Get Mystery Box with random crypto!

«እመነኝ ጎኔ ይህችን አታልፋትም!! አስከፍልሃለሁ!! እመነኝ ትከፍላታለህ!!» አለች እየጮኸች። | አትሮኖስ

«እመነኝ ጎኔ ይህችን አታልፋትም!! አስከፍልሃለሁ!! እመነኝ ትከፍላታለህ!!» አለች እየጮኸች። <ጎኔ> ብላ ነው ያቆላጰሰችው? ዛሬማ የሆነኛው ፊልም ተዋናይት ሆኛለሁ እንጂ እየሆነ ያለው እውን በእኔ ህይወት እየሆነ ያለ አይደለም!! እንዲህ አፍና ጭራው ያልተለየ እውነተኛ ህይወት ሊኖር አይችልም።
በሩን አልፈን እንደወጣን የቅድሟ ሴት ተቀበለችን። ስመጣ ያሰሩልኝን ጨርቅ ይዛ ስትቀርበኝ የያዘኝን እጁን ለቅቄ በጥያቄ አየሁት!! የታከትኩት መሰለ እና በቁጣ ጮኸ « እየገባሽ አይደለም አንቺን መምረጤ? ከዚህ በላይ ምን ባደርግ ነው የምታምኝኝ በይ? ያለፈውን ካላወቅኩ ነው? አንድም ሳይቀር አወጋሻለሁ! እዝህችው ቆመን 19 መቶ ብዬ እንዳወጋሽ አይደለማ ሀሳብሽ?» ቅድም ሴትየዋ ላይ እንደጮኸው ነው የጮኸው!! ጨርቁን እንድትሰጠው ለልጅቷ እጁን ሲዘረጋ ልጅቷ እንደማቅማማት አለች። ጮክ ብሎ ሲያፈጥባት የመወርወር ያህል እጁ ላይ ጣለችው። ከሁኔታዋ ከዚህ በፊት የሚተዋወቁ የምትፈራው ሰው መሆኑ ያስታውቃል። ምናልባት አለቃዋ ነበር? ዛሬማ የሆነ ፊልም ገፀ ባህሪ ሆኛለሁ።

ከሴትየዋ እጅ ተቀብሎ እሱ እያሰረልኝ እንደዛ እንዳልጮኸ ልስልስ ብሎ ነገር «መግቢያ መውጫቸውን እያየሽ እንድትሄጂ በጀ አይሉሽም!! ለዛሬ የምልሽን እሽ በይ በሞቴ?» አለ። ማደንዠዣ እንደወጉት በሽተኛ ፍዝዝ ድንግዝ አልኩ። ጨርቁን ካሰረልኝ በኋላ እጄን አጥብቆ ይዞ መራመድ ጀመረ። የምረግጠው ምን እንደሆነ ሳላውቅ እግሬን እያነሳሁ ተከተልኩት። መኪና ውስጥ ገባን!! ባላይም መኪናው ውስጥ ከእኔና ከእርሱ በተጨማሪ ያቺ እንደጥላ የምታጅበኝ ሴት እና ሹፌር እንዳሉ አውቂያለሁ። እኔእና እሱ መጓዝ ጀምረን የያዘኝ እጁ መያዝ ብቻ ሳይሆን መዳበስ ነገር ያደርገኛል። ልቤ የምን አጃቢ ናት አብራ የምትቀልጠው? ትንፋሹ እንዳልተረጋጋ ያስታውቅበታል። አካሉም ይቅበጠበጣል። ከእርሱ ሁኔታ በመነሳት አሁንም እርግጠኛ የሆነ ማምለጥ አለማምለጤን ጠረጠርኩ። ቆይ እራሱ የሆነ ቦታ አግቶ ይዞኝ እየሄደ ቢሆንስ? እሱንስ እንዴት አመንኩት?

«ሴትየዋ ማናት? ምንህ ናት?» አልኩት ከዛ ሁሉ አናቴን ከወጠረው ጥያቄ ይሄን ለምን እንዳስቀደምኩ አላውቅም!! በረዥሙ ተንፍሶ

«የልጄ እናት ናት!! ምሽቴ ነበረች» አላለኝም? ከዚህ በላይ ከእውነታ የራቀ ቀን አለ እሺ?
«እ?» የምትለዋ ፊደል ከየትኛው ቃል አምልጣ በአፌ እንደሾለከች አላውቅም!! ብቻ ለምሳሌ <እንደ> ከሚለው ቃል ቢሆን ተጣልተው የፈረጠጠችው …… <ን> ን እና <ደ>ን ትርጉም አልባ አድርጋ ጥላቸው ብቻዋን ስትፈረጥጥ …… ተንደርድራ አምልጣ መሆኑ የሚያስታውቀው አፌ ፊደሏን ሊያስወጣ እንደተበረገደ አልተከደነም!!

«ባሏ ነው!!» አለ አክሎ። ሰውየውን መሆኑ ገባኝ ግን ጭንቅላቴ ውስጥ ሀሳቦቹ ተጠላለፉ ነገር። የሰውየው የአሁን ሚስት የጎንጥ የድሮ ሚስት የልጁ እናት! ከዛ ግን ዛሬም ውሉን ያልጨበጥኩትን ስራ (እገታ እና ስለላ ማለት ይቀላል) አብረው የሚሰሩ? ነው ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ? ይሄ ቢገባኝም እንኳን በ2 ወር ከአስር ቀኔ እንደምንም ያጠራቀምኩትን አዲስ ትውስታ ሁላ ነው የሚያጠፋብኝ።


መኪናው ቆመ። ከአይኔ ላይ ጨርቁ ሲነሳ መኪናዋ የቆመችው ከከተማ የራቀ ጭር ያለ ቦታ መሆኑን አስተዋልኩ። በቅርብ ርቀት የእኔ መኪና ቆማለች። እዚህ ደቂቃ ላይ ማመንም መጠራጠርም አይደለም የተሰማኝ። ምንም ነው!! ጎንጥ ግን የሆነ ነገር እንዳላማረው ያስታውቃል። ዙሪያ ገባውን ከቃኘ በኋላ እስከአሁንም ያልለቀቀውን እጄን አፈፍ አድርጎ ወደመኪናችን እየሄድን።

«ከአይናችን ተሰወሩ ማለት የሉም ማለት አደለም!! አሁን አንቺን ማጥፋት ቀላሉ መፍትሄያቸው ስለሆነ ማስታወስ ችለሽ ከምትፈጃቸው በፊት የአቅማቸውን ይሞክራሉ።» እያለኝ እኔን ባልያዘው እጁ ወገቡ ላይ ያለ ሽጉጡን ጨብጦ ወደኋላ እና ወደጎን እየተገለማመጠ መሬቱን በረጃጅም እርምጃው ይመትረው ጀመር። ያደረሰችን መኪና ከኛ በተቃራኒ አቅጣጫ ሄደች። ከአይናችን ስትሰወር መኪናችንጋ ደርሰናል። ስንቀርብ የመኪናችን ጎማ መተኛቱን አይቶ ጎንጥ ጎማውን በእግሩ ሲነርተው አየሁ።

ከየት መጣ ሳይባል አንድ ፒካፕ መኪና እየበረረ ፒስታውን መንገድ አቧራ እያጨሰ መጣ። እየሆነ ያለው ነገር ከመፈጣጠኑ የተነሳ ውዥብርብር አለብኝ። በቅፅበት የተኩስ ድምፅ ተሰማ!! ማናቸው ቀድመው እንደተኮሱ እንኳን አላውቅም ምክንያቱም ጎንጥም እየተኮሰ ነው። በየትኛው ቅፅበት ሽጉጡን እንዳወጣ እንኳን አላየሁም!! የትኛው ቅፅበት ላይ እጄን እንደለቀቀኝም አላውቅም! ማየት እስኪያቅተን የበዛ አቧራ እያቦነነ እና እየተኮሰ አልፎን የሄደው መኪና በሄደበት ፍጥነት አዙሮ ተመልሶ ወደእኛ ሲመጣ በአንድ እጁ የመኪናውን በር ከፍቶ

«ግቢ!! ገብተሽ ወደታች ዝቅ በይ!!!! ከወለሉ ተኝ!» ብሎ ጮኸ! ምንድነው እግሬን ከመሬቱ የሰፋው? እኔ የድርጊቱ አካል ያልሆንኩ ይመስል ዓይኔ አንዴ ጎንጥን አንዴ በፍጥነት እየመጣ ያለውን መኪና ያያል። በሩን ከፍቶበት በነበረው እጁ ከጎኑ ወደጀርባው ገፈተረኝ። አፈሰኝ ማለት ይገልፀዋል። እኔንም ራሱን መከላከል የማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተትኩት ገብቶኛል ግን በምን በኩል ሰውነቴን ልዘዘው? ዓይኔ ስር ፊልም እየተሰራ ያለ ዓይነት ስሜት ነው ያለው። እኔን ወደጀርባው በደበቀኝ ቅፅበት ለጊዜው ምኑጋ እንደሆነ ያልለየሁት ቦታ እሱ ተመታ። እኔ የተመታሁ ዓይነት መሰለኝ። ጭንቅላቴ ለቅፅበት ያን ቦታ ትቶ ሄደ። ቅፅበት ናት ግን ድንዝዝዝ ያለ..... ብዥዥዥ ያለ ቅፅበት .... ጎንጥ የተመታበትን ቦታ በአንድ እጁ ይዞ

«ወዳጄ ይደርሳል። ከእርሱ ጋር ሂጂ!! እቤት እንዳትሄጅ!! » ይለኛል ጮክ ብሎ!!

«ትቼህማ አልሄድም!!» ዓይኔ ከፒካፑ መኪና ጀርባ እየመጣ ያለ መኪና በአቧራው ውስጥ ቢያይም ጭንቅላቴ ግን እዛው ገትሮኝ ሄዷል። አንድ ጥይት በጎኔ አልፎ መኪናውን ደነቆለው:: ሰውነቴ አይታዘዝም!! ደንዝዟል::

"ዝቅ በይ!" እያለ ይጮሃል ጎንጥ በከፊል ዘወር ሲል ከጎኑ የሚፈስ ደሙን እያየሁ ሀሳቤ ሄደ .... እዛ ቀን ላይ!!

ጥይቱ የተከፈተ የመኪናዬን መስኮት አልፎ ጡቴ ስር ሲመታኝ!! የመጀመሪያውን ህመም በቅጡ አስተናግጄ ሳልጨርስ ሁለተኛው ተመሳሳይ ቦታ ሲያገኘኝ። - የተመታሁ ቀን!! አንድ በአንድ ቁልጭ ብሎ ስዕሉ ጭንቅላቴ ውስጥ መጣ!! የማደርገው እና የማስበው በአንድ እኩል ቅፅበት ነበር። እጄን ማዘዜን አላስታውስም ብቻ ከጎንጥ እጅ ላይ ሽጉጡን እንደቀማው አውቃለሁ። ክፍቱን በተተወው የመኪና በር ግማሽ ሰውነቴን ከልዬ ሳደርገው የኖርኩት ልምዴ መሆኑን እርግጠኛ የሆንኩበትን ድርጊት እከውናለሁ። ከኋላ የመጣው መኪና በእኛና በፒካፑ መሃል ገብቶ ቆመ።

« ሂጅ እኮ አልኩ!!» ብሎ አምባረቀብኝ። በእጁ ጎኑን ደግፎ መሬቱ ላይ ተቀምጦ የመኪናውን ጎማ እንደተደገፈ።

«ደፋር እየሸሸ አይሞትም! እየተዋጋ እንጂ!» ስለው በህመሙ መሃል በስቃይ የታጀበ ፈገግታ አሳየኝ። ትውስታዬ ሳይከዳኝ በፊት አዘውትሬ የምለው አባባል ስለነበር ገባው። ጭንቀቱ የቀለለው መሰለ እና ህመሙን ማድመጥ ጀመረ። ፒካፕዋ መኪና ከአይኔ ራቀች። ወዳጄ ነው ያለው ሰውም ከመኪናው ወርዶ ወደኛ መጣ!! ሁለት ቦታ ነው የተመታው። አንዱ ከትከሻው ዝቅ ብሎ ሌላኛው ጎኑ ላይ የጎድን አጥንቶቹ መሃል ……. የለበስኩትን ሹራብ አውልቄ የሚንዥቀዥቅ ደሙን ለማቆም ከአንዱ ቁስል ወደ አንዱ እላለሁ።