Get Mystery Box with random crypto!

#ህያበ ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_ሁለት ፡ ፡ #ድርሰት_ኤርሚ 'እሱን እንዳታስቢው ወይም ራስሽ ፈል | አትሮኖስ

#ህያበ


#ክፍል_አስራ_ሁለት


#ድርሰት_ኤርሚ

"እሱን እንዳታስቢው ወይም ራስሽ ፈልገሽ አግኝው... ደግሞ አታገኝውም" አማራጭ የለኝም ሻንጣዬን ይዤ ወደኋላ ተመለስኩ።

"እሺ ውሰደኝ አሁን ውሰደኝ"

"አይ አይሆንም ነገ ነው የምንሄደው" በእሽታ አንገቴን ነቀነኩለት።

ወደቀኝ ገልመጥ ብዬ ሳይ የሰርግ ቬሎዬ ተሰቅሏል። ለራሴ ወደኋላ የለም አልኩ...

"አንደርስም እንዴ ደግሞ እኮ አይኔን በጨርቅ አስረህዋል። የት ነው የምንሄደው ራቀብኝ? ያ ውሻ የት ነው ያለው?"

"አይንሽን ከገለጥሽ ከኔ ጋ ትጣያለሽ ማርያምን የምሬን ነው። ታገሽ ትንሽ ነው የቀረን ደርሰናል" ጥቂት ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ መኪናውን አቆመው

"አሁን ጨርቁን ማንሳት ትችያለሽ" ቶሎ ብዬ ፈታሁት... ሰው የሌለበት ቦታ ነው።

"ምንድነው ቢኒ እየቀለድክብኝ ነው" ፊቴን አዙሬ በንዴት አየሁት

"ውረጂ.,. ያውልሽ እዛጋ ይታይሻል...( በወዳደቁ ነገሮች የተሰራች ቤት) እዛ ውስጥ አለልሽ ውረጂና የፈለግሽውን አድርጊው" ሳላቅማማ ወረድኩ። በእልህና ንዴት እየተራመድኩ ወደቤቱ ተጠጋሁ ልገባ ስል

"እባቷ ነኝ ባሏ. ... ሀ ሀ ሀ... ንገሩኝ እስኪ እናቷን አግብቶ ልጁን ያስረገዘ አባት ታውቃላችሁ... አታውቁም? ሙትቻ ለምንድነው የምታፈጡብኝ... መልሱልኝ... ኧረ ተውኝ ኡ ኡ ኡ..." ጩኸቱ አስደንግጦኝ ወደኋላ ተመለስኩ። ትንሽ ተራምጄ ቆምኩና ልጄን አሰብኳት "እገለዋለሁ" ወደ ቤቷ ተመለስኩና ከፍቼ ጎንበስ ብዬ ገባሁ። የቤቱ ጠረን ይገፈትራል ሰው የመጣም አልመሰለው ዝምም ብሎ ልፍለፋውን ቀጥሏል። የማላውቃቸውን ብዙ የሴት ስሞች ይጠራል... ያለቅሳል፣ ይስቃል፣ ይራገማል፣ ድንገት ደግሞ አስደንጋጭ ጩኸቱን ይለቀዋል። ለደቂቃዎች ዝምምም ብዬ ሰማሁት... በብዙው የቤቱ ቀዳዳ በሚገባ ብርሀን አየሁት ከድምፁ ውጪ ምኑም እሱን አይመስልም። ልብሱ ተቀዳዷል፣ ፊቱ ጠቁሮ ከሰል መስሏል፣ ፀጉሩ ተንጨባሯል፣ እላዩ ላይ ተፀዳድቶ መሬቱ ጭምር በሽንትና ሰገራ ተበክሏል። ዮኒ እኔ ልሰጠው ካሰብኩት ሞት በላይ በቁሙ ሞቷል... ልቤን ሽው የሚል የሀዘኔታ ጦር ወጋኝ። ወዲያው ደግሞ ልጄን የከዳኋት መሰለኝ... እየሮጥኩ ከቤቱ ወጣሁ... ልፍለፋው ከኋላዬ ይሰማኛል... እያለቀስኩ መኪናውን ከፍቼ ስገባ

"አደረግሺው ህያብ ገደልሽው" አለኝ

"ሞቷል እኮ ቢኒ የሞተን ሰው ድጋሚ እንዴት እገለዋለሁ" ድፍት ብዬ ተንሰቀሰቅሁ

"ቢኒ እባክህ ምንም ሰላም ሊሰማኝ አልቻለም ዮኒን ሆስፒታል እንውሰደው" ደረቱ ላይ ተኝቼ ለቀናት ከራሴ ጋ ስከራከርበት የነበረውን ሀሳብ ነገርኩት

"እኔ የማውቃትም የምወዳትም ህያብ ይቺ ናት ለጠላቷ ሳይቀር የምትራራ። አታስቢ የኔ ቆንጆ ዛሬውኑ እናደርገዋለን" እዛው ቦታ ተመልን ሄድን። ወደዛች ቤት ገባን አጠገቡ ዳቦ ቁጭ ብሏል። ለነፍሱ ያደረ ሰው እንደሚመግበው ገባኝ። መለፍለፉን አላቆመም እንጂ ተዳክሟል... ይዘናቸው የሄድነው ባለሞያዎች በግድ አንስተው ስትሬቸር ላይ አደረጉት... ከኪሱ የተጣጠፈ ወረቀት ወደቀ፤ ቀልጠፍ ብዬ አነሳሁትና ዞር ብዬ ከፈትኩት በትልቁ ርዕስ "ፀፀት" ይላል። ከስሩ ደግሞ "ለማታዩኝ እኔ ግን በየቀኑ ለማያችሁ ለበደልኳችሁ ሁሉ" ይላል... ትርጉም ያለው ነገር ሊሆን ቢችልም ማንበብ አልፈለኩም... ሌላ ሸክም መሸከም አልፈልግም... እጄ ላይ ያለውን ሶስት ገፅ ወረቀት ቀዳድጄ ዱቄት አደረኩትና ለነፋስ ሰጠሁት ብትትንን... አምቡላንስ ውስጥ አስገብተው ይዘውት ሄዱ። ሰላም ተሰማኝ

አዳራሹ በእንግዶች ጢም ብሎ ተሞልቷል። ቃል የሚያገባቡን ቄስ ቦታቸውን ይዘው ተቀምጠዋል።

"በሀዘን በደስታዋ በህመም በጤናዋ..." ቢኒ ቃል ገባ እሱ ያለውን መልሰው እኔንም አስባሉኝ።

የጋብቻ ቀለበት ጣቴ ላይ አደረገልኝ እኔም እንደዛው አደረኩለት.....
ገና ወደሰውነት ቅርፅ ያልተቀየረው የአምስት ሳምንት ልጄ ደስ ብሏት/ብሎት ይሆን ሆዴን ዳበስኩት። የልጄ አባት ቢኒ ፈገግ ብሎ አየኝ

"ተመስገን" አልኩ በልቤ የማያልፉ የመሰሉኝ ሁሉ አለፉ... ዛሬ ደስተኛ ነኝ... ነገን አምላክ ያውቃል።

ተ ፈ ፀ መ