Get Mystery Box with random crypto!

አሮሯ (ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል) ምዕራፍ _አንድ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ አ | አትሮኖስ

አሮሯ
(ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል)
ምዕራፍ _አንድ
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ

አሮራ  ውብ ነች ከማለት ይልቅ ጣኦት ትመስላለች ማለት ይበልጥ ይገልፃታል።ብዙውን ጊዜ የውበት መስፈሪያውን ወይም መለኪያውን በተመለከተ አጨቃጫቂ የሆነ ክርክር አለ።አንድ ማህበረሰብ ጋር ደልደል እና ደርፎጭ ያለች ሴት ውብ ስትባል በሌላው ማህበረሰብ ደግሞ ሰበር-ቅንጥስ የምትል ሴት ውብ ነች ይባላል።በግለሠብ ደረጃም እያንዳንድ ሰው የራሱ የሆነ ቴስት አለው። አሮራ ግን ለማንም ሰው አስማሚ የውበት ሚዛን ነች።ሴቶች በቅናት ወንዶች በመጎምዠት  እኩል የሚያደንቋት ሴይጣንም መላዕክም እኩል የሚስማማባትና ሳይጨቃጨቅ የሚመርጣት የውበት ጣኦት ነች።የወንዶችን  የፍቅር ስሜታቸውንና የወሲብ ረሀባቸውን በአንድ ቅፅበታዊ እይታ የማናጋት ልዩ ኃይል ያላት አደገኛ ሴት ነች፤በዛ ላይ ተስረቅራቂና ተንሳፋፊ ድምፅ ያላት ታዋቂ ወጣት ድምፃዊ ነች።
አሮራ እድሜዋ 21 ነው።የምትኖረው ኑሮ ከላይ በድፍኑ ሲታይ እጅግ የቅምጥልና  ፍፅም የምቾት ነው።አባቷ ከተማዋን  ከሚዘውሩ ጥቂት  ቱጃሮች መካከል አንደኛውና ዋነኛው ነው።በዛ ላይ በእሷ ህይወት ውስጥ ፍፁም አድራጊ ፈጣሪ ከመሆኑም በላይ ማናጀሯ  ነው።በእሱ በኩል ካልሆነ ማንም ሰው ወደዚህቺ አማላይና ፅፀ-ወሲብ ወደ ሆነች ልጅ  መጠጋት አይችልም።ለሠላምታ እንኳን እሱ መፍቀድ አለበት።
አሮሯ አሁን የገዛ መኝታ ቤቷ አልጋዋ ጠርዝ ላይ ቁጭ ብላለች።ፊት ለፊቷ የልቧ ሰው የሆነው ተወዳጅ አጎቷ እዝራ ቁጭ ብሎ እያጫወታት ነው።እዝራ አጎቷ ብቻ አይደለም ከ20 ዓመት በላይ የእድሜ ልዩነት በመሀከላቸው ቢኖርም ብቸኛውና ተወዳጅ ጓደኛዋም ጭምር ነው።ለሰው የሚነገር ሆኖ ለእሱ የማትነግረውና ከእሱ ጋር ማትማከርበት አንድም ጉዳይ የለም።ክፋቱ ከእሷ ነገሮች አብዛኞቹ ለማንም መነገር የማይችሉ አሰቃቂ ጨለማ ምስጢሮች በመሆናቸው እሱም ቢሆን እንኳን ስለእሷ የማያውቃቸው ነገሮች ከግማሸ ይበልጣሉ።
እዝራ አባቷ ካለምንም ገደብና ክልከላ እንደፈለገች እንድትገናኘው የሚፈቅድላት ብቸኛው ሰው ነው።ምን አልባት በጣም የሚወደው ብቸኛ ታናሽ ወንድሙ ስለሆነ ሊሆን ይችላል?ምን አልባትም ነገረ-አለሙን እርግፍ አድርጎ በህይወት ተስፋ የቆረጠ ጉዳት- አልባና ጥቅም-አልባ ሰው አድርጎ ስለሚያስበውም ሊሆን ይችላል።

"ሮሪ ስምሽን አሮራ ብሎ ማን እንዳወጣልሽ ታውቂያለሽ?"ሲል ጠየቃት።
"አጎቴ አውቃለሁ አንተ ነህ።"
"ከመልክሽ በላይ አንፀባራቂ ስም ነው ያወጣሁልሽ።አሮራ ጥልቀት ያለው ብርሀናማ  ስም ነው።ቀለል አድርገሽ ስትተረጉሚው  በማለዳ  ከእንቅልፍሽ  ተነስተሽ ከነቢጃማሽ በረንዳ ላይ ቁጭ እንዳልሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ብልጭ ስትል የምታያት ልብ ሰንጣቂ  የፀሀይ ብርሀን ማለት ነው።በሌላ ጎኑም ማታ ለመጨረሻ ጊዜ ውስጥሽ በፍራቻ እየተሸበረ እያየች ግን ደግሞ ተሠናብታሽ የምትጠልቀው የመጨረሻዋ የፀሀይ ፍንጣቂ  ማለት ነው።"
"አጎቴ ስሜ ብዙ ትርጉም ያለው ነው..አውቃለሁ ደጋግመህ ነግረኸኛል።"
"አዎ ነግሬሻለሁ።የፀሀይ አካል የሆኑ የኤሌክትሪክ ቻርጆች (ፓርቲክሎች) በምድር አካባቢ  ከሚገኙ ናይትሮጂን እና ኦክስጅንን ከመሰሉ ጋዞች ጋር  ሲዋሀድ   የሚፈጠርና  በምድር  ከፍታ(ሰማይ) ላይ በሚፈጠር በአረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ቀይና ነጭ ቀለም የሚገለፅ የተፈጥሮ ክስተት ማለትም ነው።ሌላውጨደቡብ እና ሰሜን ዋልታ ጫፍ ላይ ያለች ውብና ተወዳጅ የፀሀይ ብርሀንም ብለሽ ብትተረጉሚው ትክክል ነሽ።"
"አጎቴ ይሄንን ስም ለእኔ መሰየም የለብህም ነበር።ዝብርቅርቅ ትርጉም ያለው ስም ሰጥተኸኝ ዝብርቅርቋ የወጣ ልጅ ሆኜ ቀረሁ።" አለችው።
"ወድጄ ይመስልሻል ይሄን ስም የሰጠሁሽ?እንዲህ አሁን ባለሽበት አፍላ እድሜ ላይ ጣሊያን እያለሁ  ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ልቤን የከፈትኩትና በእንብርክኬ እስክሄድ ያፈቀርኩት አሮራ የተባለች  ስፔናዊት ልጅን ነበር...."
ንግግሩን አቆመና ኪሱን በረበረ...የሮዝማን ሲጋራ ፓኮውንና ላይተሩን ከኪሱ አወጣና  አንድን ከውስጡ መዞ በመለኮስ የሲጋራውን ፓኮና ላይተሩን ፊት ለፊት ጠረጴዛው ላይ ጣል አድርጎ  የለኮሰውን ማብነን ጀመረ...እዝራ ይሄንን ታሪክ ለአሮራ ሲነግራት   ምን አልባት ለአስር ሺኛ ጊዜ ሊሆን ይችላል ።እሱም ስለፍቅረኛው አሮሯ  አውርቶ አይደክመውም እሷም አይ ይሄኛውን ታሪክን ከመቶ ጊዜ በላይ ነግረሀኛል አሁን ሰለቸኝ መስማት አልፈልግም ብላው አታውቅም።እንደዛ የማትለው ደግሞ እሱን ማስቀየምና ማስከፋት ስለማትፈልግ ብቻ አይደለም በእሱ የማፍቀር መጠንና ጥልቀት ስለምትቀናም ጭምር  ነው።በእሱ መጠን አፍቅሮ በእሱ መጠን መሠቃየት ስለሚያምራት ነው።እንደዚህ እንዴት ልታስብ እንደቻለች ለራሷም ይገርማታል።እንደእሱ ለይቶላት ህይወቷን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጋ በመተው የሙሉ ጊዜ እብድ አትሁን እንጂ ከእሱ የበለጠ የውስጥ ህመም፤ ከእሱ የበለጠ የልብ መሠባበርና የስሜት መፈረካከስ ያጋጠማትና በዛም የተነሳ የማይድን በሽታ ታቅፋ የምትኖር ልጅ  ነች፣ለዛውም በዚህ ጨቅላ ዕድሜዎ። እሱ ግን ስለዛ መራር የስደት አለም የፍቅር ታሪኩ ለእሷም ሆነ ለሚያዳምጠው ለማንኛውም ሰው ሲያወራና በናፍቆት እንባ በጉንጮቹ እያንጠባጠበ በኩራት ሲተርክ ደስታውንም ሆነ ሀዘኑን ከሌላው ሲያጋራ ይኖራል ።በዛም እራሱን ያክማል።እሷ ግን እንደዛ አይነት እድል የላትም።ስለፍቅር ታሪኳ ለራሷም የማውራቱ ሞራልም ሆነ ድፍረቱ የላትም።ስሜቷን አዳፍና ህመሞን በውስጧ ቀብራ እህህ ማለት ብቻ ነው ያላት እድል።እስከአሁን ግን እንዴት እንደእሱ እንዳለየላትና እንዳላበደች ይገርማታል...አንድ ቀን ግን የእሱ እጣ እንደማይቀርላት እርግጠኛ ነች።ከአንድ ቤት ሁለት እብድ።

እዝራ ሲጋራውን ግማሽ ድረስ ከማገ በኃላ ወሬውን ካቆመበት ቀጠለ"አሮራ ልክ እንደአንቺ ውብ ነበረች.. ጥርት ያለ ድምፅ፣ልስልስ ቆዳ፣ ስስ ልብ...ሰው ሳይሆን ከሰማያዊው መንደር ጠፍታ በስህተት በምድር እየኖረች ያለች መላአክ ስለምትመስለኝ አብዝቼ እሳሳላት ነበር...ስስማት እንኳን ከንፈሯን አሳምማት ይሆን ?እያልኩ እጨነቅ ነበር።በሆነ ንግግሬ ግንባሯን ከቋጠረችማ በቃ  ክፍሌ ገባና በራፌን ዘግቼ በጉልበቴ ተንበርክኬ ለሠራሁት ሀጥያት እግዜር ይቅር እንዲለኝ እፀልይ ነበር።በእሷ ምክንያት የድሮ ነገሬን ሁሉ ረስቼ ነበር።ከኢትዬጰያ መሄዴን ረሳሁ።ዘመዶች እንዳሉኝ እረሳሁ።ጥቁር መሆኔንም እረሳሁ።..በቃ እኔ የአሮራ ፍቅር ብቻ ሆንኩ።ለመጋባት ወሰንን፣ እቤት ገዛን ፣ሁሉ ነገር ተዘጋጀን ...ግን ለሰርጋችን አንድ ወይም ሁለት ቀን  ሲቀረን እሷ ከጎደኞቾ ጋር እቃ ለመግዛት የሆነ ሱፐርማርኬት እንደገባች አጋጣሚ ሆኖ  የሆኑ ዘራፊዎች በቦታው ተከሰቱ፤ ፓሊስ በአካባቢው ስለነበረ መታኳስ ጀመሩ ፤ከአንድ አስጠሊታ ሽጉጥ የወጣች አስጠሊታ ጥይት የእኔ መልአክ  ጉሮሮ ውስጥ ተሠነቀረች።ከዛ አሮራ የምትጠልቀው ፀሀይ ሆነች....ከዛ በኃላ እንደምታውቂው  ሁለ ነገሬ ፈራረሰ ..መስራትም መማርም አልቻልኩም። ከአስር አመት ቆይታ  በኃላ ሳልወድ  በግድ  ግማሽ ልቤና ግማሽ ነፍሴ ታሞ ወደሀገሬ ተመለስኩ።ስመለስ ወንድሜ እንዳገባ እንኳን ሳላቅ አንቺን የመሰለች ፀሀይ ልጅ ወልዶ ጠበቀኝ ።በወቅቱ አምስት አመትሽ ነበር ።በጣም ነው የወደድኩሽ ...ሰው ሁሉ ቢያስጠላኝም አንቺን ግን ወደድኩሽ። ከዛ አንቺም የምታንፀባርቂ ፀሀይ ስለሆንሽ እግረመንገድም ለፍቅሬ መታወሻ ለማድረግ...ማለቴ በየቀኑ ደጋግሜ  ስሟን ለመጥራት እድሉን ለማግኘት ስል  አሮራ የሚል ስም