Get Mystery Box with random crypto!

#ህያብ ፡ ፡ #ክፍል_ሶስት ፡ ፡ #ድርስት_ኤርሚ እና ሁሉም ነገር እንደዚህ ሊቀጥል ነው? አይሆ | አትሮኖስ

#ህያብ


#ክፍል_ሶስት


#ድርስት_ኤርሚ

እና ሁሉም ነገር እንደዚህ ሊቀጥል ነው? አይሆንም! እናቴም እኔም አንገታችንን ከምንደፋ የሆነ ሀሳብ በውስጤ መጣልኝ። እንደማደርገው እርግጠኛ ሆንኩ....
ቤት እንደደረስን ቁጭ አድርጋ የምክር ናዳ አወረደችብኝ ግን አንዱንም ከልቤ ሆኜ አልሰማኋትም..... እንዴት እንደማደርገው እቅድ እያወጣሁ ነበር።

ሁሌም ማክሰኞ ቀን እናቴ ገበያ ትሄዳለች። ያሰብኩትን ለማድረግ ከዚህ ቀን ውጪ የተመቸ እንደሌለ አውቃለሁ ስለዚህ ማክሰኞን መጠበቅ አለብኝ።
....
የምጥ ቀን እሁድ አለፈና ሰኞ መጣ.... ብርድ ልብሴን ክንብንብ ብዬ የተኛሁ መሰልኩ። እማዬ ቤት ውስጥ ውዲህ ወዲያ ስትል እንቅስቃሴዋ ይሰማኛል። አጠገቤ መጣችና
"አንቺ ሚጣ.... ሚጣዬ..... ሚጣ" ብላ ጠራችኝ። ባልሰማ ዝም ብያት የተኛሁ እንዲመስል ጣርኩ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤት መሄድ በጓደኞቼ እና በሌሎች ተማሪዎች መዋረድ አልፈልግም።

እኛ ላለንበት ማህበረሰብ ይሄ ከባድ ነገር ነው። መደፈሬን የሚያውቀው ሳይቀር
"የወይንሸት ልጅ ዲቃላ አረገዘች.... ድሮም ሴት ያሳደገው" ብለው እኔን ብቻ ሳይሆን ብርቱዋን እናቴንም ጭምር ነው የሚሰብሩብኝ

"አንቺ ሚጣ... ተነሽ እንቅልፍ እንዳልወሰደሽ አውቃለሁ..." አለችኝ። ምንም ማምለጫ የለኝም ፊቴን ቀስ ብዬ ገለጥኩና አጠገቤ የቆመችውን ድንቅ ሴት ከታች ወደላይ አየኋት..... እምዬን.... እናቴን። ጎንበስ ብላ በስስት እያየችኝ ነው። ከተኛሁበት ቀና ብዬ ቁጭ እንዳልኩ አጠገቤ መጣችና ጥምጥም ብላ አቀፈችኝ።

"ልጄ የኔ ስስት.... አለሜ እኮ አንቺ ብቻ ነሽ.... በዚህ እድሜሽ እንደዚ ስብር አትበይብኝ። ምን ያክል እንደሚያም ካንቺ በላይ ይገባኛል። ህመምሽ ካንቺ የበለጠ እኔን ያመኛል። ነገር ግን ቁጭ ብለን በእንባ እና ያለፈውን መራር ጊዜ በማሰብ ነጋችንን አናጨልመውም ልጄ ትማሪያለሽ ልክ እንደምትመኝው ዶክተር ትሆኛለሽ..."

"እማ እኔ ትምህርት ቤት አልሄድም" እንባዬ ከአይኔ ክልብስ አለ። እየተንሰቀሰኩ አለቅስ ጀመር።
"አይ እንግዲህ የምን ለቅሶ ነው" አለችኝ ቆጣ ብላ ይሄን ቁጣዋን አውቀዋለው ምናባሽ.... የታባሽ..... የሚባለው አይነት ቁጣ አይደለም። ቃሏ እና ፊቷ ላይ "መፍትሄ አለው" ከሚል መልዕክት ጋር ነው የምትናገረው። ለቅሶዬን አቁሜ የምትለውን ለመስማት ተመቻቸሁ።

"ልብ ብለሽ ስሚኝ የኔ ልጅ...."
በሚገባኝ ቋንቋ አስረዳችኝ።

ሙሉ ለሙሉ ነው ሀሳቤን ያስቀየረችኝ የኔ እቅድ የነበረው ገበያ ስትሄድልኝ የገዛሁትን የአይጥ መርዝ ጠጥቼ ይህችን አለም መሰናበት ነበር። ንቁዋ እናቴ ግን እቅዴን ሁሉ ቀድማ ደረሰችበት። አዲሱን እቅዷን ከነገረችኝ በኋላ እንዲህ አለችኝ።

" ያቀድሽውን ሁሉ ደርሼበታለሁ ሚጣ.... መርዝ ልትጠጭ ነበር አይደል" ክው ብዬ ነው የደነገጥኩት
........

"እንዴት ሆኖ ከኔና ባለሱቁ ውጪ እኮ መግዛቴን የሚያውቅ አልነበረም" አልኳት ምን ያክል እንደምትደነግጥና ልታዝንብኝ እንደምትችል እያሰብኩ... ፊት ለፊቴ ያለችው ሴት ግን ፍፁም መረጋጋት ነው የሚታይባት

"ባለሱቁ ባንዴ ሶስት ስትገዢው ተጠራጥሮ ነው። በመንገድ ሳልፍ ጠርቶ የነገረኝ አልዋሽሽም እንደሰማሁ ምድር ነበር የከዳችኝ... ቶሎ ብዬ ቤት ሰመጣ በረንዳ ቁጭ ብለሽ አገኘሁሽ ያኔ ወደቤት ገብቼ ከደበቅሽበት ፈልጌ አገኘሁትና ወሰድኩት....."

"ይቅርታ እማዬ ሁሉም ነገር ጨለመብኝ ከኔ ብሶ አንቺም አንገትሽን ደፋሽ..."

"ይገባኛል ሚጣዬ አሁን ስለ እቅዱ ምን ትያለሽ...." ብላ ሀሳቤን ጠየቀችኝ። እናቴ ለኔ እንዲህ ናት አስፈላጊ ያለችው ነገር ላይ ምን ታስቢያለሽ ብላ ታማክረኛለች። ምንም እንኳን ከልቤ ባልሰማት............
..........ወይም እሷ እያወራች ለጨዋታ ጓደኞቼ ሲጠሩኝ ሳላስጨርሳት ሮጬ ብሄድ..........
....... ወይም ደግሞ የልጅ ሀሳቤን ነግሪያት ሆዷን ይዛ ፍርፍር ብላ ብትስቅ... እናቴ ልጅ ናት ብላ ልትነግረኝ እንደሚገባ ያሰበችውን ለኔ ከመንገር ወደ ኋላ አትልም። በሀሳብ ጭልጥ ብዬ ስሄድባት

" ምን ትያለሽ እያልኩሽ ነው ሚጣዬ" አለችኝ ዘልዬ ጥምጥም አልኩባትና

"እጅግ በጣም ምርጥ ሀሳብ ነው ቶሎ ብለን እናድርገው አልኳት

"ኦ ኦ ልጄ እስከምትወልጂ ድረስ እንደፈለግሽ መዝለልና መንፈራገጥ የለም። በይ አሁን ተነሽ ቁርስ እንብላና ያልኩሽን እናደርጋለን።

ለብቻዬ ሌላ ጀንበር የወጣችልኝ መሰለኝ ...... ብሩህ ተስፋ.....

የተሳፈርንበትን አውቶብስ መስኮት በትንሹ ከፈትኩት፤ በመስኮቱ የሚገባው ቀዝቃዛ አየር ከነፋስ ጋር ተቀላቅሎ በጆሮዬ ላይ ቢያፏጭም ምቾት አልነሳኝም። በመስታወት ውስጥ አሻግሬ ሰማዩን ስመለከት ፀሀይ ደም የተነከረ ሸማ መስላ ከወደ ምስራቅ ብቅ ማለት ጀምራለች። በፎቶግራፍ መቅረት ያለበት ድንቅ የተፈጥሮ ውበት። አይኔን እድማሱ ላይ ሰክቼ በራሴ ከቀናት በፊት የነበረውን ነገር ማስታወስ ጀመርኩኝ።
................

ልክ እንደዛ ስብር እንክትክት ብዬ በነበረበት ሰዓት...... ራሴን ላጠፋ ጫፍ በደረስኩበት ሰዓት..... ሀሳቤን አስቀይሮ በደስታ ያስፈነጠዘኝ የእናቴ እቅድ ይህ ነበር።

" ሁሉም ሰው የሚያውቀው የአባትሽ ወንድም አጎትሽ ያለው አዲስ አበባ እንደሆነ......." አላስጨረስኳትም

"አዎ ግን የሱ እዛ መሆን ለምን ይጠቅመናል"

"እዛ የምንሄደው እሱ አንቺን ለማስተማር ጠርቶሽ እኔ ደግሞ ካንቺ አልለይም ብዬ ነው አሉ.... ይህን ለሚጠይቀን ሁሉ እንነግራለን"

"እሺ ግን መቼም አጎቴ ጋ እንሂድ አትይኝም አይደል" አይን አይኗን እያየሁ ጠየኳት

"ለጊዜው የምናርፈው እሱ ጋር ነው ትላንትና ማታ ሱቅ ሄጄ ደውዬለት ነበር ባይዋጥለትም ሁሉንም በዝርዝር ነግሬዋለሁ"

"ምን እያልሽ ነው እማ... የወንድሜ ልጅ ብሎ አንድ ቀን እንኳን ዞር ብሎ ላላየኝ.... አንቺን ሳይቀር ወንድሙን እንደገደልሽበት ለሚቆጥረው.... ለሚጠላን ሰው ነገርሽው"
አልኳት ያልጠበኩት ነገር ነው

"አዎ እኔም አንቺም ይህን ተፅዕኖ መቋቋም አንችልም። ይሁን ብንል እንኳን የኔ ችግር የለውም አንቺ ግን ይከብድሻል ለህክምና ክትትሉም ሆነ ለትምህርትሽ አዲስ አበባ ይሻልሻል...."

"ግን እዛ ሄደንስ ምን ሰርተን እንዴት ሆነን ልንኖር..." ግራ ግብት አለኝ

" እሱ እያሳስብሽ እኔ እናትሽ ላንቺ አላንስም አንቺንም ልጅሽንም ማኖር አይከብደኝም ዳገት ወጥቼም ሆነ ቁልቁለት ወርጄ ህልምሽን እንድታሳኪ አደርግሻለሁ። ታዲያ ለዚህ ያንቺ ጥንካሬ ወሳኝ ነው። በይ አሁን ለጠየቀሽ ሁሉ ካልኩት ውጪ እንዳትናገሪ ነገሮችን ላስተካክልና በጥቂት ቀን ውስጥ እንሄዳለን።

ከሀሳቤ ስመለስ እናቴን ዞር ብዬ አየኋት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ውስጥ ናት።
መስኮቱን ተደግፌ አይኔን አድማሱ ላይ ተከልኩ

፧፧
ከኔ አካል ቅጥነት ጋር ሲነፃፀር ሆዴ ትልቅ ሆኖ ላየው ይሰቀጥጣል። ምጤ መቶ ሆስፒታል ገብቻለሁ
"አይዞሽ በርቺ..... ግፊ.... አይዞሽ እንደሱ..... በርቺ..... ግፊ" ብዙ ጊዜ ደጋግመው ቢሉኝም ያለኝን አቅም አሟጥጬ ባምጥም ልጄ ሊወለድ አልቻለም። እኔ ግን እቅት ድክም አለኝ የሚሉት በሰመመን ይሰማኛል...

"የልብ ምቷ በጣም እየወረደ ነው ባስቸኳይ ዶክተር ፋሲልን ጥሪ" ልሞት ነው ማለት ነው። የሰዎች መሯሯጥ ድምፅ ተሰማኝ ትንሽ ቆየት ብሎ

"በአስቸኳይ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል አስገቧት ይህቺን የምታክል ትንሽ ልጅ እንዴት በምጥ እንድትወልድ ታደርጋላችሁ..."