Get Mystery Box with random crypto!

በመጽሐፍ ታሪክ፥ በናዝሬት ገሊላ ከተማ የተፈጸመውም ይኸው ነበር /የሥጋን እያወራን ነን፤/፡፡ ድን | በማለዳ ንቁ !

በመጽሐፍ ታሪክ፥ በናዝሬት ገሊላ ከተማ የተፈጸመውም ይኸው ነበር /የሥጋን እያወራን ነን፤/፡፡ ድንግል ማርያም "እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" ካሰኛት ጽሩይ እምነት ባሻገር፥ ቃልን የምትቀበልበት ሌላ መንገድ አልነበረም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ መሬት ያለ ዘር የምታፈራበትን ጥበብ ቅድሚያ በእምነት እንጂ በምን ይቀበሉታል? መልአኩ ወደ እርሷ መጥቶ 'ተቀበይው' ያላትን ቃል በእምነት ተቀበለቺው፡፡ በተቀበለች ቅጽበት፥ ጸነሰቺው፤ ወለደችውም፡፡ ፊተኛው ሂደት፣ የዚህ ዓለም ጉዳይ፣ የኢየሱስ ልደት ይሄ ነው፡፡

የተወለደው ልጅ ትምህርት እየተማረ ማደጉን ይቀጥላል፡፡ በወላጆቹና በአምላኩ ፊት በሥጋና በዕውቀት (በነፍስ) ከፍ ከፍ ይላል፡፡ የዕድገቱን ደረጃ በመቀጠል ወደሚቀጥለው ይጓዛል፡፡ እስከአሁን በዕውቀትነት ከውስጡ የኖሩትን ሃሳቦች ራሱ ማብላላት፣ ማሳመክ ይጀምራል /አሁን አሁን እንኳ ይሄ የእድገት እርከን ታላቅ ማዕቀብ ተጥሎበታል፤/፡፡ ለምሳሌ እናቱን፥ እስከዛሬ ስለ እርሷ ከራሷና ከሌሎች በተቀበለው ዕውቀት በኩል ሲያገኛት ቢቆይም፥ በራሱ ማውጣት ማውረድም ውስጥ ያገኛት ይጀምራል፡፡ ይሄ ጊዜው፥ ነፍስ አወቀ (አስተሳሰቡ ነቃ) የሚባልለት ዕድሜው ነው፡፡ በመሆኑ ክፉና ደጉን ራሱ በራሱ ትርጓሜዎች መለየት ይጀምራል፤ ፍላጎትና ጠባያቱን እንደ አተያየቱ ይቀርጻል፤ ተሠርቶ የመጣ ስብዕናውን በራሱ አሠራር ያጸናል፤ ያፈርሳል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ሳለ፥ አስቀድሞ በእምነት ከውጪ ያገኛቸው ዕውቀቶች፥ ማንጸሪያዎቹና ማሰቢያዎቹ ሆነው ያገለግሉታል፡፡ /አስተዳደግ እጅጉን ወሳኝ ነው የሚባለው ለዚህ ነው አይደል? ወላጆች ከወለዳችሁ አይቀር .. /፡፡

የተዋህዶ ሃይማኖታዊው አካሄድ ወይም ክፍል (ከወንዙ በፊት ያለው የሕይወት ዛፍ አውድማ) የምንለው፥ እነሆ ይሄ ከላይ በሥጋ ልደት አማካኝነት የዳሰስነው በዚህ ዓለም ስላለን ብቻ የምናውቀውን ሂደት ነው፡፡ አንድ አማኝ፥ "እንደ ቃልህ ይሁን" እያለ ቃልን በንጹሕና የዋህ እምነት ከመቀበል ይጀምራል፡፡ ተወላዲ ቃልን በእምነት ተቀበለው ማለት ይወለድ ዘንድ ጸነስነውም ማለት ነው /ድንግል ማርያምን ያዩአል፤/፡፡ ምእመን የሚጸንሰው በልቡ ነው፤ ቃልን በእምነት መቀበል የልብ ነውና፡፡ ጽንስ ደ'ሞ እስከ ጊዜ ልደቱ ድረስ ያድግ ይለወጥ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡ እነሆ ከውስጣችን በእምነት ጽንስነት የተቋጠረ ቃል፥ ትምህርትን ከመጽሐፍትና መምህራን እየተመገበ ያድጋል፡፡ ከፍ ከፍ ይላል፡፡ ዕድገት ደ'ሞ ወዳስፈላጊው ደረጃው እንዲደርስ ጥበቃ ያስፈልገዋል፤ መፈጸም የሚያስፈልጉና የማያስፈልጉ ነገራት ይኖራሉ፡፡ ሕግና ትእዛዛት እዚህ ይመጣሉ፡፡ አድርግ አታድርግ ወደተፈላጊው ስፍራ የሚደረገውን ጉዞ አቅጣጫ የሚያሲዙ ጥቆማዎች ናቸው *5፡፡ እና በአስተምህሮቱ መግቦት የሚያድገው ልጅ፥ አስተምህሮቱን መሠረት ባደረጉ ሕግ ትእዛዛት እየተመራ ከፍታውን ይቀጥላል፡፡

ምእመን በአስተምህሮት መልክነቱ እየወሰደ የሚያሳድገው የእውነት ቃል፥ ጌታ እንዳለው ለሚሰሙት ሕይወትም መንፈስም ነው *6፡፡ ሕይወትነቱ የኢየሱስ ክርስቶስ በመሆን ነው፡፡ ስለሆነ ቃልን ሰምተው እንደሰሙት ባዩት ልክ፥ በርሱ ኑሮ የሆነው በአማኙም ኑሮ ይሆናል፡፡ ይሄ በአማናዊ ትንሣኤው ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ከሞት ሲነሣ ከሞቱ በፊት የኖረው ጭምር ነው አብሮ የተነሣው፡፡ ስለዚህ የሕይወተ ሥጋው ጉዞ፥ ከተያዘበት ጊዜ አጥር ውጪ የመሆን ሕያውነትን ነሥቷል፡፡ እንኪያስ ለሚቀበሉት ሁሉ፥ በስሙ ለሚያምኑት፥ የኢየሱስ ኑሮዉ ትናንት ያለፈ ታሪክ ሳይሆን አሁን የሚያዩት ህይወት ሆኖ በፊታቸው እየተገለጠ ይሄዳል *7፡፡ ወንጌልን በመረጃነት ለሚያጠናት ድሮ ናት፥ እንደማኅተም በልቡናው ክንድ ለሚያስራት ግን ዘንድሮ ናት! ለዚያውም አሁንነት ያላት ዘንድሮ!

__
*4 -
ክርስትና፥ በተለይ በሩቅ ምሥራቁ ዓለም ውስጥ ከሚዘወተሩ የዳግም ልደት (reincarnation) ሃሳቦች የሚለይበት አስተምህሮት ይሄ ነው፤ በዳግም ልደት በኩል የሚከሰተው ሌላ ማንነት ሳይሆን በቀዳሚው ልደት የመጣው ራሱ ነው ይላል፡፡ ኢየሱስና ኒቆዲሞስ ሲጨዋወቱ፥ ኒቆዲሞስ ይሄ ገብቶት ይመሰላል "እንዴት ሰው ወደእናቱ ማኅፀን ዳግመኛ ተመልሶ ሊወለድ ይችላል?" ሲል የጠየቀው፡፡ ክርስትና በሥጋ ልደት የተገለጠው አካላዊ ማንነት ወደ መንፈስ ልደት ይሻገራል እንጂ በሥጋ እንደገና አይወለድም እያለ ያስተምራል፡፡ የሩቅ ምሥራቅ እምነቶች በበኩላቸው ወደ ሌላ አካል፣ ወደ ሌላ ፍጡርነት በመቀየር ዳግም ልደት ይከናወናል ይላሉ፤ ከሥጋ ወደ ሥጋ አልሸሹም ዘወር አሉ ነገር፡፡

*5 - ህግና ትእዛዝ ግብ አስፈጻሚ ባለተልዕኮዎች መሆናቸው ተረስቶ በራሳቸው ግቦች ሆነው ካረፉ ትንሽ ሰነባብቷል፡፡ በዛሬይቱ ዓለም በሃይማኖታዊ ተቋማትም ሆነ በሌሎቹ ዘንድ፥ ለአንድ ሃሳብ የመጨረሻ ፍጻሜ ሲባል የተፈቀዱ ትእዛዛትና የተከለከሉ ህግጋት የሃሳቡን ፍጻሜ ከጥግ የሚያደርሱ መሆናቸው ተዘንግቶ ነገር ዓለሙ ሁሉ ደንቦችን ብቻ የመከተል ያለመከተል ግብዝነት ሆኗል፡፡ ህግ ምሪት ናት፤ በሙሴ ትወከላለች፡፡ ሙሴ ደግሞ አገልግሎቱ ወደ ከነዓን ነው፡፡ ከነዓን የሌለው ሙሴ የለም፡፡ አሁን ግን የሆነው፥ ሙሴን የምንከተለው በከነዓን ምክንያት መሆኑ ቀርቶ ትክክልነት ሙሴ በሄደበት መሄድን ማስመሰል "ስለሆነ ነው"፡፡ ህግ ያለ አንዳች ፍጻሜ ወግ ብቻ ናት፡፡ ተማሪ አታጥና እና አጥና በሚሉ ጥንድ መርሆች ወደፊት የሚሄደው ላሰበው ውጤት ካልሆነ ምን ጥቅም አለው? በተለይ ሃይማኖቶች ያው እንደምናየው የወግ መናህሪያ ሆነዋል፡፡ ጉዳዩ፣ ፍጻሜው፣ አድራሻው በውጪም በውስጥም ወደምትገለጽ ልዩ መንግሥት፣ ጠቅላይ ሥርዓት፣  ከምንም በላይ ምሉዕ ወደ ሆነ ፍቅር መግባት መሆኑ ከነአካቴው ጠፍቶ፥ በየዓመቱ ዓሣ ይበላል አይበላም በሚል መሰል የተራ ተራ ሙግት ውስጥ ለዝቅጠት መቧጠቅ ሆነ፡፡ 

*6 - ይህ ቃል፥ ወንጌለ እግዚእ ነው፤ ሌሎቹ አስተምህሮቶች ሁላቸው በወንጌል ማዕከላዊነት የተያዙና በዙሪያው የሚዞሩ ናቸው፡፡

*7 - ጳውሎስን "ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤" ያስባለው ይህ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ.15፥14) የእርሱ የሥጋው ወራት ኑሮ እንደማንኛውም ሰው በሞት ተደምድሞ ቢሆን ኖሮ፥ ነገሩ ከአግራሞት ባሻገር ምንም ነበር፤ ጠቢቡ ከፀሐይ በታች ሁሉ የከንቱ ከንቱ ነው ያሰኘው፥ ነገር ሁሉ በሞት ስለሚጠናቀቅም አይደል? በዓለም ውስጥ ብዙ ለሰው ልጆች የሚሆኑ ጠቃሚ ሃሳቦችን፣ ሥራዎችን ለየትውልዳቸው የሰጡ ብሩህ አእምሮዎች ነበሩ፤ ይኖራሉም፡፡ ይሁን እንጂ ያለፉቱ በሞት በመሸነፋቸው ምክንያት፥ ያሉትም ቢሆኑ በሥጋ ሕግ ከመያዛቸው የተነሣ፥ የህይወታቸው ውጤት በሆነ ሥራቸው መገልገል እንጂ በህይወታቸው መስመር ዘልቀን፣ በኑሮአቸው ጊዜ ገብተን የኖሩትን መኖር አንችልም፡፡ የልባቸውን ፍሬ እንጂ ልባቸውን ማግኘት አንችልም (የክርስቶስን ልብ ግን እንችላለን)፡፡ በሞትና በሥጋ ሕግ ተዘግተዋልና፡፡ የማርያም ልጅ የተለየው ይህን ዝግ ማኅተም በመክፈቱ ነው፡፡ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት የተዘጋውን የኅልውና ቁልፍ ከፍቶት፥ በርሱ የኑሮ ጊዜ፣ የህይወት መስመር ውስጥ ገብተን የኖረውን እንድንኖረው ሆነልን፤ ታዲያ ወደርሱ ዓለምነት ማለፊያ በሩ ዳግም ልደት ነው፤ ለዚህ ልደት መጸ'ነሻዋ (ጥምቀት)፣ መጋቢዋ (ቁርባን፣ ትምህርት) እና መውለጃዋ (የመስቀል መከራ) መንፈሳዊቷ ማኅፀን ደግሞ ወንጌል ናት፡፡

ይቀጥላል ...

@bemaleda_neku