Get Mystery Box with random crypto!

'ኧረ ተይ እንደዚህማ አትበይ እናቷ እኮ መድሀኒት ቤት ልካት ስትሄድ አግኝቷት ነው አሉ' የእናቴ | አትሮኖስ

"ኧረ ተይ እንደዚህማ አትበይ እናቷ እኮ መድሀኒት ቤት ልካት ስትሄድ አግኝቷት ነው አሉ" የእናቴ ጓደኛ አየለች

"ኡኡቴ እና ምን ልትልልሽ ኖሯል ልጄ ከኔ ተደብቃ ወንድ ፍለጋ ሄደች ትበልልሽ እናቷ እኮ ነች። ደግሞስ ከመች ጀምሮ ነው ሚጣን መድሀኒት ማስገዛት የጀመረችው...."

ከዚህም የባሱ ብዙ ሽሙጥና ስድቦችን በተቃራኒውም ብዙ አይዞሽ በርቺ የሚሉ ቃላቶችን እሰማለሁ። ለኔ ግን ከአስር አይዞሽ አንድ ምናባሽ ልቤን ያርደው ነበር። ጭምትና በትንሽ ነገር የምበረግግ ፈሪ ሆንኩ።

እኔ እምቢ ብልም በእናቴ ጉትጎታ ወደትምህርት ቤት ሄድኩ። እዛም የባሰው ነገር ጠበቀኝ አንድም ሊቀርበኝ የሚፈልግ ልጅ የለም ሁለም ራቅ ራቅ ብለው በዩኒፎርማቸው ኮሌታ አፋቸውን ሸፍነው ይንሾካሾካሉ።

ሁሉም ነገር ሊያሳብደኝ ደረሰ የሚያውቁኝ እንደማያውቁኝ ሲሆኑብኝ ጓደኞቼ እኔን ለመቅረብ ሲፈሩ ማየት አሳመመኝ። ምንም ሳልል ቦርሳዬን ይዤ ከትምህርት ቤት ወጣሁ። አረማመዴ ሁላ የእልህ ነበር። ቤት ስደርስ እማዬን አሻሮ እየቆላች አገኘኋት...

" ከዚህ ከተማ አስወጪኝ... እማ ለምን እልም ያለ ገጠር አይሆንም ሄጄ የከብት እረኛም ቢሆን እሆናለሁ ብቻ ከዚህ አርቂኝ ' እግሯ ላይ ተደፍቼ እየተንሰቀሰኩ ለመንኳት

"ችግርሽ ሳይገባኝ ቀርቶ መሰለሽ እኔም ወሬው ሰልችቶኛል የኛ ሰፈር ሰው እንኳን ይቺን አግኝቶ.... እህ.. መች አጣሁት... ግን የፖሊሶቹ ምርመራ አልቆ ያን እርኩስ ሰው ታስሮ ሳላይ ከዚህ ንቅንቅ አልልም። ያኔ እውነቱ ሲታወቅ አንቺም ቢሆን አንገትሽን ቀና አድርገሽ ትሄጃለሽ" እንባዬን ጠራርጋ እና አባብላ ብዙ መከረችኝ ምክሮቿም ብርታት ሆኑኝ።

ምንም እንኳን በተኛሁበት መበርገጌ የምጥ እንቅልፍ መተኛቴ ባይቀርልኝም የሰፈሩ ሰው ግን ቀስ በቀስ ወሬውን እየረሳው ጓደኞቼም " ነይ እንጫወት" እያሉ መምጣት ጀመሩ።

ትምህርት ቤትም ተማሪዎቹ እንደድሯቸው ሆኑልኝ እኔ ግን እንደድሮዬ መሆን አቃተኝ ትምህርት ስማር በሀሳብ ጭልጥ ብዬ እሄዳለሁ... ወንድ አስተማሪ ሲገባልን እሱም ልክ እንደዛ ሰው አውሬ እንደሆነ አስብና እጠላዋለሁ ከመምህሩ እኩል የሚያስተምረውም ትምህርት ያስጠላኛል። እንዳዛ እንደዛ እያለ የእናቷ " ሚጣ" እኔ 'ህያብ በዛብህ' ከማንነቴ ተፈናቅዬ እንዳልነበርኩ ሆንኩ። ሰው ሲያየኝ እንደበፊቱ ብመስልም ውስጤ የተረበሸ ከተማ ሆነ።
....
ከአራት ወር የፓሊሶች ምርመራ እና ድካም በኋላ ውጤቱ ፍሬ አልባ መሆኑን ለእናቴ ነገሯት.... ደፋሪዬ ደብዛውም የለም። እኔ በነገርኳቸው ትንሽ ምልክት ብቻ እሱን ለማግኘት መሞከር እንደሚከብዳቸው ስለገባኝ አላዘንኩባቸውም።
...

ከእለታት በአንደኛው እሁድ
ፀጉሬን ከታጠብኩ በኋላ ገላዬን ልታጠብ የበርሜል ጉራጅ ላይ ቁጭ ብዬ ሙቅ ውኋዬን እስከምታመጣ እናቴን እየጠበኩ ነው። ውሃው መጣና እኔ ከፊቴ እናቴ ደግሞ ከጀርባዬ እያጠበችኝ
"እስኪ እጅሽን ዞር አድርጊ አሁን በዚህ ጭራሮ እጅሽ አሽተሽው ነው የሚጠራው..." ሁሌም እናቴ ከፊት ለፊቴ ልታጥበኝ ስትል የምትለው ነገር ነው። ልማዴ ስለሆነ እኔም አልቃወማትም እጄን ከፍ አድርጌላት እያጠበችኝ ድንገት የያዘችውን ውሃ የያዘ ጆግ ለቀቀችው። በርሜል ውስጥ ስለወደቀ ከስር ያለው ውሃ ተፈናጥሮ አለበሰኝ።

'እንዴ እማ ምን ሆነሽ ነው ታጥቤ ታጥቤ' ተነጫነጭኩና ጆጉን አንስቼ ውሃ ልቀዳ ስል

"ቆይ ቆይ ቆይ እስኪ አንዴ ቁሚ" አለችኝ። ቀና ብዬ ሳያት ደንግጣለች

'እማዬ ምን ሆነሻል' አልኳት

"ወሬውን ትተሽ ያልኩሽን አድርጊ" ብላኝ እየተርበተበተች እጄን ይዛ አቆመችኝና ፍጥጥ ብላ ሆድ ሆዴን ካዬች በኋላ

"ልጄ" አለችኝ በሚያሳዝን ቅላፄ

'ወዬ እማ ለምን ነው እንደዚህ የምታይኝ'

"ሆድሽ" ጎንበስ ብዬ አየሁት እኔንም አስደነገጠኝ

'አብጦ ነው እማ? ወይስ እንደ ምንትዋብ ቁዝር ልሆን ነው' አልኳት። ቀጫጫዋ እና ሆዷ ቁዝር ያለውን የክፍላችንን ልጅ ምንትዋብን አስታውሼ ማንም ምንትዋብ ብሎ የሚጠራት የለም ሁሉም "ቁዝር" ነው የሚሏት። እኔም እንደሷ ቁዝር እየተባልኩ የተማሪዎች መሳለቂያ ልሆን ነው.... ወይኔ... ከሄድኩበት ሀሳብ እናቴ ልብሴን እላዬ ላይ ስታሳርፈው ተመለስኩ

'እንዴ እማ በደንብ ሳልታጠብ' እንዳልሰማ ዝም ብላ አለበሰሽኝና እየተጣደፈች ወደቤት ገባች። ተከትያት ገባሁ ነጠላዋን ለበሰችና እኔንም አነስ ያለች ፎጣ አለበሰችኝ

'ወዴት ልንሄድ ነው እማዬ'

"ሀኪም ቤት"

'ሳልታመም'

"አይ ታመሻል" እጄን ይዛኝ ስትሄድ በዝምታ ተከተልኳት
....
እናቴ ቁጭ ብላ እንባዋን ታዥጎደጉደዋለች። እኔ በድንጋጤ ደርቄ ምን ማሰብ እና መናገር እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ ቆሚያለሁ። ድንገት የሆነ ሀሳብ መጣልኝና ከቆምኩበት ኮሊደር ላይ ሳላንኳኳ የዶክተሩ ቢሮ ገባሁ።

"አቤት ህያብ" አለኝ ዶክተሩ ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ካየኝ በኋላ

'ማስወረድ እፈልጋለሁ' አልኩት

"ምን" የሚል ድምፅ ስምቼ ስዞር እናቴ ከኋላዬ ቆማለች።

ይቀጥላል