Get Mystery Box with random crypto!

አሮራ (ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል) ምዕራፍ _3 ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ሊሄድ በመነ | አትሮኖስ

አሮራ
(ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል)
ምዕራፍ _3
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ
ሊሄድ በመነሳቱ ቅር ብሏት"አጎቴ ደግሞ...እዚሁ ምትፈልገውን መጠጥ ያምጡልህ "አለችው።
አልተስማማም"አይ የዚህ ቤት መጠጥ ውስኪ.. ቢራ ምናምን ነው ..እኔ ምፈልገው ካቲካላ ነው።"አላት።
"እሺ ግን በልክ ጠጣ ...አብዝተህ ጠጥተህ ብኃላ  ቢያምህ በጣም እበሳጭብሀለሁ።"
"እቪ ሮሪ "አለና እንደልማድ ቦርሳዋን በመክፈት ...የተወሰኑ ብሮችን መዘዝ አደረገና ኪሱ ከቶ...ግንባሯን ስሞ ወጥቶ ሄደ።እሷም በተቀመጠችበት ቦታ ሆነ በስስት አይኗ ሸኘችው።ከዛ ጠረጴዛው ላይ ትቶት የሄደውን ሲጋራ አነሳችና አንድ መዛ ለኮሰች...ከዛ ማጨስ ጀመረች...የረሳ መስሎ አውቆ ለእሷ ሲል ትቶላት እንደሄደ ታውቃለች።ሁሌ እንደዛ ነው የሚያደርገው።የእሷ ተወዳጅ የልብ አውቃ አጎት።

ከምታጨሰው ሲጋራ ጭስ እየትጎለጎለ ሄዶ በአየር ላይ ሲበተን ማየት ያስደስታታል።እሷም የውስጥ ህመሟና የልብ ሀዘኗ አንድ ቀን እንዲህ ከውስጧ ተመዘ ወጥቶ በአየር ላይ ተበትኖላት ነፃና ደስተኛ ሆነ ለአንድ ወር እንኳን ሰላማዊ ህይወት ኖራ ሰላማዊ ሞት ብትሞት ደስ ይላታል።በውስጧ የተዳፈነው ሚስጥር ውስጧን በልቶ ሊጨርሳት ነው።
ሁል ጊዜ በልባችን አርቀን የቀበርነው ምስጢር ከሌላ ከማንም ሰው ጋር አንስተን ልንነጋገርበት  የማንችለው ስውር ገበናችን እያንዳንዶን ቀን በውስጣችን  የሚኖረው እኛኑ እየበላ ነው።ልባችንን ይቀረጣጥፋታል ነፍሳችንን በስለታም ጥርሱ ያደቃታል...አዎ ሄዶ ሄዶ መፍትሄ ማናገኝለት ከሆነ ሙሉ በሙሉ ይውጠናል።ምናችንንም አያስቀር ነፍሳችንንም ስጋችንንም ሰልቅጦ በመዋጥ ከህልውና መዝገብ ላይ ያጠፋናል።

እናም አሮራ ይሄ በደንብ ይታወቃታል የገዛ ምስጢሯ ማንም እንዳያስተውለው ማንም እንዳይረዳው እታች ጥልቅ ንብርብር ልቧ ውስጥ እንደቀበረችው ብታውቅም ከዛ አፈንግጦ በመውጣት ከአንጀቷ ሙዳ ስጋ ዘንጥሎ ወደቦታው ሲመለስ በደንብ ይታወቃታል በሌላ ቀን ደግሞ ወደጨጓራዋ ሄዶ የላይ ንብርብርና ሻካራ ክፍሉን ሞዣልቆ ሲያነሳውና ሲሠለቅጠው በደንብ ይሰማታል።ድንዛዜውና ቀጠሎ  መፈጠሯን እስክጠላ ያሰቃያታል።ብቻ በአጠቃላይ በውስጧ አውሬ እያሳደገች ነው።እሷን እየተመገበ በማደግ ላይ ያለ አውሬ።እሷ እንዲህ የተሠቃየች አባቷስ እንዴት ነው መኖር የቻለው?ሁል ጊዜ በውስጧ የሚላወስ ጥያቄ ነው።እንደሷ ሲያዝንና ሲተክዝ እንኳን አይታው አታውቅም።ሁል ጊዜ እንደሮጠ ሁል ጊዜ የሆነ ገንዘብ ለማግኘት...የሆነ ኃይል ለመጨበጥ...የሆነ ተልኮ ለማሳካት እንደባከነ ና እንደተዋከበ ነው።ስለውስጥ ህመሙና ስለልብ ስቃዩ ማሰቢያ ጊዜም ያለው አይመስላትም።አረ መታመሙን ራሱ እርግጠኛ ሆና መናገር አትችልም። ከተቀመጠችበት ክፍል ወጣችና ኮሪደሩን አልፋ ታናሽ እህቷ መኝታ ክፍል ሄደች።አንኳኳችን ገፋ አድርጋ ስትገባ እህቷ አልጋዋ ላይ ቁጭ ብላ  የስዕል መሳያ ደብተሯን ዘርግታ የተለያዩ ከለሮችን እየቀባች ነበረ...መጀመሪያ ሞግዚቷ የመጣች መስሎት ቀና አላለችም ነበር
"የእኔ ፅጌረዳ ምን እየሠራሽ ነው?"የሚለውን የእህቷን ድምፅ ስትሰማ ግን እጇ ላይ ያሉትን ከለሮች በትና ደብተሯንም ጥላ ከአልጋዋ ተስፈንጥራ ወረደችን አላዬ ላይ ተጠመጠመችባት።
አሮራም እንጠልጥላ እንዳቀፈቻት ወደአልጋው ወሰደቻትና እሷን አስቀምጣት ከጎኗ ተቀመጠች።

ታናሽ   እህቷ ሳሮን ገና ሰባት አመት ለመድፈን ሁለት ወር ይቀራታል።እናቷ ገና የሁለት አመት ጨቅላ እያለች ነው የሞተችው።በዚህ የተነሳ አሮሯ እንደእህቷ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደራሷ ልጅ ነው የምታያት..ከሞግዚቶቹ ጋር በመተጋገዝ በምቾት እንድታድግ የተቻላትን አድርጋለች
ቢያንስ የእናቷ የሙት መንፈስ በእሷ ላይ ያለውን ቅሬታ ሊያለዝብ የሚችልበት አንድ ብቸኛ  የሠራችው ጥሩ ተግባር   ይሄ ታናሽ እህቷን ለማሳደግ የምታደርገው  እንክብካቤ ነው።
ከእህቷ ጋር ብዙ ነገር ከተጫወቱ በኃላ በመሀል የልጠበቀችው አስደንጋጭ ነገር  አንደበቷ ወጣ።
በተኮላተፈ አንደበት"እኔም እንደአንቺ ቶሎ ባድግ ደስ ይለኛል"አለቻት።
አሮሯ ደነገጠችና"የእኔ ውድ ለምንድነው ፈጥነሽ ማደግ የፈለግሽው...?ብዙ ትላልቅ ሰዎች እኮ እንደውም ተመልሰው ልጅ መሆን ነው የሚፈልጉት።"
"እንዴ !!!ልጅ መሆን ምን ሊያደርግላቸው?"
"ትልቅ ስትሆኚ ህይወት እየጠቆረችና እየቆሸሸች ትሄዳለች።ስታድጊ ደስታሽ እየደበዘዘ ሳቅሽ እየፈዘዘ ይመጣል።ትልቅ ስትሆኚ  ሀሳብሽ  በተንኮል የተሞላ ምኞትሽም በራስ ወዳድነት የተሰላ እየሆነብሽ ይሄዳል።"
ትንሽ እህቷ አሮራ ካተናገረቻቸው ነገሮች መካከል አንድም አልገባትም።
"እህቴ ምንድነው ምትይኝ?"
"የተናገርኩትን እርሺው...ለመሆኑ አንቺ እንደእኔ ቶሎ ማደግ የፈለግሽው ለምንድነው?"ስትል መልሳ ጠየቀቻት...የሠማችው መልስ ግን ጭንቅላት የሚያዞር እና ፈፅሞ ያልጠበቀችው ነበር።"አባዬ እንደአንቺ እንዲወደኝ"ነበር ያለቻት።
ይህን ቃል ስትሰማ በአእምሮዋ ደማሚት ነገር ነው የፈነዳው...በጦር ጎንን የመወጋት አይነት  ስቃይ ያለው ስሜት።
ብዙም እርግጠኝነት በማይገለፅበት የድምፅ ቅላፄ "እንዴ ?አባዬ እኳ አንቺን ነው ከእኔ በላይ የሚወድሽ "አለቻት።
"አይ አይደለም...ግን እንደአንቺ ባድግ ካንቺ እኩል ይወደኛል... አብሬው እንድተኛም ይፈቅድልኛል።"ስትላት
ሽምቅቅ አለች።ኩምትርትር አድርጎ ውስጥን የሚቆራርጥና የሚሸረካክት መሠነጣጠቅ።
ትንሽዬ ተወዳጅ እህቷን...የእናቷን አደራ የተሰጠቻት እህቷን ወደራሷ ስባ አቀፈቻት።የእኔ ውድ በደንብ እንድትስሚኝ እፈልጋለሀ
"..እኔ  የራሴ መኝታ ቤት የሌለኝ እና አባቴ መኝታ ክፍል የምተኛው አባቴ ከአንቺ በላይ ስለሚወደኝ ሳይሆን እኔ ስለሚያመኝና ለሊት ተነስቼ መድሀኒት መውስድ ስላለብኝ ሰዓቱን ጠብቄ እንድነሳ አባቴ ስለሚያግዘኝ ነው።እንጂ እንደውም እኔ እንደአንቺ የግሌ የሆነ የሚያምር መኝታ ክፍል   ቢኖረኝ በጣም ደስተኛ እሆን ነበር"አለቻት።አዎ ልትነግራት የምትችለው ይሄንን ብቻ ነው።ይሄንን ምክንያት የኮረጀችው ከአባቷ ነው።ብዙውን ጊዜ እቤቱ ውስጥ ላሉ ሰዎች ደጋግሞ ይሄንን የመድሀኒት ታሪክ ሲያወራ ሰምታለች።እናም እሷም ያንን ምክንያት ደግማ ማውራት ከጀመረች ቆይታለች።እርግጥ ከልብ በሽተዋ ጋር ተያይዞ ብዙውን ጊዜ በተከታታይ የምትወስደው መድሀኒት አላት።ግን አንደኛ መድሀኒቱን ከመተኛቷ በፊት መወሰድ የሚትችለው  ነው።እንደው ለሊት የሚወሰድ ቢሆንም እንኳን አሮራ በፈለገችው ሰዓት በመነሳት የፈለገችውን ነገር የማድረግ ችግር የለባትም።እሱም እንደሚያወራው በዚህ ጉዳይም ረድቷት አያውቅም።
ታናሽ እህቷም መጨናነቋል አውቃ"በቃ ገብቶኛል..ግን አንዳንዴ እኔ ጋር ብተኚ ለሊት ቀስቅሼሽ መድሀኒትሽን አውጥሻለሁ"አለቻት።
"የእኔ ውድ አውቃለሁ..እንዳልሺውም አልፎ አልፎ አብረን የምንተኛበት ሁኔታ እናመቻቻለን... አሁን  ተነሽ ወደሳሎን እንሂድና እራታችንን እንብላ"አለቻት።እየተሳሳቁ ተያይዘው ወደሳሎን ሄድ

ይቀጥላል......
    ሀሳብ አስተያየታችሁን 
@Tsiyon_awit አድርሱኝ
   ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@itsmetsiyearsemalj
@itsmetsiyearsemalj