Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ዘጠኝ) (ሜሪ ፈለቀ) | አትሮኖስ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ዘጠኝ)
(ሜሪ ፈለቀ)

እንዲህ ነው የሚመስለኝ :- የራሴን ህይወት ራሴው ኖሬው እና ሌላ ሰው ሆኜ ደግሞ ከውጪ ሳየው!! ራሴን ሌላ ሰው ሆኜ ባየው ምን አይነት ሰው ነኝ ብሎ አስቦ የሚያውቅ ሰው ይኖራል? እድሉ ተሰጥቶትስ ራሱን ከውጪ ቢያየው ስንት ሰው ራሱን ይወደዋል? ወይስ ይፀየፈዋል?

እንግዲህ መታደል ይሁን መረገም እኔ የደረሰኝ ይህ እጣ ነው!! እንደ ሌላ ሰው ከውጪ ያየኋትን የድሮዋን ሜላት ድጋሚ መኖር ወይም ሌላ ሜላትን መፍጠር ደግሞ ከፊቴ ያሉ ምርጫዎች ናቸው። ሁለቱም አስፈሪ ምርጫ ነው!!!

በደም በተለወሰ ልብሴ ደሙ እጅና ፊቴ ላይ ደርቆ የሆስፒታሉ መጠበቂያ ቦታ ለሰዓታት ከአንዱ ቦታ ወደሌላው እንደፌንጣ እየዘለልኩ ነው ይሄን የማስበው። ስንት ሰዓት እንደጠበቅን ከማላውቀው ጊዜ በኋላ ከዛ ውጥንቅጥ ቦታ ይዞን የመጣው የጎንጥ ወዳጅ ወንበሩ ላይ ከነበረው ሰውነት በግማሽ ያነሰ መስሎ ተኮራምቶ እንደተቀመጠ

«መታጠቢያ እኮ አለ ቢያንስ ደሙን ከሰውነትሽ ታጠቢ!! ወይ መቀየሪያ ልብስ ላምጣልሽ?» ያለኝ እሱም እንደእኔ ሰውነቱ በደም መቅለሙን ሳያውቀው ይሆን እንጃ!! <አንተምኮ ደም ብቻ ነህ!> ማለት እፈልጋለሁ ግን አፌ ተለጉሟል። አውልቄ የጎንጥን ደም ለማስቆም ቁስሉ ላይ ይዤው የነበረውን ሹራቤን ይዞት ነው የተቀመጠው። - የኪዳን መልዕክት!! ዘልዬ ተነስቼ ሹራቡን ስወስድበት ብርግግ ብሎ አፈጠጠብኝ!!

«ሜል ይቅርታ እሺ!! ብዙ የምፅፍበት ጊዜ እና ሁኔታ ላይ አይደለሁም!! ማስታወስ እንደማትችዪ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። ነገሮችን ስገጣጥማቸው ገባኝ!! እመቤትን እመኛት!! ያለችሽ ብቸኛ ጓደኛ እሷ ብቻ ናት!! ሌላው እኔ ማን እንደሆነች ብዙ ያልገባኝ አምነሽ ቪዲዮዎቹን ኮፒ ያስቀመጥሽባት ሴት አሁን ከእነርሱ ጋር ናት!! በቢዲዮዎቹ እየተደራደረች ነው!! እንዳታምኛት!! ታውቂ የለ እወድሽ የለ?»

«ይህቺ ከንቱ!» አልኩኝ ሳላስበው!! ወትሮም ጓደኛዬ አይደለችም!! ጥቅም ነው ያገናኘን!! እኔ ለጥቅሟ የምደምርላት ነገር እንደሌለ ባወቀች ቅፅበት ልትቀብራቸው ጉድጓድ ስትምስ የኖረችባቸው ሰዎች ጋር ሌላ የጥቅም ወጥመድ የዘረጋችበት ፍጥነት ……. ድሮም ትርፍ ካገኘችበት የገዛ ባሏን ከመሸጥ የማትመለስ ነጋዴ መሆኗን አውቃለሁ። የከንቲባው ሚስት ናት!! ባሏ ከንቲባ ከመሆኑ በፊት ከደሳለኝ (ኪዳንን ያገተው ሰውዬ) ጋር ወዳጃሞች ነበሩ!! ለአንድ ቦታ ለመመረጥ ፉክክር እስከጀመሩባት ጊዜ አንዳቸው ከሌላቸው ቤት የማይጠፉ፣ ልጆቻቸው እንደእህትና ወንድም የተቋለፉ ፣ ሚስቶቻቸው ከፀጉር ቤት እስከ ትልልቅ የህዝብ መድረክ ተቆላልፈው የሚተያዩ ዓይነት ነበሩ። ከንቲባው ሞተሩ ሚስቱ ናት እንደፈለገች በቀን ሙዷ የምታሾረው እንጂ የዋህ ቢጤ ነው። ደሳለኝ በገዛ ፍቃዱ ከውድድሩ ራሱን እንዲያገል ያን መረጃ ከእኔ ጋር በልዋጭ ጥቅም ተደራድራ ነው!! ተማምነን አይደለም የጠላቴ ጠላት በሚለው ተወዳጅተን እንጂ!! እከኪልኝ ልከክልሽ ተባብለን ነገር ……. እኔ አደጋ ላይ ብወድቅ እሷጋ ያለው ቅጂ ማስያዣ እንዲሆን ፤ እሷ አደጋ ላይ ብትወድቅ እኔ ጋር ያለው ቅጂ መገበያያ እንዲሆን ነበር ውላችን!! ድንገት በአንድ ቀን ጀንበር ያለድካም የተገነባ መተማመንም አልነበረም!! ከአንዲት 10 ሺህ ህዝብ ከሚኖርባት መንደር ወጥቼ ስልጣኑና አቅሙ አለን ከሚሉት ወንበዴዎች ጋር ለመግባት ለመውጣትስ የተጓዝኩት ጉዞ ቢሆን በቀላል ድካምና ላብ የተገነባ መች ነበር?

«የአቶ ጎንጥ ቤተሰቦች?»

ዘልዬ ተነሳሁ!! ዶክተሩ ከማውራቱ በፊት ነገረ አካላቴን በሀዘኔታ እያየ ነው ቀዶ ጥገናውን በስኬት መጨረሱን የነገረን።

«እስኪነቃ ድረስ እቤት ሄደሽ ተጣጥበሽ ልብስሽን ቀይረሽ መምጣት ትችያለሽ!!» አለኝ የጎንጥ ወዳጅ!! አልሄድኩም!! ተናኜጋ ደውዬ የምቀይረው ልብስ እንድታመጣልኝ አደረግኩ። ስልኩን ስዘጋ ተናኜ መርሳቴን አስታክካ የተቀበለችውን ደሞዝ ድጋሚ እንደተቀበለችኝ አስታውሼ ፈገግ አልኩ። የጎንጥን መመታት ስነግራት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቷስ? የአባቷን ለቅሶ የተረዳች አስመስላ አረፈችው። ልብሴን ቀያይሬ እንድትረጋጋ ላሳያት የተኛበት ክፍል ይዣት ብገባ ተኝቶ ስታየው ያን ለቅሶዋን አመጣችው። የልብሷን አንገትጌ በእጇ ጨምድዳ ይዛ ወደአፏ አስገብታ ንክስ አድርጋ…… <ህእእ > እያለች ሳጎን ወደ ውስጥ እየሳበች ተነፋረቀች።

«ምን ልሁን ነው ምትይ?» ሲል ነው መንቃቱን ያየነው። ይሄኔ ግራ የገባው ስሜት ተሰማኝ። የሆነኛው ልቤ (የሁለት ወሯ ሜላት ልብ ይመስለኛል) ስለነቃልኝ መፈንጠዝ ፣ አጠገቡ ሄጄ መነካካት ያምረዋል። የሆነኛው ልቤ (የድሮዋ ሜላት ልብ ይመስለኛል) ቆጠብ ማለት ፣ ኮስተር ማለት ያምረዋል። አጠገቡ ደረስኩ ግን እጁን ሊይዘው የተዘረጋ እጄ መንገድ እንደሳተ ነገር የአልጋውን ጫፍ ጨበጠ። ቅድም ሁለት ምርጫ አለኝ አላልኳችሁም? ወይ አሮጌዋን መሆን ወይ አዲስ መሆን? ሁለቱንም መሆን እንደማልችል እዚህ ጋር ገባኝ!! ቢያንስ በጎንጥ ጉዳይ!! ልቤ እና ሰውነቴ እንዳልተስማሙ ገብቶታል መሰለኝ ተናኜም ወዳጁም እግራቸው እንደወጣ ጠብቆ

«ተቀይመሽኝ ነው እንዴ?» ሲለኝ እስካሁን ስለማንነቱ፣ ስለዋሸኝ ዘበኝነቱ …… ተያያዥ ነገር ጭራሽ አለማሰቤ ገረመኝ። እዛ መኪናው ጋር ራሱን ከፊቴ አድርጎ የእኔን ሞት የተጋፈጠልኝ ሰዓት መቀየሜን ተውኩት? እዛጋ የበደለኝን አጣፋሁት?

«ቅያሜ አይደለም ያለኝ ጥያቄ ነው» አልኩት። ፈገግ ብሎ <ጠይቂኝ> እንደማለት በእጁ ወዲህ በይው ዓይነት ምልክት ሰራ። ወንበሩን ስቤ ከፊቱ እየተቀመጥኩ። <እዝህችው ቆመን 19 መቶ ብዬ እንዳወጋሽ አይደለማ ሀሳብሽ?> ብሎ የጮኸብኝ ትዝ ብሎኝ

«ገና ከመንቃትህ 19 መቶ ዓመተምህረት ብለህ ልታወጋኝ አይደለምኣ ሀሳብህ? (ፈገግ አለ) አንተ ጥለኸኝ የመጥፋት ሀሳቡ ከሌለህ በቀር እኔ የትም አልሄድም ያንተ እና የእኔ ጉዳይ ይደርሳል። ኪዳንን ጭረት ሳይነካው ዛሬውኑ ከዛ ቤት እንዲወጣልኝ ማድረግ አለብኝ።» አልኩት።

******

ልጅነቴ አጎቴ እንዳለው በጀግንነት እና ጀብድ ብቻ የተሞላ አልነበረም። ያ እነሱን ሆነው ሲያዩት የገባቻቸው ሜላት ናት። አባቴ የሞተበት ቦታ እየሄድኩ ሬሳው የነበረበት ቦታ ተቀምጬ በለቅሶ የምደነዝዝባቸውን የትዬለሌ ሰዓታት እሱ አያውቅም!! እናቴን የደፈራት ሰውዬ ፊት ለዓመታት በህልሜ እኔኑ ሲደፍረኝ እያየሁ በላብ ተጠምቄ ስንቀጠቀጥ የነጉትን ቁጥር አልባ ለሊቶች እሱ አያውቅም። ከሞቱ በፊት የነበረው የአባቴ ፊት ጠፍቶብኝ አባቴን ሳስብ የማስታውሰው የዛን ቀን ያየሁትን ፊቱን እየሆነብኝ ተሰቃይቼ ፎቶውን አቅፌ ማደሬን አያውቅም!! እናቴ ተመልሳ ትመጣ ይሆናል ብዬ ስንት ቀን እንደጠበቅኩ አያውቅም። አባቴን የገደሉብኝን ሰዎች ኮቲያቸውን ልኬት ሳይቀር በጭንቅላቴ ውስጥ ስዬ እንዳስቀመጥኩ አያውቅም!! ብዙ አያውቅም !! ብዙውን አልተናገርኩም!!