Get Mystery Box with random crypto!

#ህያብ : : #ክፍል_አምስት ፡ ፡ #ድርሰት_በኤርሚ አንዳንዶች ለወደዱት ብቻ ጥሩ ይሆናሉ... | አትሮኖስ

#ህያብ
:
:
#ክፍል_አምስት


#ድርሰት_በኤርሚ


አንዳንዶች ለወደዱት ብቻ ጥሩ ይሆናሉ.... አንዳንዶች ደግሞ እንዲሁ በተፈጥሯቸው ጥሩነትን ይታደሉታል። ቢኒ እንደዛ ነው መልካምነትን የታደለ ጥሩ ልብ ያለው ልጅ ነው። ድሀ ወይም ሀብታም፣ ክርስቲያን  ሙስሊም ወይም ሌላ እምነት፣ ቆንጆ ወይም መልከ ጥፉ፣ ቢኒ ጋር መስፈርት አይደሉም። ለሁሉም እኩል ፍቅርና እንክብካቤ ሲሰጥ ታዩታላችሁ..... ግቢ ውስጥም ሆነ ከተማ ውስጥ ያሉ የበጎ አድራጎት ስራዎች አያመልጡትም.....

"ቢኒዬ ግን እርግጠኛ ነህ እዚህ ብሆን አረብሽህም.." እረጅም ሰዓት ተጨቃጭቀን እስከፈለኩ ድረስ ቤቱ እንድኖር ከነገረኝ በኋላ ሀሳቡን ቢቀይር ብዬ ጠየኩት

አጠገቤ መጣና ቁጭ አለ.... እጆቹን ልኮ ሁለት እጆቼን ያዘና አይን አይኔን እያዬ "ህዩ አንቺ ጓደኛዬ ነሽ... ጓደኝነት ውስጥ ደግሞ እኔ የሚባል ነገር የለም በተለይ እኔ ካንቺ እኔን ላስቀድም አልችልም ምክንያቱም......" ከንፈሮቹ ተንቀጠቀጡ።

"ምክንያቱም ምን ቢኒዬ" እጄን ለቆ ተነሳና ጀርባውን ሰቶኝ ከመስኮት ዳር ቆመ።

"ህያብ ጊዜ የነገሮች ጌታ ነው ብዬ አምናለሁ... እናም ሁሉም በጊዜው ሲሆን ደስ ይላል። አሁን ከኔ ምክንያት በላይ ያንቺ ሁኔታዎች ናቸው መስተካከል ያለባቸው...." ክትክት ብዬ ሳቅሁ... የእብደት ሳቅ
ከሳቄ በኋላ

" እስኪ ንገረኝ ምኑን ነው የምታስተካክለው.... እናቴን ልጄን ወይስ ከሀዲው ባሌን ማንን መልሰህ ልታመጣልኝ የምትችል ይመስልሀል..." ድጋሚ አመመኝ... መቋቋም አቃተኝ... በሁለት እጄ ጭንቅላቴን ጥፍንግ አድርጌ ያዝኩት። የሆነ ሽክርክሪት ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኛል ዥውውውውውውውው.... ሳቅ ከዛ ደግሞ ዝምምምምታ.... ከዛ ደግሞ ሌላ ሳቅ.... ይሄኛው አለም የተሻለ ይመስለኛል።

የሆነ ሰው አፌ ውስጥ የሆነ ነገር ለማስገባት ታገለኝ አልከለከልኩትም ዋጥኩት ከዛ ሁሉም ነገር ፀጥ አለ።

ምን ሰዓት እንደተኛሁ ባላውቅም ራሴን ጋቢ ለብሼ ሶፋ ላይ ተኝቼ አገኘሁት። ቀና ብዬ ተስተካክዬ ቁጭ ስል ቢኒን ከእግሬ ስር ቁጭ ብሎ መፅሀፍ ቅዱስ ሲያነብ አየሁት።

"ይቅርታ ቢኒ ረበሽኩህ መሰለኝ.." መፅሀፍ ቅዱሱን ዘግቶ ከሳመ በኋላ የኔንም ግንባር ነካ አደረገበትና ተነስቶ አስቀምጦ ተመለሰ።

"ሁለተኛ እንደዚህ እንዳትይኝ ማስቸገር ገለመሌ የሚባል ታሪክ የለም ያራቅሺኝ ነው የሚመስለኝ..."

"እሺ በቃ አይለመደኝም..... ይልቅ እስኪ ንገረኝ የውጪ ቆይታህ እንዴት ነበር የተመለስከውስ መች ነው"

"ቆይታዬን በደፈናው ጥሩ ነበር ልበልሽ መሰለኝ። የተመለስኩት ሁለት ወር አካባቢ ሆነኝ ግን ቀጥታ ቤተሰብ ጋር ክፍለ ሀገር ነው የሄድኩት ከተመለስኩ ገና ሳምንትም አልሞላኝ"

"እና ለምን ልትፈልገኝ ወደ ቤት አልመጣህም..." ክፍት ነው ያለኝ ምንም እንኳን የሱን ስም ሲሰማ ባሌ ቢናደድም ቢኒ ላጣው የማልፈልገው ጓደኛዬ ነው እና እንዴት...

"ወዳንቺ ጋር እየመጣሁ እያለ እኮ ነው መኪና ውስጥ የገባሽብኝ"

"ኦ እሺ እንደዛ ከሆነ"

"አልተዋጠልሽም አይደል ህያቤ ብዙ ጊዜ እንዳልደወልኩልሽ አውቃ..." አቋረጥኩት

"ምን ብዙ ጊዜ ትላለህ ከሄድክ ጀምሮ ሁለቴ ብቻ እኮ ነው የደወልከው.... እናም አልዋሽህም ተቀይሜሀለሁ"

"ምክንያቴን ስታውቂ እንደምትረጂኝ ስለማውቅ ችግር የለውም.... የሆነ ነገር መብላት አለብን ምን ትፈልጊያለሽ..." አለኝ ወደ ኪቺን እየገባ

"ፍላጎትሽን አትናገሪም ካለዛ ዱባ ወጥ ነው የምሰራው ሀ ሀ ሀ" ሽርጡን አገልድሞ ብቅ አለ

" ዱባ ስራና ሶስት ቀን ውጪ አሳድሬ ነው የማበላህ.... አንተ ደግሞ ሼፍ መስለህ የለም እንዴ"

"ነይ አሁን ተነሺ ቢያንስ ዱባውን እንኳን በመክተፍ አግዢኝ" ከስሙ ጭምር እንደምጠላው ስለሚያውቅ እኮ ነው ...ዱባን....

"ሀ ሀ ሀ አንተ እብድ ትቀልድብኛለህ አ" ከረጅም ጊዜ በኋላ ሳቅሁ
......

፨፨፨ ፨፨፨፨ ፨፨፨፨
ጎንደር ዩንቨርስቲ ሁለተኛ አመት

"ቢኒ ዮናታንን እወደዋለሁ ከዚህ በላይ መቋቋም አልችልም እናም እነግረዋለሁ"

"ህያብ ዮናታንን ታውቂዋለሽ.... እሺ አለሽ እንበል ከዛ እነኝህን ሁሉ ሴቶች ትቶ ካንቺ ጋር ብቻ የሚሆን ይመስልሻል"

"አላውቅም ግን እድሌን ልሞክር.."

"ተይ ህያብ ይቅርብሽ"

"አይሆንም ቢኒ እድሌን እሞክራለሁ" ይሄን ሁሉ የምንጨቃጨቀው ዮናታን የሚያመሽበት ጭፈራ ቤት በር ላይ ሆነን ነው። ወደ ውስጥ ገባሁ... አይኔን ዞር ዞር እያደረኩ ፈለኩት ጥግ ሶፋ ላይ ከአንዲት ሴት ጋር የተሰፋ ያክል ተጣብቋል.... በደንብ ቀረብኳቸው... አንገቱ ስር ስማው ቀና ስትል አይን ለአይን ተገጣጠምን... የትናዬት....

ደንዝዤ አንደቆምኩ የሆነ ሰው እጅ ትከሻዬ ላይ አረፈ "የኔ ቆንጆ በዛኛው በኩል ቦታ አግኝቻለሁ.... እንሂድ አይደል"  ውጪ ቆይ አላልኩትም ነበር.... ቢሆንም ግን ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው የደረሰው።

"አየሽ አይደል በራስሽ ላይ ምን እያመጣሽ እንደሆነ"

ሲጀመር እሱን ብቻውን አገኘዋለሁ ብዬ ማሰቤ ነው የኔ ጥፋት እርር ድብን ብሽቅቅቅቅ ብያለሁ እኮ

"አረጋጊው እንጂ ውዷ ጉበትሽን መትፋት አማረሽ እንዴ"

"ተወኝ ባክህ ልጠጣበ" ከነ ጠርሙሱ አንስቼ ለመጠጣት ስሞክር ከእጄ ቀማኝና

"ነይ በቃ እንሂድ ግቢ ይዘጋል" አለኝ

"የትም አልሄድም ተወኝ"

"ይሄንን ነው መፍራት... ኧረ ህያብ በፈጠረሽ..." ጠርሙሱን ተቀብዬው እየተንገዳገድኩ እነሱ ወዳሉበት ቦታ ሄድኩ....

"ህያብ አንቺ ህያብ" የእናቴ ድምፅ መሰለኝ.... እየጠራችኝ ነው።

"አቤት እማ መጣሁ" ብዬ ከተኛሁበት ለመነሳት ስሞክር ሀይለኛ ራስ ምታት አናቴን ይዞ እየፈለጠኝ ነው። ጭንቅላቴን በሁለት እጄ ጥፍንግ አድርጌ ይዤው ከቆየሁ በኋላ አይኔን በደንብ ከፍቼ ሳይ ያለሁት እናቴ ቤት አይደለም....

ከፊት ለፊቴ ቢኒ ተቀምጦ የማደርገውን ነገር ያያል።

"ኡፍፍፍፍ የት ነው ያለሁት ምን ተፈጥሮ ነው.... ቆይ እማዬ የጠራችኝ አልመሰለኝም.."

"ባክሽ እኔ ነኝ የጠራሁሽ ክፍል ልቀቁ እየተባልን ነው ተነሺ..." ቢኒ እንደዚህ አውርቶኝ አያውቅም....

"ምንድነው ቢኒ ችግር አለ እየተነጫነጭክ እኮ ነው ምነው ማታ አስቀየምኩህ እንዴ.... ማታ....ቆይ ቆይ እንዴት ወደዚህ ልመጣ ቻልኩ? ማነው ያመጣኝ? ማለት ምን ተፈጥሮ ነው?..." የጥያቄ መአት አከታተልኩበት

"በመጀመሪያ ተነሽና ታጠቢ ከዛ ወደ ግቢ እንመለስና ዶርም ገብተሽ እረፍት አድርጊ ከዛ ተገናኝተን ጥያቄዎችሽን እመልስልሻለሁ እስከዛው ትዝ የሚልሽ ነገር ካለ ራስሽ ጥያቄሽን መመለስ ትችያለሽ" እንዴ ምንድነው ጉዱ ቢኒ እንደዚ ከረር ብሎ አይቼው አላውቅም ጭራሽ የማላውቀው ሰው ነው የሆነብኝ። ተጨማሪ ጥያቄ ሳልጠይቅ ጭንቅላቴን ደግፌ እየተጎተትኩ መታጠቢያ ቤት ገባሁ።
ሰውነቴ ስብርብር ያለ ያክል እየተሰማኝ ታጥቤ ጨረስኩ

፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨

"አንተ ቢኒ ግን አልተኛህም እንዴ አይንህ እኮ በርበሬ ነው የሚመስለው" ወደ ግቢ እየሄድን ጠየኩት