Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ ... ምንም እንኳ ለሃይማኖት፥ ትምህርት፣ ሕግጋትና አምልኮት መሠረቶቹ ቢሆኑም፥ ለሁለቱ | በማለዳ ንቁ !

የቀጠለ ...

ምንም እንኳ ለሃይማኖት፥ ትምህርት፣ ሕግጋትና አምልኮት መሠረቶቹ ቢሆኑም፥ ለሁለቱ መሠረታዊያን ደግሞ ሥርዓተ አምልኮት መሠረታቸው ነው፡፡ በግልጽ አገላለጽ አስተምህሮትና ሕግጋት ምንጫቸው ከአምልኮት ነው፡፡

አምልኮት መንፈሳዊ ክንውን እንደመሆኑ፥ ከመንፈሳዊ ዓለም ጋር የሚደረግ ግንኙነት ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት አምልኮ ራሱን የቻለ መንፈሳዊ ትስስር ይኖረዋል፡፡ ከሌለው ልማድ ወደመሆን ይወርዳል፡፡ አምልኮት በሚፈጥረው ግንኙነት የተነሣ፥ ለአስተምህሮትና በአስተምህሮቱ ዙሪያ ለሚኖሩ ሕግጋት ምንጭ የሚሆኑ ሀሳቦችን ከማይታየው ወስዶ ያመጣል፡፡

በአስተምህሮት መንገድነት፣ በሕግጋት ጠቋሚነት እየተጓዘ ያለ ምእመን ታዲያ፥ የሂደቱን ዓላማ የሚቀርጸው፣ ወደ መዳረሻው በሚራመድበት ጉዞው የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች የሚያልፈው፣ እንዲሁም በአስተምህሮት በኩል የተቀበለውን ቃል በጊዜው ውስጥ የሚተረጉመው በአምልኮት ረዳትነት ነው፡፡ መንፈሳዊ ትስስር መፍጠር የሚችሉ መንፈሳዊ ልምምዶችን እየፈጸመ ካልሄደ ወደ ቀጣዩ የዕድገት ክፍል መዝለቅ አይችልም፤ ይልቁን ዝንት ዓለሙን ከመምህራንና መጽሐፍት እየወሰደ፣ ከሕግና ትእዛዛት በታች ሆኖ ሊወሰን ይገደዳል፡፡ *8

ወደ ሥር ነገራችን ስንመለስ፥ በአስተምህሮትና ሕግጋት ዕድገቱን የቀጠለው ምእመን በአምልኮት በኩል እየተረዳ፥ ባገኘው ማስተዋል ልክ በእምነት የሰማቸውን ቃላት እንደገና በውስጡ ይሰማቸዋል፡፡ አስተሳሰቡን በወንጌል ቅኝት ይዋጃል *9፡፡ ፈጣሪውን፥ እንደሚነገረው ብቻ (ከውጪ፣ በሌሎች) ሳይሆን እንደሚያስበውም (ከውስጥ፣ በራሱ) ሊያገኘው ይጥራል፡፡ እውነትን ከወረቀት ብቻ ያይደል ከሕይወትም ሊያነባት ይጀምራል፡፡ አሜን ያለውን የእምነት ቃል፥ በራሱ ማውጣት ማውረድ ውስጥ በኑሮው አሚንነት ይፈትሻል፡፡ በሃሳብም፣ በሕይወትም መውጣት መውረድ ዕለቶቹን ይመራል፡፡ *10

በቤተክርስቲያን ዋነኛውና ወንጌሉን ህይወት የሚሰጠው ሥርዓተ አምልኮ ቅዳሴ ነው፡፡ ቅዳሴ በአጭሩ ወንጌል ተተርኮ ማለት ነው፡፡ እዚያ ሥርዓት ውስጥ በተለያዩ መሥዋዕቶች ቃሉ በመንፈስነት ወደተሳታፊው እየደረሰ ይቆይና በመጨረሻም ሁላቸውን መሥዋዕቶች የሚጠቀልላቸው መሥዋዕት ይቀርባል፤ ይኸውም ሰማያዊው ማዕድ - ቅዱስ ቁርባን ይባላል፡፡

ቅዱስ ቁርባን የሐሙስ ሥርዓት ነው፤ ፍጻሜውን ያገኘው ግን በአርብ ዕለት ነው፡፡ እንካችሁ የሚፈስ ደሜን ጠጡ እያለ የወይኑን ጽዋ ጌታ ለወዳጆቹ ሐሙስ ቢያድላቸውም፥ ደሙ ግን የፈሰሰው አርብ ላይ ነው፡፡ አርብ ነገረ መስቀሉ ነው፡፡ ወይም ሞቱ ነው፡፡ አስቀድመን እንዳወሳነው ደ'ሞ በዚህ ዓለም ተገልጦ የሚኖረው የሥጋ ኅልውና፥ ከልደት እስከ ሞት ይጓዛል፡፡ ይሄም ነው ከሴት የተወለደ "ሁሉ" ሞትን ያያል የሚያሰኘው፡፡ ሰው ሲወለድ ሞትንም ይዞት ይወለዳል፡፡

በምእመንነት ያለው ይህ ነው፡፡ በእምነትነት ተጸነሰ ያልነው ቃል፥ በተቀበለው ውስጥ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሞት ይከተለዋል *11፡፡ ቃሉ ሕይወት ነው የተባለውን አልረሳንም፡፡ ሕይወትነቱም የኢየሱስ በመሆን ነው፡፡ እርሱ ደ'ሞ በመዋለ ሥጋው ሞት ከብቦት ነው የኖረው፡፡ በመጨረሻ በመስቀል ተገደለ፤ ከነበረበት ትውልድ ተወገደ፡፡

አማኝም ተቀብሎ በውስጡ ካዋሐደው በሞት መካከል ከኖረ ከዚህ ቃል የተነሣ ሞት ከብቦት ይኖራል፡፡ በትምህርት መግቦት፣ በሕግጋት ሞግዚትነት የሚያድገው ሐዲስ ባሕርይ፥ ሲሆን እንዳይወለድ፥ ቢወለድ ከዚህ ዓለም እንዲወገድ፥ የግድያ ትእዛዝ ከየአቅጣጫው ይወጣበታል፡፡ ስላንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንግዲህ ይኸው ነው፡፡ በማይታየው ሆነ በሚታየው የሚገለጽ የጥፋት ስደት እውነተኛ ምእመንን ያሳድደዋል፡፡ እንዲጠፋ ይፈርድበታል፤ ዐወጅ ይነገርበታል፡፡

ዮሐንስ በራእዩ አንዲትን ሴት ዘንዶው ሲያባርራት፣ ሳይዛትም ሲቀር ከዘርዋ የሚወለዱትን ሊያገኛቸው ሲጣጣር ተመልክቷል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ትርጓሜ፥ ሴቲቱ በሚሥጢር ቅድስቲቱ ወልድ ናትን እንይዛለን፤ ዘር የሚሰኘው ደ'ሞ ቃል እንደሆነ ራሱ ተርጉሞልናል፡፡ (ማቴ. 13፥18) ስለዚህ በቃሉ ዘርነት ሊወለዱ የተጸነሱትንና የተወለዱትን ሁሉ ሊበላቸው በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ይቆማል *12፡፡ ክፉው ወደ ስብዕናቸው ፍጻሜ ሊደርሱ እየተጉ ያሉትን በሚታየው (የሥጋ ነገራቸውን) ይዞ ይገድላቸዋል /ለዚህ ነው አይደል 'ሥጋችሁን የሚገድሉትን.. ' የሚለው?/፡፡ የራሱ ከሆነው ሁሉ እየፈለገ ያጠፋቸዋል፤ በዚህ ሳይበቃው ዙሪያቸውን ጭምር ተከታትሎ ያጠፋል፡፡ አንተም ከነርሱ አንዱ ነህ እያለ የተጠጓቸውን ያስጨንቃል፡፡ እንዳልነው ይሄ በክርስቶስ ሕይወት ንጣፍነት ለሚመላለሱት የሆነና የሚሆን ኑሮ ነው፡፡ ሆኖም ግን ስለ ቁርባን ደ'ሞ በአንድ ቦታ እንዲህ ይነበባል፥

            "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።" (ዮሐ. 6:54)

በመጨረሻው ቀን?

በሥጋ ወራት ላለ ማንም ሰው መጨረሻ ቀኑ ዕለተ ሞቱ ናት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ከታየ፥ የመስቀል ሞቱ የዚህ ዓለም መጨረሻው ነው፡፡ ይሁን እንጂ "መጨረሻው" የሆነ ሥጋን እንደገና በትንሣኤው አስጀምሮታል (አድሶታል)፡፡ እንዲሁ፥ 'ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ፥ ቢሞትም እንኳ እንደኔ ይነሣል' የሚል ቃሉን ደ'ሞ በእርሰነቱ ላሉት ሰጥቷል፡፡