በአውታሩ አሁን ከምናውቀው ይለያል፤ በአካሉም መንፈሳዊ ነው፡፡ ይሄን ያለንበትን ዓለም የሚገናኘውም በመንፈሳዊ ትስስር ነው፡፡ ለምሳሌ ከተነሣ በኋላ መግደላዊቱ አስቀድማ እንዳየቺው ተጽፏል፡፡ ሆኖም በመልኩ ወዲያውን አላወቀቺውም፡፡ ለምን?

እርሷ እየተመለከተች ያለቺው በዚህኛው ዓለመ ገጽ ጊዜና አውታር ውስጥ ሆና ነው፡፡ በአጭሩ፥ በሥጋ ነው፡፡ ሥጋ ደ'ሞ መንፈሳዊን አካል ወይንም በመንፈሳዊ ዓለም ያለን አካል በቀጥታ አያየውም፡፡ ወይ የተዋሐደ የመንፈስ እይታ ያስፈልገዋል አሊያም መንፈሳዊው አካል ራሱን በግዝፈት ለዚህ ዓለም መግለጥ ይኖርበታል፡፡

               "ስለዚህ ማንም በ(ትንሣኤ)ክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።" (2ኛ ቆሮ. 5፥17)

እውነት ነው! አሮጌው ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ በየዕለቱ እያለፉም ነው፡፡ በነዚህኞቹ አንጻር ያሉት ሥጋና ነፍስ (ፊተኛው አዳም፣ መሬታዊው ሰው) እንዲሁ ያልፋሉ፡፡ የሥጋና ነፍስ ማለፍ ደግሞ፥ እስከአሁን ወዳወሳነው ወደ ትንሣኤ ሥርዓት ነው፡፡ በትንሣኤ ዳግም የተገለጠው ማንነት፥ ከሞቱ በፊት የነበረው (አሮጌ) አይደለም፡፡ ይልቅ የመንፈስ ሕይወትን ያገኘ አዲስ ማንነት ነው፤ አዲስ ፍጥረት እንደማለት! ስለዚህ?
    
             "እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።" (1ኛ ቆሮ.15፥31)

ደ'ሞም በሌላ ስፍራ፥

             "እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና።" (2ኛ ቆሮ. 4፥9-11)

በእዛው መጽሐፍ ወረድ ብሎ፥

           "ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።" (ቁ.16)

ይሄ እንዲሁ የጽድቅ የኩነኔ ስብከት አይደለም፡፡ ወይም ያልተጨበጠ ተስፋ አሊያ ሩቅ ሕልም አይደለም፡፡ የሰዎች ሁሉ የባሕርይ መሻት በአንድም በሌላም ዘወትር በፍርሃት አስሮ ከሚያኖር፥ በሥጋ ልደት አማካኝነት ከገባንበት ከዚህ የድካም ዓለም አርነት መውጣት አይደል? ይሄ ታመነም አልታመነም የማንኛውም ሰው ውስጣዊ መቃተት ነው፡፡ የፍርሀቶች ሁሉ መንስኤ ደ'ሞ የሞት ነገር ነው፡፡ መታመምም፣ መራብም፣ መቸገርም፣.. የሚያስፈሩት በሞት ምክንያት ነው፡፡ የሥጋ ማንኛውም ዓይነት ጉስቁልና ሟች ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጳውሎስ ግን እንደዘበት "ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ" ይላል፡፡ ምን እያለ ነው?

አንባቢ ዕለት ዕለት ሞት የሚታወጅበትን እውነተኛ ምእመን አስታወስከው? በመጨረሻው ቀን እንዲነሣ ኪዳን (ቃል፣ ቁርባን) የተሰጠው? .. እርሱን እኮ ነው አሁን የምንነጋገር፡፡

እንዲህ ያሉ ምእመናን ሐዋሪያው እንደሚለው፥ የኢየሱስን ሞት በሥጋቸው ተሸክመው የሚዞሩ የዚህ ዓለም ባዕዳን ናቸው፡፡ ክርስትና ከተመሠረበት መነሻው ጀምሮ እስከዛሬ እንደዘለቀበት ጠቅላይ እውነታ፥ ሂደቱ በሞት መንደር መካከል ነው፡፡ መጥፋት፣ መሰደድ፣ ቦታ ማጣት፣ .. የዚህ፥ በተዋኅዶ ስም የተገለጸ የሰው ልጅ እውነት፥ ኑሮ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ መንግሥት፣ ከሃይማኖት እስከ መናፍስት ባለው ስብስብ፥ በትንሣኤ መሠረትነት ለታነጸው ክርስትና ሁነኛ ጠላቶች ናቸው *14፡፡ ያገኙት ያሳድዱታል፡፡ ከያዙት አያራሩለትም፤ ይገድሉታል፡፡

ይሁን እንጂ ከክርስቶስ እውነት የተነሣ ሊሞት የሚታወጅበት ምእመን፥ ከክርስቶስ ሕይወትነት የተነሣ ቢሞትም ይነሣል፡፡ በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለው ያለው ቃል በራሱ ሕይወት ነው፤ ስለዚህ በአማኙ ኑሮ ላይ በፊቱ ተገልጦ ይከወናል፡፡

የምእመን አነሣሱ እንደ አማሟቱ ነው፡፡ የገደሉ(በ)ትን ነገር፣ ሃሳብ፣ ግብ፣.. ያህል ይነሣል፡፡ ሞቶ በተነሣ ልክም የሞተው ከፍ ከፍ ወደማለት ለጥቆ ይሄዳል፡፡ ወደትንሣኤ ጥልቀት ይጠልቃል፡፡ የዚህ ዓለም ግንዛቤዎች ወደማይደርሱበት ጥግ ይገሰግሳል፡፡ እነሆ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም የሚያስብለው ይሄ ነው፡፡ /ዓለም በተለይ በዚህ ሰሞን 'ሊነጋ ሲል ይጨልማል'ን የስኬት ማበረቻ፣ የስሜት ማነቃቂያ አድርጋ የራሷን "ትንሣኤ" ትሰብካለች፤ በመጥፋት በኩል የመትጋት ሃሳቡ ግን፥ ሕይወት ሆኖ፥ ከዛሬ ፪ሺዎች ዓመት ጀምሮ ሰዎች በእውነት ኅልውና ሲመላለሱበት ቆይተዋል፤/

የዚህ ዘመን የእውነት ገዳይና አስገዳይ እንደቀደመው ብዙም በሥጋ ግድያ አያምንም (ከስሕተቱ ተምሮ ይሆናል¡)፡፡ ከዚህ ይልቅ የሞት ሥልጣኑን የሚነጥቀውን፣ እንደ ጳውሎስ 'ምን በሚያስፈራ ኑሮ ያባትለኛል?' ሊያሰኝ ትውክልት የሚሰጠውን አስተሳሰብ፣ መንፈስ (የውስጥ ሰውነት) ላይ ማተኮሩ አዋጭ ሆኖለታል፡፡ በሚከተለው መሠረታዊ ምክንያት፥

             "ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።" (2ኛ ቆሮ. 5፥16)

እንኪያስ እንደምን እናውቀዋለን? ጳውሎስ መልሱን ይቀጥላል፥

            "ልጆች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።" (ገላ. 4፥6)

ወሳኝ ነውና እንድገመው፥

           " ... በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።" (ሮሜ 8)