Get Mystery Box with random crypto!

#Update የተማሪዎቹን ጥያቄ በትምህርት ሚኒስቴር ህጋዊ አሰራር ብቻ እንደሚመለስ የመቀሌ ዩ | ATC NEWS

#Update

የተማሪዎቹን ጥያቄ በትምህርት ሚኒስቴር ህጋዊ አሰራር ብቻ እንደሚመለስ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

ከሰሞኑን በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የተካሄደው ሰልፍ ከዩንቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውጪ ነው ሲል ያስታወቀው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረውን ነገር በሶሻል ሚዲያ መከታተሉን ገልፃል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞብናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር፡፡

ይህንን በተመለከተ ኢትዮ ኤፍ ኤም የዩኒቨርሲቲውን የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴን አነጋግሯል ፡፡

ዳይሬክተሩ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱ በኮሮና ከዛም በጦርነት ምክንያት ተቆርጦ መቆየቱን አስታውሰው ነገር ግን ከፕሪቶያው የሰላም ስምምነት በኃላ ትምህርት መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በተቻለ አቅምም በግቢው ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር በመደበልን መሠረት ከ11ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለን እያስተማርን እንገኛልን ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ ከዚህ ዓመት ቀጣይ አንድ ሴሚሰተር ይቀራቸው የነበረ ሲሆን ይህንን መቀበል ባለመቻል ሰለማዊ ሰልፉን አካሂደዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሀገር ደረጃ የመውጫ ፈተና የሚሰጠው ሁለት ጊዜ በመሆኑ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ግንቦት ከጨረሱ በኃላ ፈተናውን ለመውሰድ አንድ ሴሚስተር እንደሚቀራቸው አስታውሰዋል፡፡

ይህንንም በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን የገለፁት ዶክተር ትካቦ ይሁን እንጂ ከስብሰባው ከወጡ በኃላ ከግቢው ውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያካሂዱ በቅተዋል ነው ያሉት ፡፡

የተማሪዎቻችን ጉዳይ አጠቃላይ የዩኚቨርስቲው ጉዳይ በመሆኑ ጉዳያቸውን እየተከታተልን እንገኛለን ያሉ ሲሆን አሁንም ቢሆን በህጉ መሠረት ብቻ ነው መሄድ የሚኖርብን ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ የተራዘመ የመመረቂያ ጊዜን በመቃወም ሰልፍ የወጡ ሲሆን ፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እና እንግልት እንደፈፀሙባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡

[ኢትዮ ኤፍ ኤም]
ለጥቆማ @atc_newsbot
https://t.me/atc_news