Get Mystery Box with random crypto!

'ይቅርታ ዶክተር ፋሲል እናቷ ልትፈቅድልን አልቻለችም' በሆስፒታል አልጋ እየገፉኝ እየወሰዱኝ እያ | አትሮኖስ

"ይቅርታ ዶክተር ፋሲል እናቷ ልትፈቅድልን አልቻለችም"
በሆስፒታል አልጋ እየገፉኝ እየወሰዱኝ እያለ አይኔን ለመግለጥ ሞከርኩ እናቴን በጭላንጭል አየሁዋት የአልጋውን ጠርዝ ይዛ በለቅሶ እየተከተለችን ነው የሆነ ክፍል አስገቡኝና በሩን ዘጉት ለመጨረሻ ጊዜ የሰማሁት የእናቴ ድምፅ

"ልጄን አድኑልኝ.....ልጄን"

እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ይሰማኛል
"ከሁለት አንዳቸው አይተርፉም ካልፈጠንን ግን ልጅቷንም በሆዷ ያለውንም ነው የምናጣው... ፍጠኑ.... "

በጭንቅ ግራ ቀኝ ስወዛወዝ ከፊት ለፊቴ ያለው የተሳፋሪ ወንበር ላይ ተደፋሁ። ግንባሬን የመታኝ ወንበር ካለሁበት አስፈሪ ህልም ቀሰቀሰኝ.....ተመስገን በህይወት አለሁ።

እጄን ሰድጄ ሆዴን ዳበስኩት አሁንም ያቺ ትንሽዬ እብጠት ነው ያለችው።

ረዳቱ ጮክ ብሎ"ለምሳ ሀያ ደቂቃ ከዚህ በላይ መቆዬት አይቻልም" እለ። እናቴን ዞር ብዬ ሳያት ወደኋላ ለጠጥ ብላ ተኝታለች። እሷም እንደኔ አስፈሪ ህልም እያየች ይሆን? ትከሻዋን ይዤ ወዝወዝ ሳደርጋት ነቃች።

አውቶብሳችን ሲቆም ወርደን ምሳ በልተን እና የሚያስፈልገንን ሸማምተን ተመለስን። ከኔ በላይ እናቴ ፊት ላይ የማየው ተስፋ እና ደስታ አቅሌን ሊያስተኝ ደርሷል። ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠን አንገቴን ወደሷ ስባ እቅፍ አደረገችኝ..... ልብ ሰርስሮ የሚገባውን የእናት ጠረኗን አሸተትኩት። "አሁን ማን ሊያቆመኝ ይችላል" አልኩ በውስጤ.... ከፊቴ ደጀን ሆና ወኔ ብርታት የምትሰጠኝ.... ሀዘኔ ከኔ በላይ የሚያሳዝናት በደስታዬ የምትደሰት ችግሮቼን ቀድማ የምትጋፈጥልኝ እናት እያለችኝ..... እኮ ማን?

፧፧፧፧፧

ከወራት በኋላ

አጎቴ ያሰብኩትን ያክል አልጨከነብንም። የራሳችንን ቤት ተከራይተን እስክንወጣ አንድ ክፍል ቤትና ምግባችንን ሰጥቶን ነበር። እኛም ብዙ ጊዜ ሳናስቸግረው ገጠር ያለውን የአባቴ ቤተሰብ ማለትም የአያቶቼ ውርስ የሆነውን የእርሻ መሬት ብዙ አመት መከራዬት ለፈለገ ሰው አከራየንውና ጥሩ ገንዘብ አገኘን። እማዬ ጊዜ ሳታጠፋ ነው በብሩ ከጀበና ቡና ጋር ጠዋት ቂንጬ ጨጨብሳ እና አንዳንድ ለቁርስ የሚሆኑ ምግቦችን ማታ ደግሞ ድንች እየቀቀለች መሸጥ የጀመረችው። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ደንበኞችን ማፍራት ቻለች። ስራው ትርፋማ እየሆነ ሲመጣ የራሳችን ቤት ተከራይተን ከአጎቴ ቤት በሰላም ወጣን።

፧፧፧፧፧፧
በቀጫጫ እና ባልጠነከረ ሰውነቴ ላይ የሆዴ ትልቅነት ሲታይ ልክ በህልሜ እንዳየሁት ያስፈራል "አምላክ ሆይ ህልሜን እውን አታድርግብኝ" በልቤ ፀለይኩ

በምጥ መውለድ አትችልም ተብሎ ስለተወሰነ በቀዶ ጥገና ልጄን ወለድኩ። እነሱ ባይሉም እንኳን በምጥ አልወልድም ብዬ ኡ ኡ ነበር የምለው። ህልሜማ እውን አይሆንም

ሆዴ ውስጥ እያለ እንደ እንቅፋት እያሰብኩ እጠላው የነበረን ልጅ አምጥተው ክንዴ ላይ ሲያስቀምጡልኝ ስፍስፍ የሚያደርግ ስሜት ተሰማኝ። ሴት ልጅ ናት እናቴ ሀዘናችንን የምንረሳብሽ ስትል ስሟን ምናሴ አለቻት። ልጄ ትንሽ ጠንከር ስትልልኝ ትምህርቴን ካቆምኩበት ሰባተኛ ክፍል ቀጠልኩ። ቀናት ሳምንታትን ሳምንታት ወራትን ወራትም አመታትን እየወለዱ የአስራ ሁለተኛ ክፍል(የዩንቨርስቲ መግቢያ) ፈተናን ተፈተንኩ።

ልጄም ልክ እንደ እኔ እሳት የላሰች ጎበዝ ተማሪ ሆናልኛለች። ከሷ ጋር ስሆን ቦርቄ ያልጨረስኩት ልጅነቴ ይመጣብኛል እና ሁሌም ቢሆን ከልጄ ጋር ልጅ ነኝ። ያለፈኝን ህይወት በሷ እየካስኩ እንዳለሁ ይሰማኛል።

ነሀሴ መጨረሻ ላይ ውጤት መጣ ተባለና አየን ጥሩ ውጤት ነው ያመጣሁት ግን ሩቅ ሀገር ነው የመደቡኝ ጎንደር ዩንቨርስቲ በምፈልገው ዲፓርትመንት(ህክምና)

እናቴን እና ልጄን ትቼ እንዴት ችዬ ይህን ያክል እርቃለሁ..

ይቀጥላል...