Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ ..                'ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ'፡፡ | በማለዳ ንቁ !

የቀጠለ ..

               "ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ"፡፡ (ዮሐ. 1፥14)
            
ይሄ የአንድ ምእመን ኑሮ ነው፡፡ አንዳንዶች ምእመናን ሲሰበሰቡ ኅብረት ይፈጥራሉ፤ በዚያም ኅብረት በኩል ወደ አንድነት ያድጋሉ፤ ወደ ቤተክርስቲያንነት እንደማለት!

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ሙሉውን የተዋኅዶ ጉባዔ የምትኖርበት መክሊት አላት፡፡ ቃል ሥጋ ሆነ ብላ የጀመረቺውን ጉዞ በጸጋና እውነት ሙላት ትፈጽማለች፡፡ ከገሊላ እስከ በዓለ ኀምሳ የሚረዝመውን የሕይወት፣ የእውነት መንገድ ትሄድበታለች፡፡ ምእመንም እንዲሁ እንደ ልቡ ርዝማኔ ይጓዛል፡፡ መንገዱን ሙሉውን ከተጓዘ በጉ በሄደበት ሄዷል ማለት ነው፡፡ እርሱ የ144ሺው ልዩ ትውልድ አካል ነው፡፡ (ዮሐ. 14፥3)

ጉዞው በመካከሉ ላይ ወንዝ እንደሚገጥመው አውስተናል፡፡ ወንዙን በክርስቶስ ሕይወት ስናየው የመስቀል ሞቱ ነው፡፡ ኢየሱስ የተጎነጫትን ይህቺ ጽዋ ለተቀበሉት ሁሉ አሳልፏልና፥ ከኋላ የሚከተሉ ምእመናንም ከጽዋዋ ይጎነጫሉ፡፡ ልደቱን፣ ዕድገቱን፣ አገልግሎቱን በሕይወታቸው እያዩ ይቆዩና ሞቱንም እንዲሁ ያያሉ፡፡ በርግጥ የሞት ሽታ የሚከባቸው ከቤተልሔም ጀምሮ ነው /እንደተወለደ ስደት እንደተከተለው ያስቧል፤/፡፡ ይሄ፥ ቀዳማዊው፥ በጉባዔ "አምላክ ሰው ሆነ" ሲል መሠረቱን ያኖረው፣ በዓለማት አንጻር "ከሚታየው ወደማይታየው" የሚወስደው፣ በአንድ ሰው አእምሮና ልቦና ዐውድ ደግሞ "ከውጪያዊ ወደ ውስጣዊ ዕውቀት" ሊጠልቅ የሚጓዘው፥ ሃይማኖታዊው ሂደት ነው፡፡

ሃይማኖት በዋነኝነት በሦስት ነገሮች መልኩ ይገለጻል፡፡ አንድን ሃይማኖት ሃይማኖት የሚያሰኙት እነዚህ ሦስቱ የተሟሉ ሲሆኑ ነው፡፡ እነርሱም አስተምህሮት፣ ሕግና ትእዛዛት እና አምልኮት ናቸው /ሦስተኛውን መንፈሳዊ ሰውም ይጋራዋል፤/፡፡ እነዚህ ሦስቱ ለሃይማኖት መሠረቶቹ ናቸው፡፡ ያለነርሱ ሃይማኖት መኖር፣ መቀጠል አይችልም፡፡ አስተምህሮት ከሌለ፥ ሃይማኖት ሊታወቅ ብሎም ሊስፋፋ አይችልም፡፡ አድርግና አታድርግ የሚላቸውም ደንቦች ከሌሉት፥ መስመር እንዲሁም ግብ አይኖረውም፡፡ በመጨረሻ ኅልውናውን የሚያሳርፍበት፣ ከማይታየው የሚገናኝበት፣ በአስተምህሮትና በደንቦች ለምእመናኑ የሚያቀብለውን የሚያገኝበት፣ የሚያሠርጽበት ሲልም በኑሮና መንፈሳዊ ኃይል የሚተረጉምበት የአምልኮ ሥርዓት የግድ ያስፈልገዋል፡፡

በአስተምህሮቱ ዘርፍ ቅዱሳት መጽሐፍት ትልቁን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ሕግና ትእዛዛትም በመሠረትነት ከነኚሁ መጽሐፍትና በመጽሐፍቶቹ የክብር ደረጃ ባሉ ሰዎች ከተሰጡ ደንቦች ይወጣሉ፡፡ በሥርዓተ አምልኮት በኩል፥ መሥዋዕት፣ ንዋየ ቅዱሳት፣ መንፈሳዊ ልምምዶች ተጠቃለው ይገኛሉ፡፡ ሃይማኖት ከብዙ በጣም ጥቂቱ ይሄን ይመስላል፡፡

ሃይማኖት በመንገድነት አብዛኛውን ይመሰላል፡፡ መንገድ ከሆነ አድራሽ እንጂ አድራሻ አይደለም ማለት ነው፡፡ መንገድ ሂደት ነው፤ በራሱ ጫፍ አይደለም፡፡ መንገድ ካለ መጓዝ አለ /መንገዱ በእምነት የሚሄዱበት ነው፤/፡፡ አስተምህሮት፣ ሕግጋትና የአምልኮ ሥርዓት ጉዞዎች፣ ወሳጆች ናቸው፡፡

ታዲያ 'ሁሉም' ሃይማኖቶች ወሳጅነታቸው ከሌሎች ዓለማት ጋር በጥብቅ ይገናኛል፡፡ እነ 'ገነት፥ መንግሥተ ሰማያት፣ ሲዖል፥ ገሀነም' ዋናዎቹ የተስፋ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በመሆኑ የአንድ መደበኛ ባለ ሃይማኖት ሰው የመጨረሻ ሃሳብ፥ በማይታዩቱ ዓለማት ዕጣ ፋንታ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ እስቲ በተዋሕዶ ቤት ያለን የሃይማኖት ዝርዝር ገጽታ ለመቃኘት እንሞክር፡፡

በተዋሕዶ፥ ከጽንሰት እስከ ሞት ያለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመንበትን ክፍል፥ ሃይማኖታዊው ክፍል ነው፡፡ የዚህ ሃይማኖት አስተምህሮት፣ ሕግጋትና አምልኮት በቃል ላይ መሠረቱን ይጥላል (መሥራቹስ አካላዊ ቃል አይደለ?)፡፡ ባለ ቃሉ ስለ ከፍተኛው ዓለም ሲናገር ፦

            "እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት (የማይታየውን ዓለም) ሊያይ አይችልም .. ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። .. ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?" (ዮሐ. 3)

ዳግም ልደት ለአድራሻው ታላቅ ዓለም፥ እንደ ይለፍ ፈቃድ ሆኖ በዚህ ንግግር ተገልጿል፡፡ ዳግም ልደት ስያሜውም እንደሚገልጠው እንደገና መወለድ ነው፡፡ ይህ ሲብራራ ማለት፥ ሰው እንደገና ሲወለድ፥ በሥጋ የተወለደበትን የመጀመሪያ ልደት አስጠብቆ ወደ መንፈስ ልደት ይሻገራል (ይታደሳል) እንጂ፥ ተለውጦ ሌላ ሰው አሊያ ፍጡር አይሆንም /የተነሣው ክርስቶስ የሞተው ኢየሱስ ነውን አስታወስክ?/ *4፡፡ ወይም 'እንደገና' ከተባለ፥ በሥጋ ልደት የታየው በመንፈስ ልደትም ላይ ድጋሚ ይታያል ማለት ይሆናል፤ ወይም ምድራዊውና ሰማያዊው አወላለድ በይዘት አንድ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምድራዊው በደንብ ከገባን ሰማያዊውም የሚገባን ነውና ለመንፈሳዊው አወላለድ መረዳት የሚሆነንን ሥጋዊውን እንየው፡፡

የሥጋ ማንኛውም ልደት፥ ማኅፀን እና ጊዜ የሚባሉ ዋነኛ ነገሮች አሉት፡፡ ሰው፥ በእናቱ የማኅፀን ጎዳና አልፎ፥ በልደት በኩል ወደ ጊዜ ይገባል፤ በሰማይ ብርሃናት የሚሰላ ዕድሜውን ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ የኢየሱስን ዕድሜ 33 ዓመት ብለን የቆጠርነው፥ የቤተልሔም ልደቱን አንድ ብለን ጀምረን ነው፡፡ ይሄ ባሕርያዊ ህግ ነው፡፡ በማኅፀን ይቋጠራል፤ በልደት አድርጎ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፤ የመምጣቱም መነሾ የጊዜውን ስፍር ያስጀምራል፡፡ ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ሁሉ፥ እንዲህ ይመላለሳል፡፡

እንዲሁ በመንፈስ ልደትም ማኅፀንና ጊዜ አሉ፡፡ ሰው ዳግም በሚወለድበት በመንፈስ ማኅፀን ተጸንሶ ሲያጠናቅቅ፥ በዳግም ልደት አልፎ ወደ ሌላኛው ዓለም ይሄዳል፡፡ ወይም የመንፈስ ልደት በሚያዘልቀው የጊዜ መስመር ውስጥ ይገባል፡፡

ልደት፥ የተወላጁ አካል ወደ ጊዜ መግቢያ በር ነው፡፡ ሃሳቡን ወደ ሥነ ፍጥረት ብንስበው፥ አንድ ነገር ተፈጠረ ማለት ወደ ጊዜ ገባ ማለትን ያመጣል፡፡ የእግዚአብሔር የመፍጠር ነገር፥ በፍጥረታት የመውለድ ነገር ተንጸባርቆ ይታያል፡፡ ፈጣሪ በእናትነት አንቀጽ የሚገለጽበትም ዋና ምክያት ይሄ ነው፡፡ ለማንኛውም ልደት ካለ፥ የሚገባበት ጊዜ (የሚዘለቅበት ዓለም) አለ፡፡

እንደሚታወቀው፥ በሥጋ ወደዚህ ዓለም የተወለደ ልጅ ዕውቀት ይዞ አይወለድም፡፡ ቃል (ቋንቋ) የለውም፡፡ ቃል ከሌለው ሃሳብ የለውም /ሃሳቡን አይገልጽም የሚለው ይመረጣል፤/፡፡ ውጨኛውን ዓለም የሚያውቅበት ዕውቀት ወደ ውስጡ አልገባም፡፡ ስለዚህ ቃል ከውጪ ወደ ውስጥ ይነገረዋል፡፡ ከቅርቡ ጀምሮ ያሉትን አንድ በአንድ እያገናዘባቸው እንዲሄድ ትምህርት ይሰጠዋል፡፡ እርሱም በእምነት እየተቀበለ ዙሪያውን እየተረዳ ያድጋል፡፡ ከእምነት በቀር ሌላ ቃልን የመቀበያ መንገድ የለውም፤ ለምሳሌ አንዲቱ ሴት እናትህ ናት ሲባል እናትነቷን በእምነት ተቀብሎ ያድጋል፡፡