Get Mystery Box with random crypto!

ጉባዔ ዘተዋሕዶ (የዮሐንስ ራእይ ምዕ. 22) ---- 1፤ በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና | በማለዳ ንቁ !

ጉባዔ ዘተዋሕዶ

(የዮሐንስ ራእይ ምዕ. 22)
----
1፤ በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።
2፤ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።

ሃይማኖትን መንገድ ይሉታል፡፡ ከየት ወደየት የሚወስድ? ከሚታየው ወደ ማይታየው፣ ከገዘፈው ወደ ረቀቀው፣ ከዚህ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም፣ .. ፡፡ በሰው ማንነት ስናየው፥ የሚታየው፣ የገዘፈው፣.. የሚሰኙት ዐለባውያን የሥጋ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የማይታየው፣ የረቀቀው እያልን ካወሳን ነፍስን፣ መንፈስን ወደተመለከተው እንሄዳለን፡፡ እስቲ ሐሳቡን ዘርዘር እናድርገው፡፡

በተዋህዶ ቤት የሚነገረው "አምላክ ሰው ሆነ፥ ሰውም አምላክ ሆነ" የሚለው ጉባዔ ከፅንሰት እስከ ዕርገት ድረስ የተዘረጋ ነው፡፡ ይሄ ጉባዔ በመሠረትነት ለሁለት የተከፈለ ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ በሚለው ቀዳሚው፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ልጅ ይሆን ዘንድ የተገለጠበትን ይተርካል፡፡ የሰው ልጅ የሥጋ ሕይወት በርዝማኔ ቢለካ፥ ከፅንሰት እስከ ሞት ይደርሳል፡፡ እንጸነሳለን፣ እንወለዳለን፣ እናድጋለን፣ .. ከዛ እንሞታለን፡፡ ይሄን የኅልውና ሥርዓት፥ ተፈጥሮአችን ያውቀዋል፡፡ በመሆኑ የአምላክ ልጅ የሰውን ልጅ ሆነው ስንል፥ እዚህ የባሕርይ መስመር ውስጥ ሳያዛንፍ ገባ እያልን ነው፡፡ ስለዚህ በሥጋ ማኅፀን ተጸነሰ፣ በሥጋ ተወለደ፣.. እያልን በሰው አንቀጽ ከገሊላ እስከ ቀራኒዮ የተጓዘውን ጉዞ እንተርከዋለን፡፡ /ታሪክ የሥጋ ነው፤/

ታዲያ ጎለጎታ ላይ ተፈጥሮአችን የሚያውቀው ይሄ የሰውነት ጉዞ በሞት ይዘጋል (ሕልም ብናይ፥ አእምሮአችን ሞትን በህልውና ስለማያውቀው ልንሞት ስንል ይነቃል፤ እንባንናለን)፡፡ ይሁን እንጂ ማንም የማይዘጋውን በሚከፍት ኀይለ ጥበብ የኢየሱስ የሞተ ሥጋው ከመቃብር ተነሥቷል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት፥ ከፅንሰት - ሞት የሚሄደው ባሕርያችን በዚህ ዓለም የማያውቀውን አዲስ እንግዳ ነገር ሊያይ ችሏል፡፡ እንደተነሣም አስቀድሞ ሲመራቸው ወደነበሩት ወዳጆቹ ገስግሶ ቀድሟል፡፡

የተነሣው ክርስቶስ የሞተው ኢየሱስ ነው *1፡፡ ግን የተነሣው እርሱ ሳይሞት ከነበረው የሚለይበት ዋነኛ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ሞት የመጨረሻው የነበረ ሥጋው፥ ሕይወትን አግኝቷል፡፡ በፅንሰት ተጀምሮ በሞት የሚጠናቀቀው ሥጋ፥ የወትሮ ፍጻሜው፥ ልዩ መነሻው ሆኖለታል፡፡ ይሄ የትንሣኤ ሥጋ አዲስ አካል ነው፤ ከእንግዲህ የማይሞት፣ የዚህ ዓለም ማንኛውም ሕግ የማይይዘው አዲስ ማንነት ነው፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱን ሊያገኝ በትንሣኤው ሥርዓት ሆኖ ወዳሉበት ሲሄድ፥ በዚህ ልዩ ኅልውናው ሆኖ ነው፡፡ አግኝቶም እንደገና ጠርቶ ለአንድነት ሰብስቧቸዋል፡፡ ለጥቆ ወደ ቢታንያ ኮረብታ አውጥቶ ባረኳቸዋል፡፡ በመጨረሻም እንደማይለያቸው ነግሯቸው እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ወደ ሰማያት ዐረገ (ወደ ዘላለምነት፣ ወደ ምልዓት ወጣ)፡፡ ይሄ ሁለተኛው ጉዞዉ ነው፤ ከሞት - ዕርገት የተለካው!

በመግቢያችን፥ በአደባባይቱ መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን፣ እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወት ውኃ ወንዝ ዮሐንስ በራእይ ሲያየው አይተናል፡፡ በዚህ ወንዝ ወዲህና ወዲያ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ አዝመራ አለ፡፡ ይሄ በወዲህና በወዲያ የሚያፈራው አዝመራ፥ ከላይ በመስቀል ሞት መካከልነት የከፈልነው የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ጉዞ ነው፤ አንዱ የትሕትናው አንዱ የልዕልናው ጉዞ፡፡

 ከፅንሰት                                                  ከመስቀል
     እስከ                |       ወንዙ        |               እስከ
   መስቀል         | (ቁርባን ፤ ሞት) |             ዕርገት
(ለዚህ ዓለም የሚታየው)       (ለዚህ ዓለም የማይታየው) 
                    
በወንዙ ወዲህ ማዶ (ከሞቱ በፊት) ተዘርቶ የሚለቀመው ፍሬ፥ የሥጋውን ወራት በረከቶች ይመለከታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳደዱት ተይዞ እስኪገደል ድረስ በእርምጃዎቹ ሁሉ ፈውስን፣ ትምህርትን፣ እውነትን እየሰጠ ለብዙዎች አገልግሏል፡፡ የተጠሩት ተማሪዎቹም፥ በዋለበት እየዋሉ፣ ባደረበት እያደሩ ቃሉን ሰምተዋል፤ ሥራውን ታድመዋል፡፡

ሐዋሪያቱ እንደየትናንታቸው አስተሳሰብ የሚለውን፣ የሚያዩትን ለመረዳት ይጥሩ ነበር፡፡ ጥያቄ ይጠይቁታል፤ እርሱም ይጠይቃቸዋል፡፡ ያስረዳቸዋል፡፡ ደ'ሞ የምነግራችሁን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከፊት ፊታቸው እንደሚቀድመው መምህራቸው በሥጋ ያሉ መሆናቸውን እዚህ ልብ የምንለው ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ከፅንሰት - ሞት ብለን በዘረጋነው በዚህ ዓለም ሕግ ሥር ያሉ ናቸው *2፡፡ ስለዚህ አረዳዳቸው፣ አኳኋናቸው፣ ሁለንተናቸው በዚህ ዓለም ቅኝት የተቃኘ ነው፡፡ እንደሚበሉት፣ እንደሚጠጡት ግዘፍ የነሣ እህል ውኃ ግዘፉን ብቻ ያስባሉ፡፡ ከሚታየው ባሻገር ስለሆኑ ጉዳዮች የሚነግራቸው ነገራት እምብዛም አይገባቸው ነበር፡፡

በየሚሄድበት እየሄዱ የተከተሉ ደቀመዛሙርቱ፥ ጉባዔያቸው በጊዜ ሞቱ ተናጠቀቀ፡፡ አበው የዚህን ጉባዔ መጠናቀቅ "ትምህርት በሰው ልቦና ተከተተ" ሲሉ ይገልጹታል፡፡ እያወጣ እያወረደ፥ በሚሥጢር፣ በግልጽ፣ በምሳሌ ሕይወትነት ያለው መንፈሳዊ ቃሉን በልባቸው ሲዘራ ቆይቶ፥ በመስቀል ተገደለ፡፡ ሐዋሪያቱ ተስፋ ያደርጉበት አስተማሪያቸውን በአደባባይ ተነጠቁ፡፡ ተስፋቸው በሞቱ ሞተ፡፡ ተስፋ ከሞተ፥ የነገራቸውም ሃሳብ አብሮ እንደሚሞት አያጠይቅም፡፡ በልባቸው የተዘራ ቃሉ አፈር ገባ፤ ከመሬት ተሸፈነ፡፡ ስለዚህ ሰብሳቢያቸውን ካሳደደባቸው ዓለም ሸሽተው በር ቆልፈው ተቀመጡ፡፡ እነዚህኞቹ ሐዋሪያት፥ ማንኛውም በሃይማኖት አስተምህሮትነት እየተጓዘ፥ በሕግ በትእዛዛት እየተመራ፥ በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ እስከ ሥጋ ደሙ (ቁርባን) የሚገሰግስን ትጉ አማኝ ይወክላሉ፡፡ /ሥዕሉን ይመለከቷል፤/

ይሁን እንጂ ሥጋ ደሙን ወስደው ደጃቸውን ዘግተው ከዓለም የጠፉት ደቀመዛሙርት፥ መሪያቸውን እንደገና በትንሣኤው ያገኙታል፡፡ በዝግ ደጅ ገብቶ ባሉበት ያገኛቸዋል፡፡ (ዮሐ 20፥19) 'በተዘጋ በር ሳይከፍት አለፈ' ከተባለ፥ ተጨባጭ የሚዳሰስ አካሉ በዚህ ባለንበት ጠጣር ዓለም የጊዜና የቦታ አውታር ሥር እንዳልተያዘ እረዳለን፤ ወይም በሌላ አነጋገር ሥጋው መንፈስነትንም እንደተዋሐደ እንገነዘባለን፤ ግዘፍነቱን ያለቀቀ ረቂቅ ሥጋ!

እንግዲህ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደነርሱ በመምጣቱ ምክንያት፥ የሞተባቸውም ተስፋ እንኪያስ ይነሣላቸዋል ማለት ነው፡፡ በልብ በአእምሮአቸው የታተመች እርሱነቱ፥ በመነሣቱ ተነሥታላቸዋለች፡፡ ከሞቱ ቀድሞ ያስተማራቸውም ሁሉ ኀልውናን በነርሱ አገኘ፡፡ በቁርባን ሥርዓት በሰውነታቸው የተቀበረ ሥጋው ደሙ ከባሕርያቸው ተነሣላቸው፡፡ እነሆ ስለዚህ፥ በሰውነት ያለን ሕያውነት ሊሰሙት ቻሉ፤ የሞትን አስፈሪነት ናዱት፤ ድንበርነቱንም ውስጣቸው ተሻገረው፡፡ በዚህ ሳያበቃ አእምሮአቸው ደ'ሞ ያስተውል ዘንድ ተከፈተ፡፡ (ሉቃ. 24፥45) አስቀድሞ በኅቡዕ የጻፈባቸው ሁሉ በዕውቀትነት ተተነተነላቸው፤ ሚሥጢር ተጨበጠላቸው፤ ምሳሌ ተፈጸመላቸው፡፡ እነዚህኞቹ ሐዋሪያት ቀድመው ከተሰበሰቡበት ይለያሉ፡፡ የማይሞት መምህር እንደገና ጠርቷቸዋልና የማይሞት ሃሳብን ተቀዳጅተዋል፡፡ ትንሣኤ ልቡናን፣ አእምሮ መንፈሳዊን አግኘተዋል፡፡ በስውር በግልጥ፣ በሥጋ በመንፈስ ላይ ሕዋሶቻቸው ሰልጥነዋል፡፡