Get Mystery Box with random crypto!

ሐዋሪያቱ አስቀድሞ በቅፍርናሆም ይሄን ፍቅር አድምጠዋል፡፡ ኋላ ብዙም ሳይቆይ ኪዳን የሰጣቸው እርሱ | በማለዳ ንቁ !

ሐዋሪያቱ አስቀድሞ በቅፍርናሆም ይሄን ፍቅር አድምጠዋል፡፡ ኋላ ብዙም ሳይቆይ ኪዳን የሰጣቸው እርሱ ተይዞ ተገደለ፡፡ እነርሱም በሥጋ ተስፋ ያደረጉበት፣ የተለሙት ሁሉ አብሮ ሞተባቸው፡፡ ውስጥ ነገራቸውን ባማከለ አገላለጥ፥ ቃሉን በሥጋ የተረዱበት፣ የተረጎሙበት፣ የጠበቁበት አስተሳሰባቸው ከሞቱ የተነሳ ሞተ፤ ተለያቸው፡፡ የሞተባቸው መሪ እዚያው በተገደለበት ተቀበረ፡፡ በዚያው ትይዩ የትምህርቱ ሚሥጢር /በወቅቱ ያልተገለጠላቸው ሀሳብ፤/፣ በቁርባን የወሰዱትም ሥጋ ደም፥ ከሰውነታቸው ውስጥ ተቀበረ  *13፡፡ ደግሞ ከውስጥ ያለው በውጪኛው ይገለጻልና፥ በሚታየውም ረገድ በራቸው ዘግተው ከገፋቸው ዓለም ሸሽተው ተቀመጡ (ከዓለም ተቀበሩ)፡፡

ይህ እንደዚህ ሳለ፥ የሞተው እርሱ በአካል ተነሥቶ ወዳሉበት መጣላቸው፡፡ ስለዚህ በሞቱ የሞተባቸው ቃሉ፣ በመነሣቱ ተነሣላቸው፡፡ በመብል መጠጥነት የተዋኀደ ሥጋ ደሙ ከሰውነታቸው መቃብር ተነሣ፡፡ በተዘጋ በር አልፎ አግኝቷቸው ሲያበቃ፥ በተዘጋ ሥጋቸው አልፎ ረቂቅ ዕውቀታቸውን ከፈተው፡፡ የህሊናቸውን፣ የልቡናቸውን ሕዋሳት ሁሉ ከፈተላቸው፡፡ ስለዚህ ባሕርያቸው የትንሣኤውን ብርሃን በርግጥ አየ፡፡ ይሄ ብርሃን፥ በዚህ ይፋው ዓለም የሚያውቁት አልነበረም፡፡ ይለያል፡፡ አዲስ ነው፤ ልዩ ነው፡፡ እንዲህ መባሉ የፀሐዩን ብርሃን አያዩትም ለማለት አይደለም፤ እርሱን በሥጋ ዓይናቸው ያዩታልና፡፡ ለፀሐይ ብርሃን የሆናትን ብርሃን ግን ውስጠ ልቦናቸው ይመለከተዋል፡፡ አሁን፥ በሞትና በህይወት፣ ወደፊትና ወደኋላ፣ በሚታየው በማይታየው፥ ኅልውናን ያገኘ አዲስነት፥ ማንነታቸውን ተዋሕዷል፡፡ እነርሱ ከእርሱ የተነሣ አዲስ ሰዎች ሆነዋል፡፡ ግሩም ሰው ጳውሎስ፥

           "እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥" (ኤፌ 2፥14-15)


___
*8 - በእርግጥ አብዛኛው ሰው ፍጥረታዊ (ሥጋዊ ደማዊ ሃሳብ ያለው) ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአግባብ አስተምህሮትና ለሥነ ምግባር መግፍኤ በሚሆኑ ሕግና ትእዛዛት ሥር መኖሩ በቂው ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ትንሣኤ ሥርዓት የሚሻገሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብዛኛው፥ በጌታ ዓይን እንደታዩት፥ እረኛ እንደሚያስፈልጋቸው ተበታትነው ያሉ የበጎች መንጋ ናቸው፡፡ እውነት ከፊት እየቀደመ ተከተሉኝ የሚላቸው አሉ፤ ደ'ሞ የሚያስፈልጋቸውን በረከት ወስደው ወደየቤታችሁ የሚባሉ አሉ፤ ዋናው ነገር በክርስቶስ አባት ቤት (በጠቅላዩ ሃሳብ ዘንድ) ያሉት ክፍሎች ሰፋፊና ብዙ መሆናቸው ነው፤ ስለዚህ ለሁሉም የተዘጋጀ በቂ ማረፊያ አለ፡፡

*9 - እዚህ'ጋ ወንጌል ሲባል ሃይማኖታዊ የሆነው ገጽና ልማድ ብቻ የሚታያቸው አሉ፤ ደ'ሞም እስከአሁን ሰፍቶ እንዳለው ግንዛቤ ከዚህ መልኩ ባሻገር ሊታይም "አይችልም"፤ ይሁን እንጂ ወንጌል፥ የጽዮን ሕግ፥ የሰው ልጆች ሁሉ ምጥ ፍለጋ ናት፤ የትኛውም ዓይነት ዘውግ ያላቸው በጎ፣ ኃያልና ሰዋዊ ታላላቅ ሃሳቦች የወንጌልነት አንድምታ አላቸው፡፡

*10 - ይሁን እንጂ አስቀድሞ እንዳልነው፥ መሬት በረገጠው እውነታ ይሄ አስተሳሰብን የማንቃት ደረጃ ሆን ተብሎ ማዕቀብ ወድቆበታል፤ ወጥና ልሙጥ የሆነ ሲያክልም ቁንጽል አእምሮአዊ አተያየት በዓለሙ ሕዝብ የጋራ ናላ ላይ እንዲሰፍን በላይኛዎቹ ይፈልጋል፡፡

*11 -  ለማሳጠር ያህል ቆርጠን እንጂ፥ በርግጥ ገና ከጅምሩ የሚወለደው እንዳይፀነስ ቀድሞም ይታወጅበታል፤ ጳውሎስ እንዳለ በተለይ በመጨረሻው ዘመን ለዚህ ፅንስ ምክንያት የሚሆነው መንፈሳዊ ጋብቻ ሆን ተብሎ ይሰነካከላል፡፡

*12 - የሚገርመው ከሰባቱ አንዱ በሃይማኖቱ ክፍል ብርቱ ስፍራን መያዙ ነው፤ እንደውም ከስድስቱ ይሄኛው ይከፋል፤ ግብዝነትና ቅናት በዚህ ቦታ የሚቆምባቸው ሁለት እግሮቹ ናቸው፤ ራስ ቅሉ (ማሰቢያው) ሐሰት ይሆናል፡፡

*13 -  ቅዳሴ፥ በአምልኮ ሥርዓቱ ጠቅልሎ ይህንን ዕለት ዕለት ያውጀዋል፡፡ በቁርባን የሚሰጠው ሥጋ ደም ነፍስ የተለየው መለኮት ያልተለየው ነው፡፡ ወይም ሥጋ ደሙ የተሰጠው በሞቱ ነው፤ ስለዚህ ሕብሥትና ወይኑ ይሄን ሞቱን በምእመን ውስጥ ያውጃሉ፤ ሥጋ ደሙ በምግብና መጠጥነት በሰውነት ይቀበራል፡፡


ይቀጥላል ...

@bemaleda_neku