Get Mystery Box with random crypto!

የእናቴ ልጅ ክፍል ሰባት በሕይወቴ ውስጥ እንደዛን ቀን የማይነጋ ለሊት አይቼም | አትሮኖስ

የእናቴ ልጅ
ክፍል ሰባት

በሕይወቴ ውስጥ እንደዛን ቀን የማይነጋ ለሊት አይቼም አላውቅ ፡እናቴ የተፃፈውን ደብዳቤ እጆቿ እየተንቀጠቀጡ ስትገላልጠው ፡ የወረቀቱ ድምፅ በራሱ ሽብርን ለቀቀብኝ ፡ አቤል ተረጋግቶ ወደ እናታችን ተጠግቶ ቆመ ፡ ለራሴ በቃ ለሚመጣበት ነገር ሁሉ ተዘጋጅቷል ማለት ነው ፡በይሆንማ ኖሮ ጉዱን ከቤት ውስጥ አምጥቶ እንዲ ግድ የለሽ አይሆንም ስል አሰብኩ ፡ግን እኔ የሱ ሁኔታ ብዙም አላሳሰበኝም ከዛ ይልቅ እናቴ በጣም የምታምነውን ልጇን ማጣቷን ስታውቅ የሚሰማት መሰበር ነው ያስጨነቀኝ ፡ እናቴ ደብዳቤውን ማንበብ ስትጀምር ይበልጥ ተንቀጠቀጠች ፊቷ ተለዋወጠ ፡ ጉድ ፈላ አልኩኝ ፡በቃ አቤልን ከማነቋ በፊት አንድ ነገር ለመፍጠር ተዘጋጀው ፡እሱን ካጠገቧ አርቄ ነገሮችን ለማረጋጋት...
"እናቴ ደና ነሽ"ብዬ ስጠጋት ደብዳቤውን ጥላ በሕይወቴ አይቼ የማላውቀውን ጥፊ አሳረፈችብኝ፡በድንጋጤ ወደዋላ ተመለስኩ ፡ እንዴ የእናት ጥፊ እንደዚ ያማል እንዴ ? እንጃ ... አፍንጫዬ አካባቢ እርጥበት ተሰማኝ በእጄ ጠርጌ ሳይ ደምቻለው ፡ምንድነው ጉዱ የወንድሜን ንዴት እኔ ላይ እየተወጣችብኝ መሰለኝ ፡ ወንድሜ ደሞ ይባስ ብሎ ከሷ አራቀኝ እና እንዳልጠጋት አስጠነቀቀኝ ፡ በዚ ጊዜ ዕፃኗ ለቅሶዋን አሰማች ፡ሁሉም ነገር ድንግርግር አለብኝ የአፍንጫዬን ስር በጥፊ የበጠሰችኝ ይመስል ደሙ አልቆም አለኝ ፡ እናቴ የዕፃኗን ጩኽት ላለመስማት ሁለቱንም ጆሮዎቿን በመሸፈን
"ዲቃላኽን ይዘኽልኝ ውጣ አንተ አሰዳቢ"ብላ አንቧረቀችብኝ ፡ ማን እኔ ጉድ ነው እንዴት ነው ነገሩ ልጅቷ የኔ እንደሆነች ነው እንዴ የምታስበው ፡ በፍጥነት የጣለችውን ወረቀት አንስቼ አነበብኩት፡"ለናታኒየም ሚጡ ነኝ አዝናለው ልጅህን የማሳድግበት ምንም አቅም የለኝም የፈለከውን አድርገህ እኔን መከራ ውስጥ ከተህ መተኛት ካማረህ ተሳስተሃል ሳልፈልግ የሰጠኸኝን ዘር ልኬልሃለው እንደፈለክ ማድረግ ትችላለህ ቻዎ"እኔ አላምንም ለረጅም ደቂቃ አፌን ከፍቼ አቤልን ማየት ጀመርኩ ፡ ወንድሜ በኔ ላይ አላከከው በትክክል የሱ አሳብ መሆኑን አውቄሃለው ፡ምን ቢጠላኝ የዚን ያክል ግን በኔላይ ያምፃል ብዬ አላሰብኩም እናቴን ለማስረዳት አስቤ ደግሜ ተጠጋዋት ፡ በፍፁም ጥላቻ ተሞልታ ጣቷን ቀስራ
"ዲቃላህን ይዘህ ውጣ አሁኑኑ"አለችኝ ፡አስተያየቷ ስብርብር አደረገኝ ፡በተራዬ እኔ መንቀጥቀጥ ጀመርኩ ፡ ሕይወቴ ይበልጥ ሲመሰቃቀል ታየኝ ፡አቤል እናቴ ደግፎ እያስቀመጣት ማፅናናት ጀመረ ፡ ግራ ገባኝ እውነት ይሄ የ እናቴ ልጅ ወንድሜ ነው ፡ እስኪ ምን ብበድለው ነው እንዲ የሚያደርገኝ እኔ ላይ ከሚያላክክ ፡ምን አለ ተጥላ ነው ያገኘዋት ቢል ፡ ፍፁም ጤንነቱን ተጠራጠርኩ ፡የምታምነውን እና የምትሳሳለትን እናቱን ፡እንዴት ይዋሻታል ፡ ጠጋ አልኩትና
"አቤል ወጣ ብለን እናውራ"አልኩት ፡
"ከኔጋር የምታወራው ነገር የለም ፡እሷ የምትልህን አድርግ አለኝ አፉን ሞልቶ።ተስፋ ቆረጥኩ ፡ወደበሩ አየው ከምሯን በዚ በለሊት ዕፃን አሲዛ ልታባርረኝ ነው እናቴ ለዛውም ባልወለድኩት ልጅ ይሄን ማመን ከበደኝ ፡ዕፃኗ ለቅሶዋን አላቆም አለች ፡
"ስማ እማዬን አልሰማሃትም ልጅህን ይዘሃት ውጣ"አለኝ አቤል አይኑን በጨው አጥቦ
"እናቴ እሱ ድሮም አይወደኝም እቺ ልጅ ግን....."
"ምን እቺ ልጅምን የኔ አይደለችም ልትል ነው እናትየው በፃፈችው ደብዳቤ አረጋገጠችልን እኮ"አለ አቤል፡እናቴ ድጋሚ በንቀት እያየቺኝ ወደበሩ አሳየቺኝ ከኔጋ ለማውራት ፍላጎት አጥታለች ፡ተስፋ ቆረጥኩ ፡ዕፃኗን አንስቼ አቀፍኳት በጣም ዕፃን ናት የት ነው በዚ ለሊት ይዣት የምሄደው ፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎርምስና ጀግንነቴ ተፈተነ አይኖቼ ዕንባ አቀረሩ ፡በዘምቢሉ ውስጥ ተጎዝጉዘው ከነበሩት ወፈር ያለውን ፎጣ ሸፋፍኛት ፡ ወደበሩ ተራመድኩ ፡ እናቴ
"ስማ ዛሬ ለሊት ይለፍልህ ነገር ግን እኔ ከመነሳቴ በፊት ቤቱን ለቀ ጥፋልኝ "አለች እናቴ አሳዘነችኝ ከፊት ከዋላዋ ተኩላው ልጇ በፍቅር ሰበብ ሰቅዞ ይዟታል ምንም የምትመረምረውም ነገር የላት ፡ ,,,,,,,,

ደራሲ unknown

ይቀጥላል......
    ሀሳብ አስተያየታችሁን 
@Tsiyon_awit አድርሱኝ
   ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@itsmetsiyearsemalj
@itsmetsiyearsemalj