Get Mystery Box with random crypto!

ከዚያ ለ40 ቀናት ያህል በትንሣኤው እየተገለጠ በመመላለስ ካገኛቸው ኋላ፥ ወደ ዕርገቱ ሥርዓት (ወ | በማለዳ ንቁ !

ከዚያ ለ40 ቀናት ያህል በትንሣኤው እየተገለጠ በመመላለስ ካገኛቸው ኋላ፥ ወደ ዕርገቱ ሥርዓት (ወደ ዐሥሩ ቀናት) ቀጥሎ ሄደ፡፡ "ወደ አባቴ እሄዳለው" እንዳለ፥ ወደ አብ ከፍ ከፍ አለ፡፡ እነርሱ ውስጥ በቃል፣ በሥጋ ደሙ የተነሣላቸው እርሱነቱም በዚያው አንጻር እንዲሁ ከፍ ከፍ አለ፡፡ ወደ ባሕርያቸው ጥልቀት ዘለቀ፡፡ ቃል ወደ ወላጁ ወጣ፡፡ የቃል ወላጅ ልብ (አብ) ነው፡፡ በነርሱም ያለ የቃል ባሕርይው ወደ ልባቸው ምስጠት ገባ፡፡ ስለዚህ ጠቅላዩ ሃሳብ ታሰባቸው፤ ልዑሉን ፈቃድ ፈቀዱት፤ የመጨረሻው ጽሩይ ድምፅ ኅሊናቸውን ሞላ፤ የምልዓትን አስተሳሰብ በአርምሞ ከበሩበት፤ በመቼት ባልተገደበ እንዲህ እንዲያ ተብሎ በፍጡር ቋንቋ በማይገለጽ ጽማዌ ለ10 ቀናት ያህል ቆዩ፡፡ /ወይንም 10ሩን የጽድቅ (የመርቀቅ) ማዕረጋት ደረጃ በደረጃ ተመለከቱ፤/

በ10ኛው ቀን ቅዱስ አካላዊ መንፈስ ከሁሉ አባት ዘንድ ወረደ *3፡፡ በነርሱ ያለውን የሚገልጽ ለዓለም የተሰወረ አካል፥ ያለፈውን ሊያጸናላቸው፣ የሚመጣውን ሊያሳስባቸው ወረደ፡፡ በዚህ ስለዚህ መለኮታዊ ልዩ ምሪት፣ ልዩ ኃይል ተከናወነላቸው፡፡ ከልቡና የሚፈልቅ ህያው ዕውቀት ውስጣቸውን ሞላ፡፡ የማያባራ ንጋት አገኛቸው፡፡ ጸጋን ለበሱት፤ እውነትም ከፊት ታየቻቸው (10ኛውን ማዕረግ 'ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ' ይሉታል)፡፡ በሕይወት ውኃ ወንዝ ወዲያም ወዲህም የሚያብቡትን የብርሃን ፍሬዎች ለቀሙ፡፡ ስብዕና በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ አንቀጽ ተሠርታ እንዲህ ተፈጸመች፡፡ እነሆ ይህን ሙሉ ገባዔ የተካፈለ ከመካከላቸው የነበረም ሰው እንደሚከተለው ጻፈ፥

         "ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ" (ዮሐ. 1፥14)
        

____
*1 - ስያሜ ከማንነትና በተሰየመው ማንነት ላይ ከሚገለጥ ግብር ጋር በዋናነት ይጎዳኛል፡፡ ኢየሱስ የሚለው፥ ቃል ሥጋ በመሆኑ ምክንያትነት ለተለገለጠው ግላዊ ማንነት የተሰጠ ልዩ የተጸውዖ ሰም ነው፤ ልክ ሰዎች በየራሳቸው መጠሪያ "አብርሃም፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ .." እንደሚሰኙት፡፡ (ሉቃ. 1፥31) ህይወተ ሥጋው ላይ የሚተርኩ አራቱ ወንጌላት "ኢየሱስ" የሚለው ላይ አትኩረው በየቦታው የሚጠቅሱ ለዚያ ነው፡፡ ክርስቶስ ሲባል ግን በዚህ በኢየሱስነት በተጠራ ማንነት ላይ ይገለጥ ዘንድ ላለው የሹመት ግብር፥ ስያሜው ነው፤ በትርጉሙ የተቀባ ማለት ነው፡፡ ይሄ ስያሜ፥ ከመስቀል ሞት አስከትሎ በቀጠለው የትንሣኤና የዕርገት ስውር ጉዞ ለተገለጠው ሁለንተናዊነት ማንነት መግለጪያ ሆኖ በተለይ በጳውሎስ ተደጋግሞ ይጠቀሳል (ጳውሎስ ከአራቱ ወንጌላት ቀጥሎ እንደሚመጣ ያስተውሏል፤ እርሱ ከህይወተ ሥጋው ታሪክ ይልቅ በትንሣኤው የሆነውን ያስተምራል)፡፡ በአጭሩ ኢየሱስ፥ ቃል እኛን የሆነበትን፥ ከቤተልሔም እስከ ቀራኒዮ ተገልጾ በሥጋ የታየውን አንድ ሰውነት በግላዊ ማንነት ይጠራል፤ ክርስቶስ፥ በዚህ ማንነት ላይ የተሾመውን ህያውና መንፈሳዊ አገልግሎት አማክሎ ይገልጻል፡፡ (ማቴ. 8፥29) ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉዉ ስያሜ ሲጠራም፥ ሙሉዉን ጉባዔ ከስሙ ኋላ ይዞ ይከስተዋል፡፡

*2 - እርግጥ 'በዚህ ዓለም ሕግ' ሥር ከተባለ፥ መስመሩ ከፅንሰት ሳይሆን ከልደት ነው የሚጀምረው፡፡ ያልተወለደ ፅንስ እስኪወለድ ድረስ የሚኖርበት ማኀፀን፥ ዓለሙ እንደሆነለት ያጤኗል፡፡ ሕፃኑ፥ ከዚህ የማኀፀን ዓለም በልደት በኩል አልፎ ወደዚህ ዓለም ይገባል፡፡ በመሆኑ አሁን ስላለንበት ተጨባጭ ዓለም ሕግ ከተነሣ፥ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ያለውን ጎዳና ይመለከታል፡፡

*3 - መንፈስ ቅዱስ መውረዱ የተጠናቀቀው በ10ኛው ቀን ስለሆነ፥ በደፈናው "በሐምሳኛው ቀን (በዓለ ሐምሳ) ላይ መንፈስ ወረደ" ይባላል እንጂ፥ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ "ወደ አባቴ እኔ ስወጣ ወደእናንተ ደግሞ መንፈስ ይመጣልና ጠብቁ" ካለበት ተነሥቶ ነው መውረዱ የጀመረው፡፡ (ሉቃ. 24፥49) በሌላ አቀራረብ፥ ኃይልን እስኪለብሱ ድረስ ሐዋሪያት የጠበቋቸው ዐሥሩ ቀናት፥ የመውጣትና የመውረድ ጊዜያት ናቸው፡፡ ነገርየው ትይዩ የዕርገትና የርደት ጉዞ ነው፤ ወደ ላይ ወደ አብ ቃል እየወጣ እየወጣ ሲሄድ፥ ወደታች ደግሞ ከአብ የሚወጣው መንፈስ እየወረደ እየወረደ ለሰዎች መጥቷል፡፡ ለመንፈስ እንደ ሥጋ ውጣ ውረድ የለበትም፤ መገለጽ ያለመገለጹን በሰው ሰውኛ ማውሳት ነው፡፡

ይቀጥላል ...


@bemaleda_neku