Get Mystery Box with random crypto!

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ስምንት) (ሜሪ ፈለቀ) | አትሮኖስ

#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)

መቼም ሰው <ልቤ ዝቅ አለብኝ> የሚለው አሁን እኔ እንደሚሰማኝ ልቤ አቃፊዋን ለቃ የወጣች የሚመስል ስሜት ሲሰማ ነው የሚሆነው። የኔዋማ ዝቅ ከማለትዋም እነ ሳንባ ጉበትን <ዞር በሉ በናታችሁ> ብላ ገፋ ገፋ አድርጋ አንጀቴ ላይ ዛል ብላ ጋደም ያለች ይመስለኛል። አጅሬው እኔን ድዳና ሽባ አድርጎ በድንጋጤ አደንዝዞኝ እሱ እቴ በሙሉ አይኑ እንኳን አላየኝምኮ!!

ለመሆኑ ስሙስ የምር ጎንጥ ነው? የሚያወራው የሀገርኛ ለዛውስ ዘበኛ ለመምሰል ያስመሰለው ይሆን? ቅድም እንዴት ነበር ያወራው? ንፋስ ሲሆን ትከሻው ላይ ጣል የሚያደርጋት ፎጣውስ የትወናው አካል ትሆን? ዘበኛም ሆኖ አንዳንዴ ስንወጣ የሚለብሰውን ዓይነት ጅንስ በሸሚዝ ስለለበሰ የአለባበሱን ትወና መለየት ይቸግራል።

«ስራህንማ በአግባቡ ተወጣህ!» አለችው ሴትየዋ። ሙገሳ አይደለም! የሆነ ለበጣ ያለበት ነገር ነው! ቀጥላ የሆነ በእኔ ፊት ወይም በሰውየው ፊት መናገር ያልፈለገችውን ነገር ለብቻቸው እንዲያወሩ መሰለኝ። « ….. እኔ እና አንተ ብዙ የምናወራርደው ነገር አለ።» ብላ እጁን መንጨቅ አድርጋ ይዛው ልትሄድ ስትሞክር ከተቀመጠበት ሳይነሳ እጁን መነጨቃት። አስከትሎ ከእግሯ እስከ አናቷ በግልምጫ ካበጠራት በኋላ ራሱ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቀድማው ከሳሎኑ እንድትወጣ ምልክት አሳያት። (እንደለመደው ነዳት ብል ይቀላል) በተጫማችው ሂል ጫማ እንደዝግዛግ ያለ አረማመድ እየረገጠች ሳሎኑን ለቃ ስትወጣ ተከትሏት እየተቆለለ ወጣ!! ከትውውቅ አልፈው መደነቋቋል ላይ የደረሱ ወዳጃማሞች መሆናቸውን ለማወቅ ምንም ሂሳብ አያስፈልግም!!

< ሄሎ!! እዚህ ነኝ! ሜላት! አስታወስከኝ? ከአንድ ቀን በፊት እመኚኝ ብለህ እንደወፍጮ ቤት እህል አየር ላይ ያንቀረቀብከኝ? አልታይህም?> ይላል ውስጤኮ አፌን ቃል ማን ያበድረው? ከሳሎኑ ከወጡ በኋላ የሚያወሩት ባይሰማኝም ጭቅጭቅ ላይ መሆናቸው ከድምፃቸው ያስታውቃል። ጎንጥ እንዲህ ይጮሃል እንዴ ሲያወራ? እኔ ንግግሩን ሳልሰማ ድምፁ እንዲህ ያስደነገጠኝ እሷ እዛች ሚጢጥዬ ፊቷ ላይ ሲጮህባት ወትሮም ያነሰች ፊቷ አለመትነኗ!!

የሁለቱ ሁኔታ ግራ የገባው ከመሰለው ሰውዬ ጋር ተፋጠን ሁለታችንም ከማይሰማው የሁለቱ ጭቅጭቅ ቃላት ለመልቀም ጆሯችንን አሹለን እንቃርማለን!! ፀጥ ያሉ መሰለ ወይም ድምፃቸው ለኛ መሰማቱን አቆመ።

«ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?» አለኝ ሰውየው በተፈጠረው ክፍተት። የሆነ ተራ ጥያቄ የጠየቀኝ አስመስዬ አፍንጫዬን ነፍቼ ለማለፍ ሞከርኩ።

«ጊዜ ግን ሲገርም!! በተሰቀለው!! ምንም ምንም አታስታውሺም?» ብሎ ሊገለፍጥ ዳዳው « መቼም ግፍሽ ነው!! በቁጥር እኮ አይደለም አንቺ የህዝብ ግፍ ነው ያለብሽ!! ሃሃሃሃ ሰውኮ የዘራውን ነው የሚያጭደው ሃሃሃ ስንቱን እንዳልከዳሽ የራስሽ ጭንቅላት ይክዳሽ? እረስታለች ሲሉኝ ማመን ያቃተኝ ቀጥ ብለሽ ስትመጪ ነው። ምንም የምታውቂው እና የምታስታውሺው ሳይኖር …… » ብሎ ሲጨርስ

«እኔ እንዳልረሳው አይጠፋህምሳ መቼም!» እያለ ገባ ጎንጥ!! ሴትየዋ ትንሽ ቀይ ፊቷ ሚጥሚጣ የተነፋበት ሰሃን መስሎ ተበሳጭታ ተከትላው ገባች።

«እሷ ትሄዳለች። ወንድምየው እኛጋ ይቆያል።» አለች በኮሳሳ ድምፅ ትዕዛዝም ሀሳብ ማቅረብም በመሰለ አነጋገር - ለሰውየው። ሰውየው ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲደነፋ እና ሲጯጯሁ «ኪዳንን ትቼ አልሄድም!» ያልኩትን የሰማኝ የለም!! ጎንጥ አጠገቤ ደርሶ ቁጢጥ እንደማለት አለ እና

«እባክሽ እንዳታስቸግሪኝ (ይሄኛው ልመና ነገር ነበር) የምልሽን አድርጊ! ካለበለዚያ ያንቺንም የእኔንም የኪዳንንም ህይወት ነው እሳት ምትሰጅበት (ትዕዛዝ ነገር ሆነ) ለዛሬ! ለዝህች ደቂቃ ልታምኝኝ ይቻልሻል? (ልምምጥ ነገር ሆነ)» አልመለስኩለትም!! ሰውየውና ሴትየዋ በጥፍራቸው ቆመው ይጨቃጨቃሉ።

«ታምኚኛለሽ?» ሲል ግን በፍጥነት
«አላምንህም!!» አልኩት። ይህችን ለመተንፈስ ሰዓት እየጠበቅሁ ይመስል ተቅለብልቤ

«ሜላት እኔና አንቺ የምንነታረክበት ጊዜ የለንም! ስትፈልጊ አትመኚኝ ያልኩሽን ካልሰማሽ ሙት ነሽ!! (ይሄ ድብን ያለ ቁጣ ነው!!) እኔ እና አንቺ አሁን ወጥተን እንሄዳለን!! አንቺን እንጂ ኪዳንን አይፈልጉትም!! በምትወጅው ኪዳን ይሁንብሽ ለአንዴ እመኝኝማ! (እዚህጋ እኔን ማስረዳት የደከመው መሰለ) ኪዳን ምንም አይሆንም!! (ድምፁን ቀነስ አድርጎ) ኪስሽው ውስጥ አሁን እንዳታስታውቂ ! ኪዳን መልዕክት አኑሮልሻል!! ከዚህ ከወጣን በኋላ ታይዋለሽ!! አሁን እንሂድ? (ይሄ እባክሽ እንቢ እንዳትዪኝ የሚል ማባበል ነው።)።» ምላሴን ምን ያዘብኝ? እሺም እንቢም ማለት ጠፋኝ!! ሰዎቹ ጭቅጭቃቸውን ማቆማቸውን ያወቅኩት

« I knew it!! ወደሃት ነዋ!» ብላ እግሬ ስር ቁጢጥ ያለውን ጎንጥ በትንግርት እያየችው የሆነ ግኝት የተገለጠላት ዓይነት አስመስላ ስትጮህ ነው። ጎንጥ አቀማመጡን ገና አሁን ያስተዋለው ይመስል ተመንጭቆ ተነስቶ ክምር ተራራ አክሎ ተገተረ። ሴትየዋ አላቆመችም። እንደንቀትም፣ እንደ መገረምም ፣ እንደመናደድም …… እንደብዙ ነገር በሆነ ድምፅ እና እይታ « ጎንጥ ለዝህች? (በአይኗ አቅልላ የጤፍ ፍሬ አሳከለችኝ) ማን ያምናል? በምን አገኘችህ በናትህ?»

«አፍሽ ሲያልፍኮ አይታወቅሽም!! እረፊ ብያለሁ!» ብሎ ተቆጣ።

ቆይ እዚህጋ የትኛውን ሀሳብ አስቀድሜ የትኛውን አስከትዬ የቱን ምኑጋ ሰካክቼ ልከኛውን ምስል ላግኝ? ሰው ሀሳብ ይበዛበታል አይሉም በአንዴ ራሱን ጎንጥን የሚያካክል መአት ሀሳብ ወርውረውብኝ እዛ እንደተቀመጥኩ የሚዘነጉት? ኸረ ቆይ ጎንጥ ወዶኝ ነው የሚለውን ላስቀድም? ኸረ አይደለም! <ይህችን?> ብላ ምላሷ ላይ ያሟሸሸችኝ እኔ አስቀያሚ ነኝ እንዴ? አይደለም ኸረ ቆይ ጎንጥ ሴትየዋን ምን ቢላት ነው እኔን ይዞ እንዲሄድ የተስማማች? ኸረ ሌላው ደሞ እሱስ <ወድጃት አይደለም> ከማለት ይልቅ የሚደነፋው ወዶኝ ነበር ማለት ነው? አይ እነዚህ ሁሉ ይቅሩ እንዴት አምኜው ነው ኪዳንን ትቼው የምሄደው? ግን ምርጫስ አለኝ? ኸረ ኪዳን በምን ቅፅበት ነው መልዕክት ያስቀመጠልኝ? ምን ይሆን የሚለውስ? ደሞ ሌላ አለ እንጂ ቆይ ጎንጥ እኔን ቢወደኝ እሷ ምን እንዲህ ይንጣታል?

በአይኑ ከተቀመጥኩበት እንድነሳ ምልክት ሰጠኝ። በአይኑ አስነሳኝ። እጁን ሰጠኝ ወይም እጄን ተቀበለኝ እኔእንጃ ብቻ እጄን ያዘው እና ወደበሩ መራመድ ጀመረ። ጠባቂዎቹ ትዕዛዝ የሚጠብቁ ይመስላል ከበሩ አልተንቀሳቀሱም!! ሰውየው በአገጩ የሆነ ምልክት ሰጣቸው!! ከበሩ ገለል አሉ!! ሴትየዋ መናጥዋ በረታባት!!