2022-06-07 12:04:16
"ኦርቶዶክስ መሆን እፈልጋለሁ!"
ሚጢጢዬዋ ሰባኪ
ቦታው ሐዋሳ ነው። ባለፈው ወር ከአንድም ኹለት ጊዜ ወደ ሐዋሳ ለአገልግሎት ሔጄ ነበር። ኹሌም ወደ ሐዋሳ ስሔድ አንድ አስገራሚ ነገርን መስማትን ጆሮዬ ለምዷል። ከመልመድም አልፎ ይናፍቅ ጀምሯል። ለዚያም ነው አሁን ከሐዋሳ በ25 ደቂቃ መንገድ ርቀት ተጎራብታ ወደ ምትገኘው ሻሸመኔ እየሔድኩ ይህ ታሪክ የታወሰኝ። ለነገሩ ሻሸመኔም ብዙ ታሪክ የተሠራባት ቦታ ስለሆነች ለአንድ አዲስ ድንቃይ ታሪክ ጆሮዬ ሳይቋምጥ አይቀርም።
የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም መዋዕለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አለው። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ኦርቶዶክሳውያንም ሆኑ የሌሎች አብያተ እምነት አማኞች ይማሩበታል።
ሕፃናቱ ሰኞ ጠዋት ሲገናኙ ታዲያ የቅዳሜና እሑድ ውሏቸውን እየተሻሙ ለጓደኞቻቸው ይተርካሉ። አንዱ ከአንዷ እምቦቀቅላ አፍ ነጥቆ ያወራል፤ ሌላኛዋም እንዲሁ። ዘወትር ሰኞ ከሚተርኩት ቁምነገር መካከል ታዲያ "እኔ ትላንት ቆረብኩ" የሚለው የማይቀር ነበር። አንዷ ይህን ካለች 'እኔም' 'እኔም' የሚሉ ቀልጣፋና ኮልታፋ ኦርቶዶክሳውያን አፎች ያጅቧታል። ቁርባንን የማያውቁ ሌሎች ኮልታፎች ግራ ይገባቸዋል። ቁርባንን ከማያውቁ ኮልታፋ አፎች አንዱ የሚጡ ነው።
ሚጡ ከፕሮቴስታንት ወላጆች ተገኝታ በእናትና አባቷ ምርጫ ፕሮቴስታንት የኾነች እምቦቀቅላ ናት። ዘወትር ሰኞ ኦርቶዶክሳውያን ጓደኞቿ መቁረባቸውን በነገሯት ቁጥር ታዲያ ትቆጭ ኖሯል። አንድ ቀን ሰኞ አንዲት ሚጢጢ የክፍል ጓደኛዋ ከእናትና አባቷ ጋር አስቀድሳ መቁረቧንና በሰንበት ትምህርት ቤት የተማረችውን በመዝሙር እያጀበች ስታወራና የውሎዋን ቅድስና በመንገር እንቁልልጭ ስትል የሚጡ የመቁረብ ፍላጎት ከአቅሟ በላይ ሆነ። አንገቷን ቀለስ አድርጋ የሥረኛው ከንፈሯን እንደ ማኩረፍ ባለ መለማመጥ አሞጥሙጣ ዐይኗን በተቻለ መጠን በምስኪን አተያይ አሠልጥናና ዕምባዋም ቀሮ ወደ ቆረበችው ጓደኛዋ ሔደችና "በናትሽ እ... እኔንም እ... እ.. አቁርቢኝ" ብላ ግጥም አድርጋ ሳመቻት። ጓደኛዋ ግን "አንቺ መቁረብ አትችዪም" አለች።
"ለምን?" በሚጡ ግራ ዐይን የሞላው ዕንባ የመሬት ስበት መኖሩን አረጋገጠ።
"አንቺ ኦርቶዶክስ አይደለሽማ..."
"መቁረብ እፈልጋለሁ" ሚጡ ሊያለቅስ አምስት ጉዳይ በሆነው ድምጸት አሞሸች። ጓደኞቿ ሳቁ፤
"መቁረብ እፈልጋለሁ" ክፍሉ በሳቅ ተሞላ። ሚጡም ሳቃቸው የዐይን ሚጥሚጣ ሆነባት፤ እንባዋ ጎረፈ፤ በሳቅ የታጀበ የልቅሶ ወላፈን 'ሚስ' ባረፈደችበት ክፍል ውስጥ ተቀጣጠለ። የሚጡ ልቅሶ ካንጀት ነበርና ከሳቁ ድምቀት ይልቅ መጉላት ጀመረ። ጓደኞቿ መሳቅ ትተው ማባበል ጀመሩ። ከልብ መሻት የፈለቀች አንዲት ልቅሶ የእልፎችን ሳቅ አሸነፈች። ተቆጣጠረቻቸው። በልቅሶ የተጨመቀው ዐይን ያወጣው ዕንባ በሳቅ የተጨመቁ ዐይኖች ያፈለቁትን ዕንባ ዋጣቸው፤ የተገኘን ውኃ ኹሉ በጉልበቱ የዝናብ እንደሚያስመስል እንደ ደራሽ ጎርፍ በሳቅ የተገኘው ዕንባ ኹሉ በሚጡ ዕንባ ጉልበት እንደዚያ ኾነ...
"መቁረብ እፈልጋለሁ"
አሁን ሳቅ የለም - ማባበል ብቻ እንጂ። 'አይዞሽ በቃ' እያሉ ከልብ የሚያባብሉ ከንፈሮች ጉንጮቿ ላይም ያርፉ ነበር።
ሚጡ ቤት ስትገባ እንደውዳሴ ማርያም ቀኑን ሙሉ ስትደግመው የነበረውን ሐረግ ደገመችው፦
"መቁረብ እፈልጋለሁ"
ወላጆቿ ግራ ገባቸው። ቀልድም መሰላቸው። ለማረሳሳትም ሞከሩ። ሚጡ ግን ያነሣሣት መንፈስ ቅዱስ ነውና ዝም ልትል አንደበቷ አልታዘዘላትም።
"መቁረብ እፈልጋለሁ!"
አንደበቷ ብቻ ሳይሆን አካሏ በሙሉ በዚህ ፍላጎቷ ተቃኘ። ዐይኗ በዕንባ መቁረብን ለመነ። ጆሮዋ ሌላ ነገር መስማትን ናቀ፤ አፎች ኹሉ 'እናቆርብሻለን' የሚል የምሥራችን እንዲዘምሩም ተመኘ። እግሯ ቤተ ክርስቲያን እንጂ የትም የማይሔድ ኾነ። አፍንጫዋ የጸሎት፣ የምልጃ ዕጣንን መዓዛ እንጂ ሌላ ሽታ ከረፋው። እጇ ከቆረበች በኋላ ነጠላዋን አፈፍ አድርጎ ጸበል እስክትጠጣ አፏ ላይ ሊጫን ፣ አፏን ሊሸፍን ጓጓ - ጓደኞቿ እንደነገሯት - እንደዚያ። አንገቷ ካለ ክር መራቆቱ አሳፈረው። ግንባሯ መስቀል መሳለምን፣ ከንፈሯ ሥዕለ ማርያምን መሳምን ተመኙ። ጸጉሯ በሻሽ ተሸፍኖ፣ ትከሻዋም ነጠላ ተጣፍቶለት መዝሙር ማጥናትና ሰኞ ስትመጣ ከጓደኞቿ ጋር መዘመር የዘወትር ኅልሟ ሆነ። የሰውነት አካሏ ባጠቃላይ ኦርቶዶክሳዊነትን ሻተ፤ ጌታ የለኮሰው፣ ሐዋርያት ያቀጣጠሉት የሃይማኖት እሳት በማዕከለ ሰብእናዋ ተንቦገቦገ። (ሉቃ. 12፡49)። የሚጡ ኹለመና እንዲህ አለ፦
"መቁረብ እፈልጋለሁ፣ ኦርቶዶክስ መሆን እፈልጋለሁ!"
ይህ የሚጡ ልምምጥ ቃል ብቻ አይደለም - በዕንባ የተለወሰ ንጹህ ጩኸት እንጂ። ንግግር ብቻ አይደለም - ከደመና በላይ የሚወጣ ልመና እንጂ። ዝርው ድምጽ ብቻ አይደለም - ሳይበተን የሚያርግ ጸሎት እንጂ።
...እናም ወደላይ ወጣ። ከፍ ከፍ አለና ራማን አንኳኳ። ቅዱስ ገብርኤልም አስተናገደው።
የሚጡ ሰሞንኛ ውትወታ ግራ ያጋባቸው ወላጆቿ ከእሑዶች በአንዱ ሚጡን ይዘው ወደ ገዳሙ ሰንበት ትምህርት ቤት መጡ። ሚጡ ዛሬ ነፍሷን አታውቅም። በወላጆቿ ተይዛ ልክ እንደጓደኞቿ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጣች። ኹሉነገሯ ጥርስ ሆኗል። ሰኞ ደርሶ ትምህርት ቤት የምታወራው፣ የምትፈጥረው የትረካ ድባብ በሰንበቱ ታያት።
ወላጆቿ የሆነውን ኹሉ ለሰንበት ትምህርት ቤቱ መምህራን ነግረው "እባካችሁ ሚጡ እንድትቆርብ አድርጉልን" አሉ። ሚጡም "መቁረብ እፈልጋለው!" አለች በጥዑም አንደበቷ።
መምህራኑ ግን አንድ ሰው ለመቁረብ የሚያስፈልገውን ትምህርት መማር እንደሚቀድምና ወላጆቿም በቁርባን ጊዜ በመቅደስ መቆየት እንደማይችሉ አስረዷቸው። ሚጡም የዚያኑ ቀን እንደማትቆርብ ተረዳችው። አንድ ነገር ግን ገብቷታል - ኦርቶዶክስ ካልሆነች በገዳሙ መቁረብ እንደማትችል።
ስለዚህ ድምጿን ከፍ አድርጋ "ኦርቶዶክስ መሆን እፈልጋለሁ" አለች። ወላጆቿ ደንግጠው ተያዩ። በድምጿ ውስጥ ያለው ቆራጥነት እናትና አባቷን ለመተው እንኳን ደግማ የማታስብ አስመስሏታል።
መምህራኑ ሚጡንም ወላጆቿንም አረጋግተው ክትትላቸውን ቀጠሉ። የደብሩ ካህናትም ጉዳዩን ሥራቸው አደረጉት።
ከዕለታት ለሚጡ በተቀደሰች አንዲት እሑድ እንዲህ ኾነ....
የሚጡ ወላጆች ከመምህራኑ እንደተነገራቸው ቅዳሴ ሳይጀመር በሌሊት የገዳሙ ግቢ ውስጥ ተገኙ። መምህራኑ እየመሯቸው ወደ ክርስትና ቤት ሔዱ....
ከቆይታ በኋላ ወጥተው ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ። ሚጡ የአንድ ሰውን እጅ ይዛ የቤተ መቅደሱ በር ጋር ደረሱ። እንደተማረችው ጫማዋን አውልቃ ተሳለመች፤ ወደ ውስጥ ገባች። አብረዋት ያሉትም ገቡ። ወላጆቿም ከመግባት አልተከለከሉም።
"ፃዑ ንዑሰ ክርስቲያን" ተባለ። ወላጆቿ ግን አልወጡም።
ልዑካኑ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይዘው ከመቅደስ በክብር ወደ ቅድስቱ ተገለጡ። እንደተለመደው ብዙ ቆራቢያን ተሰለፉ። ሚጡም ሰልፉን ከሠሩት ተነሣህያን ጋር በመኾን ከበረች።
ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ መካከል በወላጆቻቸው ታጅበውሊቆርቡ የተሰለፉም አሉ። ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚጡ ተበለጡ። በርግጥ ሚጡ በልጅነት ጥምቀት ከብራ፣ በምሥጢረ ሜሮን መንፈስ ቅዱስን ተቀብላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቁረብ መቅረቧ ነው። ጓደኞቿ ግን ደጋግመው በሥጋ ወደሙ ከብረዋል። ግን ኹሉም ብቻቸውን ናቸው።
1.6K views ቀላያት, 09:04