Get Mystery Box with random crypto!

ፖሊስ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕይወቱ ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ሲሆን አስከሬ | Ayu Zehabesha-Official (አዩ ዘሀበሻ)

ፖሊስ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕይወቱ ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ሲሆን አስከሬኑም በባለሙያዎች ምርመራ ሊደረግበት መሆኑን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ማዲንጎ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 17/2015 ዓ.ም. ጠዋት 1፡30 አካባቢ ለሐኪሙ ስልክ እንደደወለና ወደ ክሊኒክ መሄዱን ፖሊስ መረዳቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚያም በኋላ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው አንድ የግል ክሊኒክ በመሄድ የህመም ማስታገሻዎችን እና ሌሎች መድኃኒቶችን መውሰዱንና 3፡00 ላይ ሕይወቱ ማለፉን እስካሁን ፖሊስ አገኘው ያሉት መረጃ ጠቅሰው ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ የድምጻዊ ማዲንጎ አስክሬን ሕይወቱ ካለፈበት የግል ክሊኒክ ወደ አቤት ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፖሊስ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት የድምጻዊውን ሞት መንስኤ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሆነ የገለጹት ኮማንደር ማርቆስ፣ ምርመራው እንደተጠናቀቀ ውጤቱን ፖሊስ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ከድምጻዊው ህልፈት ጋር በተያያዘ ህክምና ካገኘበት ክሊኒክ ሠራተኞች ታስረዋል ስለሚባለው ም/ኮማንደር ማርቆስ ተጠይቀው ሲመልሱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ሰው እንደሌለ፣ ነገር ግን አንድ ሐኪም ቃል እንዲሰጥ ተደርጎ ተለቋል ብለዋል።
የድምጻዊውን ህልፈት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የሙያው አድናቂዎች ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለጹ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “ለአገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ ነው” ሲሉ በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ማዲንጎ አፈወርቅ የተወለደው ጎንደር አዘዞ ውስጥ ሲሆን እድገቱ ደብረ ታቦር ነው። እድገቱ በወታደር ቤት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ቃለ ምልልሶቹ ላይ የገለጸው ማዲንጎ፣ ስሙንም ያገኘው እዚያ መሆኑን ተናግሯል።
ወላጆቹ ያወጡለት ስም ተገኔ የሚል የነበረ ሲሆን፣ ማዲንጎ የሚለውን ስም በወታደር ቤት ሳለ ነበር ያገኘው፤ ከዚያ በኋላ በዚሁ ስም እየተጠራ በሙዚቃ ሙያው እውቅናን አትርፏል።
ከልጅነቱ አንስቶ ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ማዲንጎ በጦር ሠራዊት ቤት ሙዚቃ መጫወት ጀምሮ በተለያዩ ክበቦችና የሙዚቃ ባንዶች ጋር በመሆን ሰርቷል።
የታዋቂ ድምጻውያንን ሙዚቃ በመጫወት የጀመረው ማዲንጎ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉለትን የራሱን ነጠላ ሙዚቃዎችና ሙሉ አልበም አቅርቧል።
ማዲንጎ በሥራዎቹ በአገር ውስጥ በታላለቅ መድረኮች ላይ ከሚጋበዙ ድምጻውያን መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከአገር ውጪም በተለያዩ አገራት በተደጋጋሚ ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል።
ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የ42 ዓመት ጎልማሳ እና የአንድ ልጅ አባት ነበር።
ነፍስ ይማር
@ayuzehabeshaofficial