Get Mystery Box with random crypto!

የማይቆጠር ጊዜ ቀዬውን ጥዬ ልሄድ አስቤ አውቃለሁ። አንድ ቀን ኪዳን ከትምህርት ቤት ሲመጣ እኔ እ | አትሮኖስ

የማይቆጠር ጊዜ ቀዬውን ጥዬ ልሄድ አስቤ አውቃለሁ። አንድ ቀን ኪዳን ከትምህርት ቤት ሲመጣ እኔ እቤት አልነበርኩም!! እያለቀሰ ስሜን እየተጣራ ሲፈልገኝ አገኘሁት
«ምን ያስለቅስሃል? ማን መታህ?» ነበር እንዳየሁት ያልኩት
«እ እ…. አንቺም እንደእማዬ ትተሽኝ አትሂጂ !! እንደአባዬ አትሙቺብኝ!» ብሎ ሲንሰቀሰቅ መቼም እንደማልተወው ለራሴ ቃል ገባሁ። በጊዜው እኔ ራሱ የሚያባብለኝ የሚያስፈልገኝ እንጭጭ ብሆንም ከእድሜዬ በላይ ሀላፊነትን ለራሴ ሰጠሁት። ከዛ በኋላ ነው ትምህርት ቤት ራሴ አድርሼ እመልሰው የጀመርኩት። ሁሌ ለሊት ተኝቶ ሲነቃ መጀመሪያ የሚያረጋግጠው የእኔን አልጋዬ ላይ መኖር ነው። ድንገት ቀድሜው ተነስቼ ካጣኝ በማጣት ሰቀቀን ሲፈልገኝ አገኘዋለሁ። የትም ጥየው እንደማልሄድ እንዲያምነኝ ብዙ ለሊት አቅፌው ካደርኩ በኋላ ነው ያመነኝ። የአባቴን ገዳዮች ከጠላኋቸው በላይ ጠላኋቸው።

በሽምግልና የታረቁ ጊዜ የተሰማኝ አጎቴ እንዳለው ቁጣ ብቻ አይደለም። መከዳት ነው የተሰማኝ!! የራሴን ወገኖችም ነው የተቀየምኩት። የእኔ እና የኪዳን ህመም ያላመማቸው ፣ እኔን አግልለው እነሱ የደስታ ጠቦት ጥለው የተቃቀፉ ……

አልገባቸውም!! አድጋ የአባቷን ደም ትበቀላለች ብለው ያጀገኑት ልቤ ውስጥ የበቀል ጥንስሴን እርሾ አድርገውበት ልቤ ልትፈነዳ እንደደረሰች። አልገባቸውም እሷማ ይሄን መንደር ታስከብራለች እያሉ ባሽሞነሙኑኝ ቃላት በጭንቅላቴ ውስጥ ያሉ ሌሎች የሰው ልጅ የመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶቼን ሁሉ አንድ በአንድ በበቀል እንደተካሁ። አይዞሽ፣ በርቺ ብለው እጄን ይዘው ከድልድዩ ካደረሱኝ በኋላ እነርሱ ከጠላቶቼ ጋር ተመሳጥረው ቺርስ የተባባሉብኝ ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ።

የአባቴ ገዳዮች ላደረጉት ነገር ሊቀጡ ሲገባቸው ግፋቸው ጭራሽ ክብር ሆኗቸው ስልጣን ሲሾማቸው የእኔው ወገን ሲያጨበጭብላቸው ብቸኝነት አጥንቴን ሰረሰረኝ። ብቻዬን የቀረሁ። ያውም ከነበቀል ጥማቴ!!

ባገኘሁት ሰው ላይ ሁሉ ከመደንፋት እና ከመደባደብ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስላላወቅኩ የማደርገው ጠፍቶኝ ሳለ ነበር አንድ ቀን ለክረምት ለክረምት አዲስ አበባ የሚሄደው ካራቴ አሰልጣኛችን በጉራ ሰውመሆንና የእሱ ቤተሰቦች አዲስ አበባ የሚጠያየቁ ወዳጃሞች መሆናቸውን ሲያወራ የሰማሁት ……. የዛን ቀን እንቅልፍ አልወሰደኝም!!! ከብዙ ጊዜ በኋላ የበቀል እቅዴን የማሳከበት መንገድ ጭላንጭል የታየኝ ስለመሰለኝ ሳቅኩኝ።

አዲስ አበባ መሄድ የሚለውን ሳስብ ደግሞ ከዚህ መንደር መራቅን አብዝቼ ሻትኩ። አዲስ ህይወት መጀመር የሚል ሀሳብ ልቤን በሀሴት ሞላው። አዲስ ያልኩት ህይወት መሰረቱ በቀል መሆኑ ካለፈው ህይወት ጋር እያመላለሰ እንደሚያላትመኝ የምረዳበት የአዕምሮ ብስለት አልነበረኝም!! ጭራሽም ከበቀል እና ከጥላቻ የተረፈ አዕምሮም አልነበረኝም!! የሚጠረጥርበት ምንም ፍንጭ ያልነበረው አሰልጣኝ አዲስአበባ ለክረምት መሄድ ማሰቤን እና ከተማውን እንዲያስለምደኝ ስጠይቀው ደስ ብሎት ነው የተስማማልኝ። ሰዎችን መጠቀሚያ ማድረግ የጀመርኩበት የመጀመሪያ ቀን መሆኑ ነው። ደሜ ውስጥ ከሚንቀለቀል በቀል ውጪ የሚሰማኝ የህሊና ደውል ስላልነበረ ያደረግኩት ብልጠት እንጂ ክፉት አልነበረም!! እንድደውልለት ስልክ ፅፎ ሰጠኝ።

«ኪዳንዬ ለሆነ ጉዳይ አዲስአበባ ደርሼ እመጣለሁ። ከዛ ግን መጥቼ እወስድህና አብረን እንኖራለን» አልኩት በራችን ላይ ቆሜ እሱ ከትምህርት ቤት መጥቶ እግሩን እየታጠበ ነበር። ያሰብኩት የነበረው ብቻዬን ሄጄ ከሸክም ጀምሮ ምንም ብሰራ ፣ ከዛ የተወሰነ ፍራንክ አጠራቅምና ኪዳንን አዲስ አበባ አምጥቼ አስተምረዋለሁ። ነው። የያዘውን ጆክ በቁሙ ለቀቀው እና እኔጋ መጥቶ እግሬ ላይ ተጠመጠመ። 15 ዓመቱ ነበር። ሁለቱንም እግሬን እንዳልፈናፈን አንድ ላይ ጨምቆ ይዞ

«የትም ትቼህ አልሄድም! ብለሽኝ አልነበር? ለምንድነው ይዘሽኝ የማትሄጂው? በዛው ልትቀሪ ነውኣ? አብሬሽ እሄዳለሁ!!» አለኝ እየጎረመሰ ባለ ድምፁ። አያለቅስም ግን ድምፁ ውስጥ ከለቅሶ የከበደ ሀዘን አለው።

«ኪዳንዬ አሁን ወስጄህ ምን አደርግሃለሁ? የምናድርበት ባይደላን ምን በወጣህ ውጪ ታድራለህ? የምንበላው ባይመቻች በምን እዳህ ትራባለህ? አንተ ገና ልጅ ነህ!! እኔ ይሰናከልብኛል የምለው የለኝም። አንተ ከትምህርትህ ለምን ትሰናከልብኛለህ?»

«ይኸው ትተሽኝ ሄደሽ ላትመለሽ ነው እንዲህ የምትዪኝ» አለ እግሬን ሳይለቅ

«እሺ በቃ ትቼህ አልሄድም!! አብረን እንሄዳለን!» ስል ራሴን ሰማሁት!! እዛው ላይ እንዴትም ብዬ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ የሚለውንም አሰብኩ።

አስቤው አቅጄው ተለማምጄው ያደረግኩት ነገር አይደለም። 19 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ መግደልን እንጂ መስረቅን ለዓፍታም አስቤው አላውቅም!! ለመግደል ለራሴ በቂ ምክንያት ስለሰጠሁት ከመግደል ይልቅ መስረቅ ፀያፍ መሆኑን ነው ህሊናዬ የመዘገበው። በዛው ሳምንት ከአጎቴ ጋር እህል ልንሸጥ ትልቁ ገበያ አጅቤው ሄድኩ። አጎቴ እህሉን እያስረከበ አይኔ ተሻግሮ ከብት የሚገበያዩት ጋር ቀላወጠ። ነጋዴው ምን ያህል ከብት ቢሸጥ ነው እጁን ሞልቶ የተረፈ ገንዘብ የያዘው ብዬ እያሰብኩ ጭንቅላቴ ወዲያው ይሄ ሁሉ ብር ቢኖረኝ ኪዳንን ይዤ አዲስ አበባ የምኖረው ህይወት ታየኝ። ሰውየውን አየሁት አየኝ። ራሴን ገሰፅኩ!!

መረኑ ሀሳቤ <ያውም ጠላትሽ ነው> አለኝ። ለምሰራው ከእነርሱ ለባሰ ክፋት እና በቀሌ የምሰጠው ምክንያት ያ ነው። ድክመቴ!! እናት እና አባት ያሳጡኝ ሰዎች ናቸው!! ከሰውየው አይን ተሰውሬ ገበያውን ለቆ ሲወጣ ተከተልኩት። መውጫው ላይ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ገጥመው ወደቀያቸው የሚወስዳቸውን መንገድ ተያያዙት። አድብቼ ተከተልኳቸው። አስር ወንድ ገጥሜ የማልፈራዋ ሴት እግሬ ተልፈሰፈሰብኝ!! እጄ አላበው!! በጥሻው አልፌ ከፊታቸው ብቅ አልኩ

«ልጎዳችሁ አልፈልግም!! እንደዛ እንዳደርግ አታስገድዱኝ!! ብር ነው የምፈልገው ብራችሁን ብቻ አውጥታችሁ እዚጋ አስቀምጡና ሂዱ!» አልኳቸው። እኔ መሆኔን ሲያውቁ ገና ብርክ ያዛቸው ….. ሽጉጥ መያዜን ሲያዩ በያዙት ሽመል ተስፋ ቆረጡ። አንደኛው ግን ወንድነቱ አነቀው። ሁለቱ ብራቸውን አስቀምጠውት መንገድ ሲጀምሩ እሱ ካልገጠምኩሽ አለ። አልምታህ ብዬ ለመንኩት።

«ግደይኝ» አለ። ቶሎ ካልሄድኩ መንገደኛ መጥቶ ሌላ አምባጓሮ ሊፈጠር እና ፖሊስ ሊመጣ ሆነ። በቆመበት ጉልበቱን ወደጎን ስረግጠው ህመሙ የእኔ ጉልበት እስኪመስለኝ ታወቀኝ። ብሩን አንስቼ ጢሻው ገባሁ። ለዘመናት ያላነባሁትን እንባ እያነባሁ ወደቤት ሮጥኩ። ሰውነትንም ከእንባዬጋ አብሬ አጥቤ ከሰውነቴ አስወጣሁት።

ይቀጥላል.........



ሀሳብ አስተያየታችሁን
@Tsiyon_awit
አድርሱኝ

ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@itsmetsiyearsemalj
@itsmetsiyearsemalj