Get Mystery Box with random crypto!

አሮሯ (ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል) ምዕራፍ _ሁለት ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ | አትሮኖስ

አሮሯ
(ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል)
ምዕራፍ _ሁለት
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ

መንግስቱ ዛሬ ከሶስት አመት የእስር ቆይታ በኃላ ከእስር  የሚወጣበት የነፃነቱ ቀን ነው።ለዛም እየተዘጋጀ ነው ።ለብሶት ያደረውን ቢጃማ አወለቀ። ከወገብ በላይ እራቁቱን ሆኖ ከአሮጌ ሻንጣው ውስጥ የተሻለ ያለውን ልብስ እየመረጠ ነው።መንግስቱ እስር ቤት ከመግባቱም በፊት ዘለግ ያለ ቁመትና ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው የ31 ዓመት ወጣት ሲሆን እስር ቤት ከገባ በኃላም ያንን ሰውነት በእስፓርት ፈርጣማና በጡንቻ የዳበረ እንዲሆን አድርጓታል።በዛ የደረጀ ሰውነቱ ላይ ደረቱ አካባቢ ወደ ግራ ልብ ዘንበል ያለ የሴት  ምስል ተነቅሶበታል ።ከጀርባው ደግሞ ከመቶ ሜትር ርቀት በሚነበብ ድምቀትና መጠን "አሮራ ፍቅር"የሚል ሌላ ንቅሳት አለበት።ይህቺ አሮሯ የልብ ሰው ነች።ክፍኛ ያፈቀራት የውስጥ እሳቱና የልብ ትኩሳት  ነች።ሶስት አመት የታሰረላት ሴት ። ልብሱን ለብሶ ሲጨርስ ሻንጣውን መልሶ ዘጋጋና ዝግጅቱን አጠናቀቀ።
መቼስ ለማንም ሰው ቢሆን ከእስር  መለቀቅ የተለየ አይነት ስሜት መጫሩ የሚጠበቅ ነው። ግን  ሶስት አመት በእስር ቆይቶ ከሚለቀቅ ሰው ይልቅ ሶስት ሳምንት ታስሮ ሊፈታ ያለ ሰው የበለጠ  እንደሚደሠትና በመፈታቱ ፈንጠዝያ ተሰምቶት አምላኩን እንደሚያመሠግን  ብዙ ሰው አያውቅም።አንድ ሰው ሶስት ሳምንት እስር ቤት ቢያሳልፍ እስር ሳይሆን እረፍት ነው ሚሆንለት።አዲስ ልምድ ያገኝበታል ፣ጥቂት ማሰቢያ ጊዜ... የተወሰነ መረጋጊያ ስፋራ  አግኝቶ  ከነበረበት የህይወት  ግርግር ገለል በማለት ከራሱ ጋር ስብሰባ እንደተቀመጠ ነው የሚቆጠረው እና ከዛ  ሲለቀቅ ከሞላ ጎደል ሁሉን ነገር በተወበት ቦታ  እንደነበረው ነው የሚጠብቀው።።እንዲህ እንደ መንግስቱ ሶስት አመት የታሰረ  ሰው ግን ትፈታለህ ሲባል ጭው የሚያደርግ ብዠታ ውስጥ ነው የሚገባው። "ተፈትቼስ እንዴት ነው የምሆነው?ምን ሰርቼስ እኖራለሁ?"ሲል ይጠይቃል።አዎ  አሁን  መንግስቱ ደጋግሞ በአእምሮ እያመላለሳት ያለውን ጥያቄ ብዙዎቹ የእሱ ቢጤ ከረጅም እስር በኃላ የሚፈቱ ታራሚዎች ሁሉ ይጠይቁታል።
መንግስቱ  ሶስት አመት በእስር በማሳለፉ ምክንያት ከስራ ተፈናቅሏል።አሁን ከእስር እንደወጣ የድሮ መስሪያ ቤቱ ሄዶ ወደስራዬ መልሱኝ ብሎ ቢጠይቅ ከመልሳቸው ቀድሞ ሳቃቸው እንደሚያመልጣቸው እርግጠኛ ነው።ለአመታት ባንክ ደብተሩ ላይ አጠራቅሞት የነበረውን ብርም አንድ ሁለት እያለ አውጥቶ ጨርስታል።በተለይ በተከሰሰበት ወንጀል ከ10-15 አመት  እንዲቀጣ ትግል ያደረግበት የነበረውን በአሮራ አባት የተቀጠረው የከሳሽ ጠበቃን  በመፋለም ከተራዘመ አሰልቺ ክርክር  በኃላ ወደ አምስት አመት እስር ዝቅ አስደርጎ ለማስወሰን በአመክሮም በሶስት አመት ለመውጣት  ላስቻለው  ጠበቃው ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ  ከፍሏል።

አሁን  ይህን ሁሉ እያሰበ ያለው እስር ቤት ግቢ ውስጥ  ሆኖ ሻንጣውን  በቀኝ ጎኑ አስቀምጦ በእጅ ላይ ያለውን የአሮሯን ፎቶ እያሻሸና  በአትኩሮትና በናፍቆት እያየ" ፓሊሶቹ ናና ውጣ" እስኪሉት በመጠበቅ ላይ እያለ ነው።ይህን ፎቶ ለአንድ ሚሊዬን ጊዜ  ነው  እያየው ያለው ።አሮሯ የጥቁር ፈርጥ ዕንቁ መልክ ያላት ዝነኛ እና ቆንጆ ልጅ ነች። ብዙ ጊዜ ኮስታራ ግን ደግሞ ከቀናቶች አንድ ቀን እንደው ተሳስታ ፈገግ ስትል የጥርሶቾ ንጣት ከፊቷ ጥቁረት ጋር  እና ከአይኖቾ ፍካት ጋር ያለቸው ህብራዊ ስምምነት እንደው ልብን ድንዝዝ ወይም ፍስስ የሚያደርግ ልዩና አጠቃላይ ሁለንተናውን  የማቅለጥ ኃይል ያላት አስማት የሆነች ወጣት ነች።
ይሄን ሁሉ ስለእሷ መልክና ቁመና ያጠናው ፍቅረኛው አድርጎ ቀርቦትና  እርቃን እሷነቷን እያገላበጠ ስላየ   አይደለም። በርቁ ስለሚያፈቅራት ነው።ባታስበውም ያለማቋረጥ ስለሚናፍቃት ነው።የለሊት ህልሙና የመላ ህይወቱ እቅድ ስለሆነች ቀኑንም ሆነ ሌቱን በአእምሮ እየተገለባበጠች ስለምታሳልፍ ነው።

አሁን በኪሱ ጥቂት ገንዘብ አለው።ይሄን ገንዘብ  እዚሁ ወህኒ ቤት የእንጨት ስራ በመስራት ካገኘው ገንዘብ የቆጠበው ነው።ይሄንን ሞያ እዚሁ እስር ቤት የተማረው ነው።ሲወጣም ምን አልባት እራሱን ሊያኖርበት የሚችለው   የተሻለው ተስፋው ይሄ ሞያ ነው። ዘመዶቹም ጓደኞቹም ከታሰረ በኃላ ለስድስት ወር ያህል እንደነገሩ በተንጠባጠበ ሁኔታ ከጠየቁት በኃላ ቀስ በቀስ እግራቸውን ሰብሰብ አድርገው ጠፍተዋል።እናም እረስተውታል። እናትና አባቱም ከረጅም ጊዜ በፊት ነው የሞቱት።በዚህም የተነሳ  አሁን የሚያስታውሰውና እየናፈቀ ያስቸገረው አንድም ሰው በምናብ የለም።ከአሮሯ በስተቀር ሁሉንም ረስቷቸዋል።አዎ አሮሯ ህመሙ ነች።አሮሯ ናፎቆቱ ነች።አሮሯ ረሀብ ነች።አሮሯ በህይወቱ የሆነ ጎኑ እንዲበሰብስበት ያደረገች ..የሆነ ገኑን ደግሞ  ሻማ ለኩሳ የሚንቦገቦግ ብርሀን በውስጡ እንዲረጭ ያደረገች  ሴት ነች..አሮራ።እና ከዚህ እስር ቤት በመውጣቱ ደስ የሚሰኝበት አንድና ብቸኛ ምክንያት  ለመጨረሻ ጊዜ የዛሬ ከሶስት አመት ከመታሰሩ በፊት አይቷት የነበረውን አሮሯን  ዳግመኛ ለማየት ብቻ ነው።እርግጥ እሷ ባለችበት አካባቢ 500 ሜትር በላይ እንዳይቀርባት  በፍርድ ቤት  የተጣለበትን  ገደብ አሁንም አልተነሳለትም።ቢሆንም ከዚህ ይውጣ እንጂ   ለዛ የሆነ መፍትሄ ያበጅለታል።"አሁን ምን ያህል አድጋ  ?ምን ያህልስ ወፍራ ወይም ከስታ ይሆን?"ሲል እራሱን ጠየቀና ፈገግ አለ።

"መንግስቱ ኃይሉ ...መንግስቱ ኃይሉ..."የሚል የፓሊስ የጥሪ ድምፅ  ከትካዜው አባነነው።
"አቤት"
"ዕቃህን  ያዝና ተከተለኝ...ልትወጣ ነው።"ሲል ማይቀረውንና አስፈሪውን የምስራች አበሰረው።ቶሎ አለና ፎቶውን ደረት ኪሱ በመክት ሻንጣውን ይዞ የስር ቤት ጓደኞቹን በየተራ እያቀፈ ለመጨረሻ ጊዜ ተሠናብቶ  ሻንጣውን በመያዝ ፓሊሱን ተከትሎ ወጣ። ወደአስተዳደር ቢሮ ነው ያመሩት።ከእስር ነፃ መለቀቁን የሚገልፅ ደብዳቤ ተቀበለና ከግቢው እንዲወጣ ተደረገ።
አሁን እዚህ ቦታ ሄዳለሁ የሚለው የተለየ ስፍራ የለውም። ወደድሮ ሰፈሩም የሚሄድበት ምንም ምክንያት እየታየው አይደለም። ከወላጇቹ የወረሰውንም እቤት ከመታሰሩ በፊት ነው በረጅም ጊዜ ኮንትራት ያከራየው።ስለዚህ ለጊዜው የእሱ አይደለም። አሁን ማድረግ የሚችለው ባገኘው በመጀመሪያው ታክሲ ወይም ባጃጅ ውስጥ ገብቶ ይሄን ሰፈር መልቀቅ ፤ከዛ ታክሲው በሚቆምበት የመጀመሪያው ወይም ሁለተኛ ፌርማታ ላይ መውረድና በአካባቢው ዞር ዞር ብሎ ኪሱን የሚመጥን ቤርጎ ፈልጎ መከራየት ...ከዛ አንድ ሁለት ቀን አርፎ መረጋጋት፣አሮሯን አፈላልጎ በሩቁም ቢሆን ማየት ... ከዛ ስራ ፈልጎ መቀጠር...እንደዛ እንደዛ እያለ ቀስ በቀስ ህይወቱን በአዲስ መልክ  ማስተካከል ...አዎ እቅድ እንደዛ ነው።

ከማረሚያ ቤቱ ቅፅር ግቢ መቶ ሜትር ተጓዘና ታክሲዎች እና  ባጃጆች የሚራኮቱበት ስፍራ ደረሰ።ወደ ታክሲ  ልግባ ፈይስ ወደ ባጃጅ ?እያለ ከራሱ ጋር ሙግት ገጥሞ ባለበት ሰዓት ከወደቀኝ በኩል  ደመቅ ያለ የመኪና ክላክስ  ጥሪ ሰማ።ሳያስበው ዞር ብሎ እይታውን ወደዛ ሲልክ  በመቶ ሜትር ርቀት አጥር ታካ የቆመች የተወለወለች አዲስ አይጥማ ከሮላ መኪና ተመለከተ።በመኪናው የኃላ ገቢና የተቀመጠች አንድ ብስል ቀይ ሴት  አንገቷን በመስኮት አስግጋ በማውጣት  እጆቾን ወደእሱ እያርገበገበች ወደ መኪናዋ  እንዲመጣ ምልክት እያሳየችው ነው።ግራ ገባው።ወደጀርባው ዞር ዞር  አለና ሌላ ሰው ይሆን እንዴ የምትጠራው? የሚለውን ጥርጣሬ ለማረጋገጥ ሞከረ።ማንም ከጀርባው