Get Mystery Box with random crypto!

#አኩርፈሻል_መሰል… ግራ እጄን አመመኝ… ከበረዶ በልጦ ይሄው ቀዘቀዘ መራመድ አቃተው… ለእርምጃ | አትሮኖስ

#አኩርፈሻል_መሰል…

ግራ እጄን አመመኝ…
ከበረዶ በልጦ ይሄው ቀዘቀዘ
መራመድ አቃተው…
ለእርምጃ ሰነፈ ቀኝ እግሬም ተያዘ
የጎረስኩት ሁሉ…
አልጣፍጥህ አለኝ ጣእም ጣ'ሙን አጣ
የመሬት መንቀጥቀጥ…
የሚያስነሳ ንዝረት አናቴ ላይ ወጣ
ሁሉም ፉርሽ ሆነ
ህዝበ አዳም ተቀጣ ሕዝበ አዳም ተቆጣ
አኩርፈሻል መሰል…

ካልጋዬ ተኝቼ..
የምሰማው ዜማ እንቅልፍ እንዲወስደኝ
የነካውን እንጃ …
ባላሰብኩት ቅጽበት እንቅልፌን ነጠቀኝ
ለሽራፊ ጊዜ…
ዜማው አልዘመመም ቅኝቱ አልፈረሰም
ልክ እንደ ጥንቱ ነው የጎደለው የለም
የሆነው ሆኖ ግን…
እንዳረጀ ወንበር…
የሚንቋቋ ሆኖ ለኔ ይሰማኛል
በጨቀየ መንገድ…
ፍሬን እንደያዘ የመኪና ጎማ
ድምጹ እንደሚረብሽ
ልብስ እንደሚያበላሽ
ሰባት አይነት ዘፈን…
እንደለቀቁበት የገበያ አዳራሽ
እንደ ቆራሌው ድምጽ…
እንደ ልዋጭ ጥሪ እንደ ፍራሽ አዳሽ
እንደ ደፈኑት ቦይ …
እንደ አጥር ምሰሶ እንደ ግንቡ ፍራሽ
እንደ ጉቶ ጥላ…
እንደ ጫካ መንገድ እንደ ነገር ብላሽ
እንደ…እንደ…እንደ…እንደ
እንዲያ ይሰማኛል
አኩርፈሻል መሰል…

የቀየዷት በቅሎ …
የጎፈላ በሬ ያልተገራ ፈረስ
መስኮት የሌለው ዳስ…
በር የሌለው ድንኳን የጨበራ ድግስ
ምስክር የፈራው…
ማህላ የረሳ ሰው ናፋቂ መቅደስ
ከራስ የተጣላ…
ሩሁን የሳተ ጥምጣም የጣለ ቄስ
መምጫው ያልታወቀ…
መሄጃው የጠፋ ከባድ አውሎ ንፋስ
እንዲያ እንዲያ…እንዲያ እንዲያ
እንዲያ ይሰማኛል እንዲያ ይታየኛል
አኩርፈሻል መሰል…

ሰለሞን ሳህለ